ከሁሉም በላይ መቅደም ያለበት የሰው ደህንነት ነው፤ ሰው በህይወት የመኖር ተስፋ ሲኖረው ልማቱም ትርጉም ይኖረዋል – የአባይ ውሃ ጉዳይ ተደራዳሪ ኢንጂነር

በተለያየ አቅጣጫ የሚካሄደው ልማት ትርጉም እንዲኖረው ሰው በህይወት የመኖር ተስፋው ሊለመልም እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኤክስፐርቶች ፓናል ሰብሳቢና የአባይ ውሃ ጉዳይ ተደራዳሪ ኢንጂነር ጌድዮን አስፋው አመለከቱ።

ኢንጂነር ጌድዮን በተለይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ እንዳስታወቁት፤ ከሁሉም በላይ መቅደም ያለበት የሰው ደህንነት ነው፤ ሰው በህይወት የመኖር ተስፋ ሲኖረው ልማቱም ትርጉም ይኖረዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ቅድሚያ የሚሰጠውና መስጠትም ያለበት ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደህንነት ነው ያሉት ኢንጂነር ጌድዮን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በህገ መንግሥቱም እንደተደነገገው በህይወት የመኖር መብት አለው። የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ህይወት በአስተማማኝ ሁኔታ መጠበቅ ካልቻልን ሌላ ትልቅ ነገር ለመሥራት በጣም እንቸገራለን ብለዋል።

እኔ በግሌ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገር ውስጥ ያለው አለመረጋጋት ለሁላችንም እንደስጋት የምንቆጥር በመሆኑ ሁላችንም ተባብረን ማቆም አለብን ያሉት ኢንጂነር ጌድዮን፣ በማንኛውም መልክ የውጭ ኃይልን ለመቋቋም የሚቻለው የውስጥ ጥንካሬና አንድነት ሲኖር እንደሆነ አመልክተዋል።

የውስጥ ጥንካሬና አንድነት በሌለበት ሁኔታ በተለያየ መልክ ኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ ተቃውሞዎችን ለመቋቋም በጣም አስቸጋሪ ነው። ኢትዮጵያ እንደህዳሴ ግድብ ያሉ እና ሌሎችንም ትልልቅ ፕሮጀክቶች በምትሠራበት ወቅት የውስጥ ትብብሩ ወሳኝ እንደሆነ አስታውቀዋል።

ኢንጂነር ጌድዮን እንዳሉትም፤ በህዳሴ ግድቡ ሥራ የታየውን ቁርጠኝነት በሌሎች ተፋሰሶችም ለማስፋፋት እንዲሁም ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ምልክት የሚሆነን ጥንካሬያችን ነው። ሌሎቹን ፕሮጀክቶች ለመሥራት አሁንም የውስጥ ጥንካሬ ያስፈልገናል። በውስጣችን አለመረጋጋት መኖሩ በጣም የሚያሳስብ ጉዳይ ሆኗል። ኢፕድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//ugroocuw.net/4/4057774