ክቶክ ‘እንጀራ’ የሆነላቸው ኢትዮጵያውያን ወጣቶች

ቲክቶክ ላይ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው ሃያት ናስር እና የትናየት ታዬ አዝናኝና ‘ቀለል’ ያሉ ጉዳዮች ላይ ያተኩራሉ። የትናየት ዘንድሮ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኮንስትራክሽን ማኔጅምንት ተመርቃ በኢንቴሪየር ዲዛየን መማር ጀምራለች።

ሃያት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኮምፒውተር ሳይንስ የ3ኛ ዓመት ተማሪ ነች። ዳንሶች፣ ከተለያዩ ቪዲዮዎች የተወሰዱ ድምጾችን በከንፈር እንቅስቃሴና በትወና መልክ መስራት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሰዎች ሊያሳዩ የሚችሉትን ስሜት ማንጸባረቅና መሰል ጉዳዮች በብዛት የሰሯቸው ቪዲዮዎች ይዘቶች ናቸው።

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይርስ መከሰት በስፋት ካስተዋወቃቸው ጉዳዮች አንዱ ቲክቶክ ሳይሆን አይቀርም። የትናየትም በዚህ ሃሰብ ትስማማለች። የትናየት የኮሮናቫይርስ በኢትዮጵያ ከመከሰቱ በፊት የነበሯት ተከታዮቿ 2 ሺህ አካባቢ እንደነበር ትገልጸለች።

ከቫይረሱ መከሰት በኋላ ግን የተከታዮ ቁጥር 200 ሺህን ተሻግሯል። ሀያት ደግሞ ከቫይረሱ መከሰት 1 ወር በፊት ቲክቶክን ተቀላቅላ ከዛ በኋላ ባሉት ጊዜያት ከ306 ሺህ በላይ ተካታዮችን አፍርታለች።

የኮሙኒኬሽን ባለሙያው አቶ ነጻነት ተስፋዬ በቫይረሱ ምክንያት ብዙዎች ቤት ለመዋል መገደዳቸውና ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች ክንውኖች በኢንተርኔት አማካኝነት እንዲሰጥ መደረጉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከፍ እንዳደረገው ይናገራሉ።

ይህም ቲክቶክን ጨምሮ የማህበራዊ ትስስር መተግበሪያዎች በኢትዮጵያ ያሏቸውን ተጠቃሚዎች እንዳሰደገም ገልጸዋል። ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱና መደበኛ እንቅስቃሴዎች ወደነበሩበት ሲመለሱ የተመልካቾች ቁጥር እየቀነሰ እንደመጣ ገለጻለች። በተቀረው ዓለምም ኮሮና ለቲክቶክ ‘ሲሳይ’ ይዞ የመጣ ይመስላል።

ሃያትም ሆነ የትናየት ቲክቶክ ያላቸውን ተሰጥኦ ለማውጣት ምቹ መድረክ እንደሆነላቸው ተናግረዋል። “ያለኝን አቅም እንዳውቅና ከብዙ ሰው ጋር እንድተዋወቅ ያደረገኝ ቲክቶክ ነው’ የምትለው የትናየት የስራ ዕድሎችም እንደፈጠረላት ገልጻለች።

የተለያዩ ድርጅቶች ያላቸውን ምርትና አገልግሎቶችን እያስተዋወቀች ትገኛለች። “በተለይ ወጣቱ ማግኘት ከሚፈልጉት ድርጅቶች ጋር እየሰራሁ ነው። የማገኘው ገቢ ትልቅ ነው ባልልም ራሴን እንድችል አድርጎኛል” ስትል ታሰረዳለች።

ሀያት በተመሳሳይ የተለያዩ ድርጅቶችን ምርት ከማስተዋወቅ አልፎ አንድ ፊልም ላይ በትወና እንድትሳተፍ ቲክቶክ በር ከፍቷል። በሌላ ፊልም ላይም እንድትተውንና የቲቪ ማስታወቂያ እንድትሰራ ግብዣ ቀርቦላታል። ይህም የፊልሙን ዓለም ለመቀላቀል ከልጅነቷ ጀምሮ የነበራትን ምኞት አሳክቷል። “እኔ ሂጃብ አደርጋለሁ። እሱን [ሂጃብ] አድርጌ ፊልም እሰራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም። ቲክቶክ ስለመጣ እንጂ ማን አይቶ ያሰራኝ ነበር” ብላለች ሃያት።

ከዚህም ሲዘል የቲክቶክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን የሌላውን ዓለም እንዲያዩ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን ባህል፣ አለባበስ፥ መልክዓ ምድርና መሰል ጉዳዮች እንዲያስተዋወቁ በር ከፍቷል ደግሞ የሚሉት የኮሚኒኬሽን ባለሙያው አቶ ነጻነት ናቸው። የኮሚኒኬሽን ባለሙያው አቶ ነጻነት ቲክቶክ ያለው ይዘትና ለአጠቃቀም ምቹ መሆኑ በወጣቶች የሚወደድ እንዲሆን አድርጎታል ይላሉ። ተመሳሳይ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች በዚህ መስመር ተገናኝተው መረጃ እንዲለዋወጡ እንድል እንደሰጠም ጠቁመዋል።

የትናየት በቲክቶክ መተገበሪያዋ በኩል ባገኘችው መረጃ ከአጠቃላይ ተከታዮቿ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከ18-24 ዕድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው። ‘ቀለል’ ያሉ ይዘቶችን በብዛት ማስተናገዱ በወጣቶች የሚመረጥ ሳያደርገው እንዳልቀረ የኮሙኑኬሽን ባለሙያውም ይሁን የቲክቶክ ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል። “ፌስቡክ ላይ ፖለቲካ ነው። ቲቪ ላይ ፖለቲካ ነው። እዚህ ላይ [ቲክቶክ] ላይ ግን መዝናኛ ነው። ለዛ ይመስለኛል ወጣቱ በደንብ የሚከታተለን” ስትል ገልጻለች ሃያት። የ3ኛ ዓመት የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪዋ ሃያት በቲክቶክ ምክንያት ያገኘችውን ፊልም የመሥራት ዕድል አጠናክራ መቀጠል ትፈልጋለች- በተለይ በድርሰት።

‘በቲክቶክ ብቻ መገደብ አልፈልግም። በጣም አሪፍ ፊልም ሰርቼ መሸለም ነው የምፈለገው ብላለች። የትናየት ከምርቃት በኃላ የጀመርችውን ትምህርት አጠናቃ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የመሰማራት ዕቅድ አላት። የቲክቶክ ተሳትፎዋንም መቀጠል እንዲሁ። “ይህን ያህል ተከታይ ማግኘት ቀላል ዕድል አይደለም” የምትለው የትናየት ይህንን ዕድል ባለማባክን ለወጣቶች መልካም ተምሳሌት ለመሆን እንደምትሰራ ገልጻለች።

ወጣቶች ያላቸውን አቅም ለማሳየት ቲክቶክ ሁነኛ መድረክ ነው የሚሉት ድግሞ አቶ ነጻነት ናቸው። እናም ወደፊት ስራ ሊያገኙበት የሚችሉባቸውን ቪዲዮዎች ፈጠራ በተሞላበት መንገድ እንዲያቀርቡ መክረዋል።

በመዝናኛ፣ በፋሽን፣ በዕደ ጥበብ፣ በጉብኝትና ጉዞ ዘርፎች ላይ መሰማራት የሚፈለጉ ወጣቶች ቲክቶክ ላይ ስራዎቻቸውን ቢያቀርቡ ወደ ገበያው ለመቀላቀል መልካም ዕድል ሊሆን ይችላል ብለዋል የኮሚኒኬሽን ባለሙያው። ምንጭ ቢቢሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *