የበረቱ ክርስቲያኖች ከጸሎተ ሐሙስ በኋላ እስከ ትንሣኤ ድረስ አይበሉም፡፡

ሁሉም ያለው ዝቅ ብሎ ከፍ ካደረገ፤ ምንም የሌለው ከፍ ብሎ ለምን ዝቅ ማለትን መረጠ? ትሑት ሁሉም ከእርሱ ጋር ነው፤ ትእቢተኛም ምንም ከእርሱ የለም፤ ቅዱስ መንፈስ የተገባች ለትሑቶች ነውና፤ ጌታ ዓለምን ከፈጠረበት፣ “ምድርን ያለ ካስማ፣ ሰማይንም ያለ ባላ” ካቆመበት፣ በሰማይም በምድርም ያለውም ፍጥረት ሁሉ ከፈጠረበት ይልቅ ሰው ሆኖ ሞቶ ሰውን ያዳነበት ይልቃል ይላሉ፡፡ ለምን ካሉ የማይሞተው ሞቷልና፤ ሞትንም አሸንፏልና፡፡ በእርሱ ላይ መቃብር ስልጣን የለውም፡፡ ይልቁንስ በሁሉም ላይ እርሱ ስልጣን አለው፡፡

“ሁሉም በእርሱ ሆነ” እንዳለ ሁሉም በእርሱ ነው፡፡ ያለ እርሱ የሆነ ነገር የለም፤ አልተደረገም አልሆነም፤ አይሆንምም፡፡ በሞቱ ሕዝብን አዳነ፤ አዳኝ ሆኖ ሳለ በስጋው መከራን ተቀበለ፡፡

ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው። እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው ሐሳብ ካገባ በኋላ ኢየሱስ አብ ሁሉን በልጁ እንደ ሰጠው ከእግዚአብሔርም እንደ ወጣ ወደ እግዚአብሔርም እንዲሄድ አውቆ ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፡፡ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፡፡ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ያብስ ጀመረ። ወደ ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም “ጌታ ሆይ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?” አለው። ኢየሱስም መልሶ “እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም በኋላ ግን ታስተውለዋለህ” አለው። ጴጥሮስም “የእኔን እግር ለዘላለም አታጥብም” አለው። ኢየሱስም “ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” ብሎ መለሰለት።

ጴጥሮስም “ጌታ ሆይ እጄንና ራሴን ደግሞ እንጂ እግሬን ብቻ አይደለም” አለው። ኢየሱስም “የታጠበ እግሩን ከመታጠብ በቀር ሌላ አያስፈልገውም ሁለንተናው ግን ንጹሕ ነው፤ እናንተም ንጹሐን ናችሁ ነገር ግን ሁላችሁ አይደላችሁም” አለው። አሳልፎ የሚሰጠውን ያውቅ ነበርና ነው፡፡ እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፡፡ እንዲህም አላቸው “ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን? እናንተ መምህርና ጌታ ትሉኛላችሁ እንዲሁ ነኝና መልካም ትላላችሁ። እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል። እኔ ለእናንተ እንዳደረግሁ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻችኋለሁና። እውነት እውነት እላችኋለሁ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም። መልእክተኛም ከላከው አይበልጥም። ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን ናችሁ።”

የፋሲካ በዓል ደረሰ፡፡ ጌታን መያዝ የሚሹ ሁሉ እንዴት እንደሚይዙት ያስቡ ነበር፡፡ በነቢያት የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ግድ ሆነ፡፡ ኢየሱስም በሰማይ ለአዳም ቃል የገባለትን ይፈፅም ዘንድ ጊዜው እየደረሰ ነበርና ቃሉን ይፈፅም ዘንድ ተነሳ፡፡ ጌታን ከተከተሉ ሐዋርያት መካከል በአንደኛው ሰይጣን ገባ፡፡ ጌታን እንዴት አሳልፎ እንደሚሰጥ ተዋዋለ፡፡ 30 ብር ተቆረጠለት፡፡ መድኃኒት ክርስቶስን በ30 ብር ለመሸጥ፡፡ ይህችም ቀን ሐሙስ ነበረች፡፡

ኢየሱስ አትክልት ወዳለበት ስፍራ ወደ ቄድሮን ወንዝ ማዶ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወጣ፡፡ እርሱም ደቀ መዛሙርቱም በዚያ ገቡ። ይሁዳ ጭፍሮችንና ከካህናት አለቆች ከፈሪሳውያንም ሎሌዎችን ተቀብሎ በችቦና በፋና በጋሻና ጦር ወደዚያ መጣ። ኢየሱስም የሚመጣበትን ሁሉ አውቆ ወጣ። “ማንን ትፈልጋላችሁ” አላቸው። “የናዝሬቱ ኢየሱስን” ብለው መለሱለት። “ኢየሱስ እኔ ነኝ” አላቸው። አሳልፎ የሰጠውም ይሁዳ ደግሞ ከእነርሱ ጋር ቆሞ ነበር። እንግዲህ እኔ ነኝ ባላቸው ጊዜ ወደ ኋላ አፈግፍገው በምድር ወደቁ። ደግሞም “ማንን ትፈልጋላችሁ” ብሎ ጠየቃቸው እነርሱም “የናዝሬቱ ኢየሱስን” አሉት። ኢየሱስ መልሶ “እኔ ነኝ አልኋችሁ እንግዲህ እኔን ትፈልጉ እንደ ሆናችሁ እነዚህ ይሂዱ ተዉአቸው” አለ፡፡ ይህም “ከእነዚህ ከሰጠኸኝ አንዱን ስንኳ አላጠፋሁም” ያለው ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።

በባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአራቱ ጉባያት መምህርና የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መላክ እንዳሉት ክርስቶስ በጸሎተ ሐሙስ ቀን ትሕትናን አሳዬ፤ አስቀድሞ ጴጥሮስ እንደሚክደው አውቆ ሳለ ጴጥሮስን አጠበው፡፡ ቅዱሳን እግዚአብሔርን ይመስሉታል፡፡ የሰው ልጅም እግዚአብሔርን መምሰል ከፈለገ ትሑት መሆን አለበት፡፡ ትእቢተኞች ይዋረዳሉ፤ ትሑታን ከፍ ይላሉና፡፡

በኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ ሥርዓት በጸሎተ ሐሙስ ቀን ከካሕናት ትልቁ ታናናሾቹን ያጥባል፡፡ ሊቀ ጳጳሱም ካሉ ሊቀ ጳጳሱ ተንበርከው የአገልጋዮችን እግር ያጥባሉ፡፡ ኢየሱስ የፈፀመውን ሁሉ ይፈፅማሉ፡፡ ትሕትና ስርቷልና ትሕትናውን ይሠራሉ፡፡ ካሕናቱ እግራቸውን የሚታጠቡት በለመለመ ቅጠል ነው፡፡ ይህም የልምላሜው ዘመን፤ መልካሙ ዘመን መድረሱን የሚያመላክት ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የነበረው መታጠብም ከሐጥያት የመንጻት ዘመን መድረሱን የሚያመላክት ነበር፡፡

ከሰሞነ ሕማማት ቀን ሐሙስ የተለያዬ ስያሜ ይሰጣታል፡፡ ሎት የተደረሰባት ነበርና “ሎተ ሐሙስ” ትባላለች፡፡ ዝቅ ብሎ የሐዋርያትን እግር አጥቧልና ይህም ኢየሱስ የዓለምን ሐጥያት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ያሳያልና ቀኗም “ሕፅበተ ሐሙስ” ትባላለች፡፡ ከሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቍርባን በዚህ ቀን ተመሥርቷልና ዕለቱ “የምሥጢር ቀን”ም ይባላል፡፡ ይኸውም ጌታ ኅብስቱንና ጽዋውን አንሥቶ “ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል ላይ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱም ጠጡ” እንዳለ ነው፡፡

ክርስቶስ መሥዋዕተ ኦሪት መቅረቱን አሳዬ፤ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመኾኑ ይህ ዕለት “የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ” ይባላል ይላሉ ሊቃውንት፡፡ ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታ ለአዳምና ለልጆቹ ዅሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለኾነ ሐሙስ “የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ” ተባለ ይላሉ፡፡ ዕለቷ ለኃጢያትና ለዲያብሎስ ባሪያ ኾኖ መኖር ማብቃቱ የተገለጠበት፤ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለ ኾነ “የነጻነት ሐሙስ” ይባላልም ብለዋል፡፡

የበረቱ ክርስቲያኖች ከጸሎተ ሐሙስ በኋላ እስከ ትንሣኤ ድረስ አይበሉም፡፡ ኢየሱስ ለሰው ዋጋ ሰጥቶ ከሰማየ ሰማያት እንደወረደ ሁሉ የሰው ልጅ አምላኩ ዋጋ ለሰጠው ፍጡር ዋጋ መስጠት አለበት ነው ያሉት ሊቁ፡፡

ፈጣሪ ያከበረውን ፍጡር አክብር፤ ትሕትናን ከእርሱ ተማር፤ በብርሃን ውስጥ ዓይንህን ካጨለምክ ጨለማ ይመጣብሃል፤ ብርሃን ይርቅሃል፤ በጎ ነገር በበዛባት ዓለም ውስጥም ክፉን ከመረጥክ መከራው ይመጣብሃል፡፡ በጎውን ምረጥ ትሑት ሁን ያን ጊዜ ያሰብከው ይሳካል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//dooloust.net/4/4057774