የግል የህክምና ተቋማት ኮረናን ሰበብ አድርገው በዜጎቻችንን ሰብአዊ ክብርና በሀብታቸው ላይ የሚያደርጉትን ዘረፋ አስቁሙልን – ሙሼ ሰሙ

አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅትና ጥንቃቄ ሳደርግ ብቆይም ከ15 ቀን በፊት በኮሮና ቫይረስ በመጠቃቴ ራሴን ኳራንቲን ማድረግ ነበረብኝ። ዛሬ ላይ ተመርምሬ የኮቪድ ርዝራዠና ቅሪት ከሆኑት ድካምና ራስ ምታት በስተቀር ከቫይረሱ ነጻ ሆኛለሁ።

ከቫይረሱ ነጻ መሆን የሚያስደስት ቢሆንም ቫይረሱ ጥሎት የሚሄደው ጠባሳ፣ የጤና እክልና ስቃይ (Ordeal) ግን ማንም ሰው እንዲፈተንበት የምመኘው ጉዳይ አይደለም። በራስ፣ በቤተሰብ በወዳጅ ዘመድ ላይ የሚያሳድረው መንፈሳዊ፣ ስጋዊና ሞራላዊ ተጽእኖ የትየለሌ ነው።

ከሕክምና ተቋሞቻችን የማስተናገድ አቅም አኳያ እየደረሰንበት ያለው የበሽተኛ ቁጥር፣ የበረዶውን ተራራ ጫፉን ያህል ብቻ ስለሆነ በቫይረሱ የመያዝ እድላችን የዛን ያክል የገዘፈ ሆኗል። ራሳችንን ለዲሲፕሊን በማስገዛት፣ የቫይረሱን አዙሪት በመስበር በበሽታ የሚያዘውን ወገን ቁጥር መቀነስ ካልቻልን በርካታ የእድሜ ባለጸጎቻችንን ጨምሮ አምራች ሃይላችንን አሟጠን እንዳንጨርስ ስጋት አለኝ።

ለዚህም፣ ትራንስፖርት፣ መምህራን፣የሕክምና ተቋም ፣ የሸቀጣ ሸቀጥ፣ ሱፐር ማርኬቶችና ባንኮች ወዘተ የቫይረሱ ከፍተኛ መናሕርያ ሆነዋል። እነዚህ ተቋማት ላይ የሚያገለግሉ ዜጎች ተገቢው ትኩረት ተሰጥቷቸው በተቻለ አቅም ክትባት እንዲያገኙ ቢደረግ ቢያንስ የስርጭቱን አዙሪቱ መስበር ይቻላል። በቀጣይ ሁለተኛም፣ ሦስተኛ ዙር የቫይረሱ ሰለባ ከመሆን በከፊልም ዜጎችን መታደግ ይቻላል።

ያም ተባለ ይህ ግን፣ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ ይቅደም እላለሁ፣ ወገን!!በመጨረሻ ላይ፣ ስም መጥራት ባያስፈልገኝም፣ ስነ ምግባር የተላበሱ ጥቂት ተቋማትና ባለሙያ ቢኖሩም፣ አብዛኛዎቹ የግል ሕክምና ተቋማት እየሰጡ ያለው አገልግሎት እጅግ በጣም የወረደ ከመሆኑም በላይ ታማሚና ሕይወቱን የተነጠቀው ወገን ቤተሰብ ላይ የምትፈጽሙት እጅግ የሚያሸማቅቅ ነውረኛና በጠላት ላይ እንኳን የማይፈጸም የስግብግቦች ድርጊት ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ይህ ወረርሽኝ ነው፣ የሞት ደግሱ የተደገሰው ለሁላችንም ነው። በዚህ ላይ በሽታው በሰበብ አስባቡ የሀገርና የዜጎችን ሀብት እያሟጠጠ የሚገኝ አደገኛ በሽታ ነው። የኮቪድ ሕክምናና ክትትል ሊጠይቀው ከሚችለው ወጭ እጅግ በጣም የናረ ቅድመ ክፍያ በማስያዠያ መልክ በመጠየቅና ታማሚው ካረፈ በኋላ ደግሞ በሰበብ አስባቡ ሀሰተኛ ወጭን በመደማመር የሚጠይቁት ክፍያ የሕክምና ስነ ምግባርንም ሆነ ሰብአዊነትን በማንኛውም መስፈርት የሚጻረር ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው አካላት የግል የሕክምና ተቋማትን ዞር፣ ዞር ብለው በመመልከት በዜጎቻችንን ሰብአዊ ክብርና በሀብታቸው ላይ የሚደረገውን ዘረፋ እንዲታደጉ ጥሪዪን አቀርባለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *