‹‹በገዥው ልሂቅ ሥርዓተ አልበኝነት ተፈጥሮ እንደ አገዛዝ ሥልት መጠቀም አዲስ ክስተት ነው›› የሺጥላ ወንድሜነህ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት ጥናት ማዕከል የጂኦ ፖለቲካና የሥልጣን መዋቅርና ተዋረድ ተመራማሪ

ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በበርካታ ችግሮች ውስጥ አልፋለች፡፡ ከእነዚህ ችግሮች እንድትወጣ መንገድ በመቀየስና መስመር በማሳየት የሚጠቀሱና ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ልሂቃን ደግሞ የታሪክ አካል ሆነው ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ልሂቃን የመፍትሔ ምንጮች ብቻ ሳይሆኑ የችግር ምንጮችም ሲሆኑ ማየት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ የዓለም አገሮችም የሚስተዋል ነው፡፡ ልሂቃንን የችግር ምንጭ ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ የልሂቃኑ የብቃት ማነስ ቀዳሚ ችግር ሆኖ በኢትዮጵያ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከራሳቸው ሐሳብ ውጪ የሌላውን ማዳመጥ አለመፈለግና ለማቻቻል ያላቸው ፍላጎት ውሱንነት አንዱ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ልሂቃን ችግር ፈጣሪዎችና አባባሾች ናቸው ይባላሉ፡፡

ነገር ግን መፍትሔውም ከእነዚህ ልሂቃን ውጪ አይደለም፡፡ ልሂቃን ያሏቸውን ፍላጎቶችና እንወክለዋለን የሚሉትን ማኅበረሰብ ፍላጎት እርስ በርሳቸው ለማጣጣም፣ እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ለውይይትና ለድርድር መቀመጥ አለባቸው የሚል ምክረ ሐሳብ የሚለግሱ አሉ፡፡ ሆኖም ይኼ ዕሳቤ በራሱ ማንን በምን መሥፈርት ለውይይትና ለድርድር ማስቀመጥ ይቻላል? ልሂቃኑስ ያሉባቸው ውሱንነቶች ምንድናቸው? ወዘተ. የሚሉ ጉዳዮች አገራዊ ችግሮችን ተረድቶ መፍትሔ ለማምጣት መንገዱን አዳጋች ያደርጉታል፡፡ በዚህ ረገድ የልሂቃንን ሚና በኢትዮጵያ ፖለቲካ እያጠኑ የሚገኙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገር ልማት ጥናት ማዕከል የጂኦ ፖለቲካና የሥልጣን መዋቅርና ተዋረድ ተመራማሪው የሺጥላ ወንድሜነህ (ዶ/ር) የልሂቃን ማንነት ብየና፣ የልሂቃን ሚና፣ ልሂቃን በማኅበረሰቡ ከየትና እንዴት መፍለቅ እንደሚገባቸው፣ እንዲሁም ልሂቃን ለአገራዊ መፍትሔ በምን ላይ ትኩረት አድርገው ለውይይትና ድርድር መቀመጥ እንደሚኖርባቸው ከብሩክ አብዱ ጋር የሚከተለውን ቆይታ አድርገዋል፡፡

የሺጥላ (ዶ/ር) ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመምጣታቸው አስቀድሞ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖሊሲና ልማት ጥናት የአመራርና ፖሊሲ ክላስተር አስተባባሪና መምህር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን አሳትመዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በበርካታ አገራዊ፣ ቀጣናዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ የሕዝብን ፍላጎት እንወክላለን የሚሉ የተለያዩ አካላት ልሂቃን በሚል መገለጫ ይጠራሉ፡፡ አንዳንዴም በእነዚህ መድረኮች የሚታዩ ችግሮች ምንጮች ልሂቃን ናቸውም ይባላልና እነዚህን ልሂቃን በመበየን እንጀምር፡፡ ልሂቃን የሚባሉት እነማን ናቸው? መገለጫቸውስ ምንድነው?

የሺጥላ ወንድሜነህ (ዶ/ር)፡- በእርግጥ በከፍተኛ ትምህርት ውይይቶች ውስጥ ልሂቃን የሚባሉት በኅብረተሰብ ውስጥ የተለየ ችሎታ ያላቸው፣ በማኅበረሰቡ ዕውቅና አግኝተው ማኅበረሰቡ እንዲመራቸው ዕውቅና የሚሰጣቸው፣ በቁጥር ትንሽ የሆኑ ግን በተፅዕኖ ከፍ ያለ ሚና በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚጫወቱ የኅብረተሰብ ክፍል ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ በትምህርት የላቀ የተለየ ችሎታ ያላቸው ሆነው ወደዚህ ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በተለያዩ ዘርፎች በሚያስመዘግቧቸው ውጤቶች፣ በሚያገኙት ተቀባይነት ልሂቃን ሊባሉ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ልሂቃን ግን በቁጥር እጅግ ጥቂት ናቸው፡፡ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ግን በጣም ትልቅ ነው፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚይዙት ማኅበራዊ ሥፍራ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ኃይል ያላቸው አካላት ናቸው፡፡ እያወራን ያለነው ፖለቲካዊ ሥልጣን በመያዝ ስለሚመሩ ልሂቃን ነው፡፡ ብዙ ዓይነት ልሂቃን አሉ፡፡ የትምህርት፣ የቢዝነስ፣ የፖለቲካ፣ የባህላዊና ሌሎች ዓይነት ልሂቃን ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

ይኼንን መለኪያ ወደ ኢትዮጵያ ስናመጣው የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ይኼ ነው የሚባልና በምዕራቡ ዓለም የምናውቃቸው ልሂቃን በኢትዮጵያ ውስጥ አልተፈጠሩም ይላሉ፡፡ የላቀ ችሎታ ይዘው በማኅበረሰቡ ውስጥ ደግሞ ያንን ችሎታ አንፀርቀው የተለየ ተፅዕኖ ለመፍጠር ወደሚያስችል ደረጃ የደረሱና የማኅበረሰቡን ፍላጎቶች በተለያየ መንገድ የሚያቀርቡ፣ ማኅበረሰቡን በመምራትም በማደራጀትም ሚና የሚጫወቱ አልተፈጠሩም የሚሉ አሉ፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ ሌሎቹ ልሂቃን የማኅበረሰቡ ነፀብራቅ ናቸውና ልሂቃን አሉ ይላሉ፡፡ ስለዚህም በኢትዮጵያ ያለው የልሂቃን መዋቅር በተለያዩ ሥርዓቶች የተለያዩ ዓይነት ልሂቃኖችን የያዘ ነበር ይላሉ፡፡ በንጉሡ ጊዜ በዋናነት የፊውዳሉን ማኅበረሰብ የሚወክሉና ከዚያ ማኅበረሰብ የወጡ መሳፍንት የሚባሉ ልሂቃን ናቸው የነበሩት፡፡

ከዚያ በተጨማሪ ከተራው የገበሬ ልጆች የተገኙና መኳንንት የተባሉና በትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ ልሂቃን ተፈጥረው ነበር ይላሉ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የነበረው ሥርዓት ችሎታን መሠረት ያደረገ ስለሆነ እንቅስቃሴን ይፈቅዳል፡፡ አንድ ሰው ከየትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል ይወለድ በትምህርትም ሆነ በተለያዩ መንገዶች ውጤት የሚያገኝ ከሆነ የሚታደግበት ነው፡፡ ያንን የሚመለከቱ ከምዕራቡ ዓለም ጋር የሚመሳሰሉ የልሂቃን መዋቅር ነበር የሚሉ አሉ፡፡ ወደ ደርግ ሥርዓት ስንመጣ ደግሞ በነበረው የልሂቃን መዋቅር አብዛኞቹ ወታደሮች ናቸው፡፡ ከወታደሮቹ በተጨማሪ ደግሞ የተማረውን ክፍል የሚወክሉና የመንግሥትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የተቆጣጠሩ ልሂቃን ነበሩ፡፡ ይኼ በዋናነት በችሎታ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የአገሪቱን የልሂቃን መዋቅር ስንመለከት ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ፣ የተለያዩ ብሔረሰቦችን የሚወክሉ የብሔር ልሂቃን (Ethno-elites) ናቸው ያሉት፡፡

እነዚህ ልሂቃን ከሌሎች ልሂቃን ይለያሉ፡፡ አብዛኞቹ ቀደምት ልሂቃን ለምሳሌ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ መኳንንት የሚባሉትና ከመደበኛው ማኅበረሰብ ወጥተው ባላቸው ችሎታና በስኬታቸው ምክንያት ነው ወደ ከፍተኛ ደረጃ የሚያድጉት፡፡ በደርግ ጊዜ ስናይ ደግሞ ጥቂት ከሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው የቢሮክራቲክ መዋቅሩን የሚመሩና የመንግሥትን አስተዳደራዊ ሥራ የሚይዙ፣ በችሎታቸው ብቻ የተመሠረቱ ልሂቃን ነበሩ፡፡ የአሁኑ የሚለየው እንደዚያ ዓይነት ጥራት ያላቸው ልሂቃን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መጥተዋል፡፡ አሁን ከብሔር ብሔረሰቦች የተወከሉ የብሔር ልሂቃን ናቸው ያሉት፡፡ እነዚህ ልሂቃን ደግሞ የመጡበት ብሔረሰብ ተወካይ ነን ብለው ነው የሚያስቡት፡፡ የሚገርመው ነገር ግን እነዚህ ልሂቃን እንዲህ ያለውን ውክልና በራሳቸው ጊዜ ራሳቸው ናቸው እንጂ የሚወስዱት፣ ማኅበረሰቡ እንዲህ ያለ ውክልና አልሰጣቸውም፡፡

ማኅበረሰቡን ወክለው እንዲደራደሩ፣ በማኅበረሰቡ ስም ውሳኔ እንዲወስኑ፣ በፖለቲካ አደረጃጀትና በተለያዩ መንገዶች እንዲሳተፉ ውክልና አልሰጣቸውም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ተነስተው የብሔረሰባቸውን ስም እየጠሩ ተወካዮች ነን ይላሉ፡፡ በዚህም የብሔረሰባቸው ጉዳይ በጣም እንደሚያስጨንቃቸው፣ የብሔረሰቦቻቸውን ጉዳዮች ለማስፈጸም እጅግ እንደሚተጉ አድርገው ነው የሚያቀርቡት፡፡ ቅድም እንዳነሳሁት በችሎታና በብቃት ልሂቃንን አጉልቶ በሚያወጣው መለኪያ ስናያቸው ግን፣ አሁን ያሉት ልሂቃን ደረጃቸው እጅግ የቀነሰ ነው፡፡ ይኼ ሁሉንም አይወክልም፣ ግን አብዛኞቹ ግን እንደዚያ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ ልሂቃን የሚባሉ በቁጥር አነስተኛ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለምንድነው ተለይተው ትኩረት የሚሰጣቸው? እነዚህ ልሂቃንስ እንዴት ነው የሚፈጠሩት?

የሺጥላ ወንድሜነህ (ዶ/ር)፡- መፍለቂያቸውን ስናይ፣ በሌላው ዓለም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ነው የሚመጡት፡፡ የልሂቃን መፍለቂያ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካም በተለያዩ አገሮች ያለውን ልምድ ስናይ ልሂቃኑ የሚወጡባቸው የቢዝነስ፣ የፖለቲካና የቴክኖሎጂም ሊሆኑ ይችላል ከተለያዩ የተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ነው የሚወጡት፡፡ መፍለቂያቸው የትምህርት ተቋማት ናቸው፡፡ በፈረንሣይ የግራንዴ ኤኮል (ኢኤንኤ፣ ኢፒ፣ ኤችኢሲና ኢኤንኤስ)፣ በእንግሊዝ ኤቶንና ኦክስፎርድ ኬ (ኦክስፎርድና ካምብሪጅ)፣ በአሜሪካ ግሮትልሴክስና የአይቪ ሊግ የኒቨርሲቲዎች (ሐርቫርድ፣ ዬልና ፕሪንስተን)፣ በጃፓን ቶዳይ (የመንግሥት ከሆኑት መካከል የቶኪዮ ዩኒቨርሲቲ፣ ክዮዳይ ዩኒቨርሲቲ፣ ሒቶትሱባሺ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም የግል ኬዮና ዋሰዳ ዩኒቨርሲቲ) እንዲህ ካሉ የልሂቃን ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ይመደባሉ፡፡

የአንድን አገር የልሂቃን ጥራትና ፀባይ ለማወቅ የዚያን አገር የትምህርት ተቋማት አደረጃጀትና ብቃት ማየት ያስፈልጋል ይባላል፡፡ ምክንያቱም የልሂቃኑ መፍለቂያ በብዛት እነዚህ የትምህርት ተቋማት ስለሆኑ ማለት ነው፡፡ ልሂቃኑ የተለየ ችሎታና ክህሎት እንዳላቸው ማስመስከር አለባቸው፡፡ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ያ ክህሎት ነው ወደ ከፍተኛው ቦታ የሚወስዳቸው፡፡ የኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ እንደሚያሳየው ብዙዎቹ ልሂቃን መፍለቂያ ምንጫቸው ብሔረሰቦቻቸው ናቸው፡፡ የትምህርት ተቋማት አይደሉም፡፡ አንዳዶቹ ከትምህርት ተቋማትም ወጥተው፣ ብሔረሰቦችን ወክለው እንዲህ እናደርጋለን ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ግን በብዛት አሁን ላይ ባለው ሁኔታ የብሔረሰባቸውን ውክልና ነው የሚያንፀባርቁት፡፡ እነዚህ ልሂቃን ታዲያ ማንም ይሁኑ ከየትም ይምጡ ለምንድነው የተለየ ትኩረት የሚሰጣቸው ካልን፣ በየትም አገር አሁን ባለው ሁኔታ አንድን አገር የሚመሩትና የሚያስተዳድሩት ልሂቃን ናቸው፡፡ ሁሉም ሰው አገር አይመራም፣ ሁሉም ሰው አያንቀሳቅስም፣ ሁሉም ሰው አያስተባብርም፡፡

በየዘርፉ ኢኮኖሚውን፣ ፖለቲካውን፣ ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚመሩ የተለየ ችሎታ ያላቸው መሪዎች አሉ፡፡ እነዚህ መሪዎች ናቸው ልሂቃኑ፡፡ ስለዚህ ስለሚመሩና በማኅበረሰቡ ላይም ውሳኔ ማስተላለፍን ጨምሮ የተለየ ተሳትፎ ስለሚያደርጉ፣ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ያገኛሉ፡፡ ከፍ ያለም ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ነገር ግን ይኼ የሚሆነው በተደራጀና አነሳሽነትና ግልጽ መዋቅር ባለበት አገር ነው፡፡ ምክንያቱም የተደራጁና ቅድም የጠቀስናቸው ዓይነት የትምህርት ተቋማት አሉ፡፡ ከዚያ የሚወጡ፣ በጣም የተለየ ክህሎትና ችሎታ ያላቸው፣ የተለያዩ የአንድን አገር የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካም ሆነ የተለያዩ ዘርፎችን ይዘው በመምራት አገሮቹን ማስቀጠል እንዳለባቸው በማኅበረሰቡ ዘንድ ይታመናል፡፡ ስለዚህም ቀጣይነት አለው፡፡

የተለየ ችሎታ እያሳዩና በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ስኬት እያስመዘገቡ ሲመጡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ተቀባይነት እየጨመረ፣ ቦታ እያስገኘና ተፅዕኖ ፈጣሪነትን እያመጣ ይሄዳል፡፡ በእኛ አገር ግን ብዙዎቹ ልሂቃን እንደዚያ ዓይነት ጥራት የላቸውም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ከማኅበረሰቡ የተለየ ችሎታና ክህሎት የላቸውም፡፡ ግን ጉልህ የሆነ እኛ እንዲህ ነን የሚል የፍላጎት መግለጫ (Bold Claim) አላቸው፡፡ ብሔረሰቦቻቸውን እንደሚወክሉ፣ ለብሔረሰቦቻቸው መብት እንደሚታገሉና እንደሚቆረቆሩ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡

ስለዚህ ያንን በመጠቀም የተወሰነውን በብሔረሰቡ ውስጥ ያለውን ክፍል በማንቀሳቀስ በሌላኛው ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የኅብረሰቡ ተወካይ እንደሆኑ ያሳያሉ፡፡ ራሳቸው ናቸው ለራሳቸው ዕውቅና የሚሰጡት እንጂ፣ እንዲሀ መዋቅራዊና ተቋማዊ የሆነ እነዚህ ልሂቃን የሚወጡበት መዋቅር የለም፡፡ ለዚያም ይመስለኛል ብዙን ጊዜ እኛ አገር ትልልቅ ተቋማትን መምራት የሚችሉ፣ የተለያዩ ዘርፎችን ማንቀሳቀስና አገሪቱ ያላትን አቅም ማውጣት የሚችሉ መሪዎችን ያጣነው፡፡ ሙሉውን ቃለ መጠይቅ ይህንን ሊንክ በመጫን ይመልከቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//naucaish.net/4/4057774