የዕለቱን ሰልፎች አስመልክቶ የጋዜጠኛው መልዕክት

ሰልፎቹ መደረጋቸው ተገቢም፣ ወቅታዊም ነው። በማንነቱ የተጠቃ፣ ግፍና መከራ እየተደራረበ የተፈጸመበት ህዝብ ቁጣውን በአደባባይ መግለጹ የዘገየ እርምጃ ነው። እንደውም ጉዳዩ የአማራ ተወላጆች ብቻ መሆኑ ቀርቶ በአዳማ፣ በሀዋሳ፣ በጅግጂጋ፣ በሌሎችም ከተሞች “በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ስቃይ ይቁም” የሚል መልዕክት ያለው ትዕይንተ ህዝብ መደረግ ነበረበት የሚል እምነት አለኝ። በአንዱ ኢትዮጵያዊ ላይ የሚደርስ ጉዳት ለሌላውም ጉዳት ነውና። አፍንጫ ሲመታ አይን ካላለቀሰ ምኑን የአንድ ሀገር ልጆች ሆንን?

መንግስት የህዝብን ድምጽ መስማት አለበት። ህዝብ ጠይቋል። ተቆጥቷል። መንግስት የህዝብ አገልጋይ ከሆነ ይኸው ህዝብ ተናግሯልና መልስ ሊሰጠው ግድ ይላል። ከዚያ ባለፈ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።

በዛሬው ዕለት በአንዳንድ ከተሞች የተስተጋቡት መልዕክቶች ከሰልፉ ዓላማ ባፈነገጠ መልኩ መሆናቸውን ተስተውሏል። ህዝብን እንደ ሀገር ወደማይጠቅሙ ስሜቶች መገፋፋት ድምሩ ዜሮ ወደሆነ፣ ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት ውጤት የሚያደርሰን ነው። ውጭ ተቀምጠው፣ እዚያው ሀገር ውስጥም ሆነው፣ አንድን ህዝብ በጅምላ በማብጠልጠልና በማውገዝ የፖለቲካ ቁማር የሚጫወቱ የደም ነጋዴዎች የዛሬውን ሰልፍ ለመጥለፍ መሞከራቸውን በትዝብት ተመልክተናል። ይህ መሆኑ የሰልፉን ሞራላዊ የበላይነት የሚያደበዝዝ ነው። የህዝቡን ህጋዊ ጥያቄ የሚያኮስስ ነው።

ይህ ለማንም የሚበጅ አይደለም። ድብቅ አጀንዳቸውንና የሴራ ፖለቲካቸውን መሬት ለማውረድ የዛሬውን ቀን አድፍጠው ሲጠብቁ የነበሩ ሃይሎች የሚችሉትን አድርገዋል። አንዳንድ የሚሰሙ ድምጾችና የሚታዩ መፈክሮች የእነዚህ ቀውስ ጠማቂዎች ስለመሆናቸው ታዝበናል። ከህዝብ ህጋዊና ትክክለኛ ጥያቄ ጋር ተለውሶ የተስተጋባውን ድምጽ ስንዴውን ከእንክርዳዱ፣ ምርቱን ከገለባው መለየት ለሚችል ብዙም አይደንቀውም። ግን ጥሩ አይደለም። ለበለጠ ቀውስና ተያይዞ ለመጠፋፋት ካልሆነ በቀር ለየትኛውም ወገን የሚጠቅም አይደለም። በሰው ሞት ፖለቲካ ለሚቆምሩ ምንም ላይመስላቸው ይችላል። ከውቅያኖስ ማዶ ሆነው እሳት በማራገብ እንጀራቸውን ለሚጋግሩትም ገበያው ደራላቸው እንጂ ከዚያ ያለፈ ጉዳያቸውም አይደለም። ህዝብ ግን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።

የዛሬውን የሮይተርስን ዘገባ ለተመለከተ አሁንም ዓይናችንን ለአፍታም መንቀል የሌለብን ነገሮች እንዳሉ ይገባናል። እንደሮይተርስ ለመሳሰሉ የኢትዮጵያን ሞት አብሳሪ ጸረ ኢትዮጵያ ሚዲያዎችና ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች የስሞኑ ክስተትና የእኛ ውስጣዊ መበላላት ሰርግና ምላሽ ሆኖላቸው ስንመለከት በእርግጥም ዓይኖቻችም መንቀል በሌለባቸው ጉዳዮች ላይ የበለጠ ትኩረት እንድናደርግ የሚያስገድደን ነው። የሁለቱ የኢትዮጵያ ልጆችን፣ ኦሮሞውንና አማራውን፣ በማባላት ኢትዮጵያን በቀላሉ ማፈራረስ ይቻላል የሚለውን የዘመናት ድብቅ አጀንዳቸውን ገሃድ አውጥተው ለማስፈጸም ጊዜው አሁን ነው ብለው ተነስተዋል። እንደሰሞኑ ዓይነት የህዝብ ሰልፎችን ተጠቅመው መርዛቸውን የሚረጩትን ከማንም በላይ ሰልፉን የታደሙ የአማራ ተወላጆች ሊያወግዙት ይገባል።

ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደሚባለው ይህቺን አጋጣሚ የእኩይ ዓለማቸው ማስፈጸሚያ፡ ኢትዮጵያን ማዳከሚያ ለማድረግ የሚሯሯጡ እንዳሉ ተረድተናል። ከወደካይሮ እንጉርጉሮው ለጉድ ነው። ካርቱምም በአቅሟ አንገቷን ቀና ለማድረግ ስትዳክር ተመልክተናል። የህወሀት ትርፍራፊ ሃይል ዓይኑን ለመግለጥ ከመቃብር ማዶ ሲፍጨርጨር እንደነበር ተረድተናል። በተለይ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ በወዲህና ወዲያ የተፋጠጡ አመራሮች ትከሻ መለካካታቸውን በእጥፍ የጨመሩበት አቅም ፈጥሮላቸዋል። በየፊናቸው የጦስ ዶሮ ፍለጋ እየኳተኑ ነው። አንደኛው ሌላኛውን ይከሳል። ይወነጅላል። ራሱን ቅዱስ ሌላውን እርኩስ በማድረግ ይመጻደቃል፡ ይራገማል። ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ሆነና ሰላማዊው ህዝብ በመሀል መከራውን በላ።

ሁሉም የየራሱን ጀግና ሊወልድ እያማጠ ነው። አብዮት መሪ መፍጠሯ አይቀርምና በዘርና በጎሳ በየአጥሩ የተሰለፈውና አብዮት ለማፈንዳት የሚሯሯጠው ብሄርተኛ የየራሱን ጀግና ሊገላገል አቆብቁቧል። የትግራዩ ብሄርተኛ ደብረጺዮን መሪው ሆኖ እንዲመጣ ከመቃብር ወዲህ ተንበርክኮ እየጸለየ፡ በባህርማዶ ደግሞ ከተሞችን በጩኸት እያደመቀ ይገኛል። የኦሮሞው ብሄርተኛም ከእስር ቤት አልያም ከወለጋ ጫካ ጀግና ሊሰይም አሰፍስፏል። አማራውም እንደዚያው። ይህ መሆኑ ለኢትዮጵያ በጎ ምልክት አይደለም። የኢትዮጵያ ጀግና ከወዴት ይወለድ ይሆን?

አሁንም እንጠይቃለን። አሁንም መንግስትን ስማን እንላለን። ግድያ ይቁም። ስርዓት አልበኝነቱ ሉጋም ይበጅለት። ጂኒዎች ወደ ጠርሙሳቸው እንዲገቡ ይደረግ። የጽንፈኞች ጥፍሮች ይቆረጡ ዘንድ መንግስት ቁርጠኛ ይሁን። መንግስት ባለችው አቅም ስርዓት እንዲያስከብር እንፈልጋለን። ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን የመከራ ምድር መሆኗ እንዲያበቃ በጽኑ እንፈልጋለን። ከማንም በተሻለ፡ አቅም ያለው መንግስት ነውና ኢትዮጵያ በከንቱ የልጆቿ ደም የሚፈስባት እንዳትሆን ከልቡ እንዲሰራ በኢትዮጵያ ስም አብዝተን እንጠይቃለን። (ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//dooloust.net/4/4057774