Press "Enter" to skip to content

እንሙላና እናውጋው (እስማኤል አባይ – በአባይ ጉዳይ ጸሀፊ ጋዜጠኛ)

በግድያና ውድመት ውስጥ ሁሌም በዳይ አለ። የዛሬ የበደል ድርጊት ትላንት ላይ አስተሳሰብ ነበር። ቁስ-አካል ሆኖም ይህን አሳይቶናል። ማን ነው ጥፋተኛው? መልሱን ተከታዩ ሐቅ ይቀድመዋል

የካይሮ ምሁራን ቤኒሻንጉል፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ ትግራይ፣ ጋምቤላ፣ ወዘተ እየዘረዘሩ “ኢትዮጵያን ያለ ውጊያ የምናንበረክክበት ካርታችን” አሉ። በካርታ እና በሴራ የተሸረቡ መረጃዎችንም አከታተሉ፤ ይህ የተባለው “ግድቡ ያለ አስገዳጅ ስምምነት የሚሞላ ከሆነ ምስራቅ አፍሪካና ኢትዮጵያ የለዬለት ቀውስ ውስጥ ይሆናሉ” የሚለውን የአል-ሲሲ ቃል ተከትሎ ከሁለት ቀን በኋላ ነበር ሲቀጥልም

ከቀናት በኋላም ከኢትዮጵያ አቋም ጋር በቆመው የሶማሊያ ጦር ሁለት ካምፖች ላይ የአልሼባብ ጥቃቶች ደረሱ በሶማሌ እና አፋር ህዝቦች መካከል በመሳሪያ የተደገፈው ግጭት ተፈጠረ

በመተከልና ወለጋ ንፁሃንን መግደል አገረሸ የካይሮ ልሂቃን “ኢትዮጵያ የአዋሽ ወንዝ ላይ ሶማሊላንድን ውሃ የሚያስጠማ ፕሮጀክት አየገነባች ነውና ተነሱ” ሲሉ መቀስቀስ ያዙ
ጂቡቲ “ከአዋሽ ውሃ የይገባኛል” አይነት ቃል አሰማችን (የካይሮ ሚዲያዎችም ይህንን አስተጋቡት) ከቀናት በኋላ ደግሞ አልሲሲ ከጂቡቲው ፕሬዘዳንት ጋር ስለ ግድቡ አስገዳጅ ስምምነት በስልክ ተነጋገሩ(ከወደ ጂቡቲ አረንጓዴ መብራት ቢያገኙ ኖሮ በሚዲያቸው ያስተጋቡት እንደነበር ይታወቃል)

የታጠቀ ነብሰ በላ በአጣዬ የጭካኔ ወንጀል መፈፀም ጀመረ ታዲያ ጥፋተኛው ማነው? ለምን አላማ? ተደብቆ ከማይቀረው የዚህ ጥያቄ ምላሽ በፊት አንድ ነገር እናስታውስ።

የካይሮ ፀኃፍት በአገራችን ቀውስ እየጨፈሩ ናቸው። “በሚፈሰው የንፁሃን ደም ላይ ግብፅ በሁለተኛው የግድቡ ሙሊት ላይ የማዘግየት ድልን ትጎናፀፋለች” የሚል ዘመቻም ሞካክረዋል።

ችግሩ ከመንግስትም ይሁን ከግለሰቦችና ቡድኖች በዚህ ወሳኝ ጊዜ ልብ ስለሚሰብረው የተበዳዮች ብሶት ጣት መቀሳሰራችን የካይሮን ህልም ቢያሳካ እንጂ የተበዳይ ዜጎችን ፍትህ ለማዋለድ የተመቸ ነገር አይታይበትም።

ከውስጥ ሆኖ ጀርባችንን የሚያስወጋው ወንጀለኛና የተባባሪዎቹ ማንነት፤ የሴራው መንስኤና አላማ ምንም ይሁን ከየት፣ ተገልጦ ቢታይ ከካይሮ ጓዳ የሚወጣ አይሆንም። (ባለፈው አመት ለመጀመሪያው ሙሊት ስንዘጋጅ በመተከል ያገረሸውን ግድያ መርሳት የለብንም) ግድቡ በተሞላ ቁጥር የንፁሃን ደም እና የወገን እምባ ደግሞ አብዝቶ እየፈሰሰ ታዝበናል። ግድቡ ለዜጎች ጥቅም እንጂ ሌላ አላማ አይኖረውም። የሚያሳዝነው ነገር ግድያው ከግድቡ ሙሊት ጋር በሚያሳየው ስንስል ውስጥ ወንጀሉን በይሁንታ የሚመለከት አይምሮ ያለመጥፋቱ መራር ሐቅ አንዱ ሲሆን፤ ለሰናይነቱ ባይታደል እንኳ ስለ ኢትዮጵያ አራምዳለሁ ለሚለው እኩይ አጀንዳ ቢያንስ የኢትዮጵያ ሕላዌ የግድ ስለማስፈለጉ ማስተንተን አለመቻሉ ነው

የሰሞኑ ወንጀል ንፁሃንን ብቻ ሳይሆን አገርንም ለመግደል ያለመ ነው። የግድቡ መጠናቀቅ ብቻ እንጂ አለመገደቡ ለቀጣይ ሰላም በፍፁም ዋስትና ሊሆን አይችልም። “የግድቡ መስተጓጎል ኢትዮጵያን እርስ በርስ ያናክስልናል በሚል የውጭ ጠላት የምኞት ትንተና ሳምንቱን ተደጋግሞ ሲስተጋባ መሰንበቱን መጠቆም እፈልጋለሁ። የሆነ ሆኖ ሐቁ ክረምቱ አልፎ ይወራል። ያኔ አገራችንን አስወግቶ የተገኘ ማንም ይሁን ማን በአደባባይ ይሰቀል።መፍትሔ ቢሆን ኖሮ ለመወንጀል ወደ ኋላ ባላልኩ እንሙላና እናውጋው።

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//zuphaims.com/4/4057774