Press "Enter" to skip to content

እኔ ብዙም እንደ አገር የሚያሳስበኝ ነገር የለም አለመሥራታችን ነው የሚያሳስበኝ – ዳንኤል ክብረት

ወደ ፖለቲካ ሕይወት እየገባ እንዳለ ሰው እንደ አገር የሚያሳስብህ ነገር ምንድነው? ዲያቆን ዳንኤል፡- እውነት ለመናገር እኔ ብዙም እንደ አገር የሚያሳስበኝ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን አለመሥራታችን ነው የሚያሳስበኝ፡፡ ማለትም ያለንን ዕድል ተጠቅመን ለሥራ አለመሠለፋችን ግን ያሳዝነኛል፡፡ ብዙ ልንሠራው የምንችለው ጉዳይ እያለ፣ ብዙ ሀብትም እያለን፣ ብዙ ዕድልም እያለን ጊዜው በወሬና በሽኩቻ ማለቁ፣ ምንም በማይጠቅሙ ጉዳዮች ማለቁ ያሳስበኛል፡፡ አንድ ሰው ለሽሮ፣ ለበርበሬ፣ ለእንጀራ የሚያወጣውን ጊዜ ለፈንዲሻ አያወጣም፡፡ የትኛውም ቤት ብትገባ ፈንዲሻውን ይተወዋል እንጂ ሽሮውን አይተውም፡፡ እኛ ግን ሽሮውን ትተን ፈንዲሻው ላይ ነው ያለነው፡፡ ፈንዲሻ ምን ያደርጋል? በዚህ ሰዓት ቢቀርስ? በእርግጥ ደስ ይላል፡፡ ፍንድትድት ብሎ ቤቱን በሙሉ ነጭ በነጭ ሲያደርገውና ኩርሽም፣ ኩርሽም ስታደርግ ደስ ይላል፡፡ ግን ምን ይሆናል? ፈንዲሻ ብቻውን ወጥ አይሆን፣ እንጀራ አይሆን፣ ግን ሊያስደስት ይችላል፡፡ ከዚያ ያለፈ ነገር ምንም ሊያመጣ አይችልም፡፡ ፈንዲሻ ከበላህ በኋላ ሽሮ ትፈልጋለህ፣ እንጀራ ትፈልጋለህ፡፡ ስለዚህ እኛ መቅደም የነበረበትን ባለማወቅ የፈንዲሻ ፖለቲካ እየተጫወትን ሰነፍ አገር ልናደርጋት ነው፡፡ እናም አያሠጋኝም፣ ነገር ግን ያሳስበኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ አላባራ ያለው ግድያ፣ ግጭትና መፈናቀል በምን ምክንያት የመጣ ነው? በተለይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ይህ ችግር ምን ያሳያል?
ዲያቆን ዳንኤል፡- ያው ሊነጋ ሲል ይጨልማል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት እኮ የአገሪቱ ብሎን ሲላላ ነበር የቆየው፡፡ አሁን ትንሽ በሄድክ ቁጥር አንድ ብሎን ይወድቃል፣ እልፍ ባልክ ቁጥር ሌላው ብሎን እየወለቀ ነው፣ ግን እንደላላ እንኳን አታውቅም፡፡ አሁን እኮ የተያዘው ማጥበቅ ነው፡፡ እናም አሁን ያለው ችግር ብሎን በሚያላሉና በሚያጠብቁ ሰዎች መካከል ያለ ግብግብ ነው፡፡ ሁሉንም ብሎን ደግሞ አታገኘውም፡፡ ተቆጥሮ በሰነድ የተቀመጠ ነገር ስሌለ ነው አሁን የቸገረን፡፡ እያለፈ ሲሄድ ግን ለዚህ ማገዶ የሚሆነው እንጨት እያለቀ፣ በፊት የገባው እንጨት እየነደደ ሲሄድና እሱ እንጨት ሲያልቅ ተጨማሪ እንጨት ስለማይመጣ እንደ አዲስ አጥብቀን እናቆመዋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የአንተ ወደ ፖለቲካ መግባት ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ጋር ምን ዓይነት ቁርኝት ይኖረዋል? ዲያቆን ዳንኤል፡- እኔ የገባሁት ለኢትዮጵያ ስል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ስትጠቀም ኦርቶዶክስ ይጠቀማል፡፡ ኢትዮጵያ ስትጠቀም እስልምና ይጠቀማል፣ ፕሮቴስታንት ይጠቀማል፡፡ ኢትዮጵያ ካልተጠቀመች ማናችንም አንጠቀምም፡፡ አንድ መርከብ ላይ እየሄድን መርከቡ ላይ ባለው ጉዞ ሳሎን፣ መኝታ ቤት ወይም በረንዳ የምትለው መጀመርያ መርከቡ ሲንቀሳቀስ ነው፡፡ መርከቡ እየሰመጠ ሳሎኑም፣ አልጋውም፣ በረንዳውም፣ ምንም ዓይነት ደረጃ ላይ ብትሆን ከመስመጥ አትድንም፡፡ ይህ የፖለቲካ ነፃነት ለብዙ የሃይማኖት ሰዎች ትልቁ ነፃነት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር ትልቁ ምክንያት ምንድነው ትላለህ? ዲያቆን ዳንኤል፡- የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አወቃቀሯ ነው፡፡ ከዚህ የመነጩ ችግሮች ናቸው ብዙዎች የምታያቸው፡፡ የተዋቀርንበት ነገር ከኢትዮጵያ ጋር አልሄድ አለና አላርጂ ሆነባት፡፡ ችግሮቻችን የፈታን መስሎን ከኢትዮጵያ ጋር የማይሄድ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ አወቃቀር ይዘን መጣን። መጀመርያ ያጠገበን መሰለን አሁን ግን እያሳከከን መጣ፣ ምክንያቱም አልቻልንም።

ሪፖርተር:- ከአገሪቱ አጠቃላይ ችግሮች በመነሳት ከመንግሥት ዕርምጃና ከማኅበራዊ የትስስር ገጾች ሁኔታ አኳያ ምን ይታይሃል? ዲያቆን ዳንኤል፡- በዚህ ከቀጠልን ለሰከንድ አንድ ሰው የአዕምሮው ጤናው ሲናጋ መጨረሻው የሥነ አዕምሮ ሆስፒታል ውስጥ እንደሚሆን ሁሉ፣ የእኛም መጨረሻ እንደዚያ ይሆናል። ማለትም አገራዊ የሥነ አዕምሮ ሆስፒታል እንደርሳለን በመጨረሻ፡፡ በመሆኑም ለዚህ ቀድመን ማሰብ አለብን፡፡ ነገር ግን እኔ የኢትዮጵያን ሕዝብ አምናለሁ፣ ፖለቲከኞችን አይደለም የማምናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ታግሶ ታግሶ ተው ይላል፣ መጨረሻ ላይ መሠረቱን የሚያናጉበት ከመጡ እንቢ ስለሚል አንድ ቀን ይነሳል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ አሁን እየጎበጠም ቢሆን ልጆቼ ብሎ ተሸክሟቸዋል፡፡ አንድ ቀን የማይሆን ነገር ውስጥ ሲገቡ ግን አሽቀንጥሮ ነው የሚጥላቸው፡፡ ሲጥል ደግሞ አይቼዋለሁ። ዕብደታቸው ወደ አገር ማጥፋት ሲሄድ ሕዝብ ዝም ብሎ አይመለከትም።

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//phaurtuh.net/4/4057774