አቶ ማሞ ይንበርብሩ (ማሞ ካቻ) አቶቢሲ ማሞ ካቻ፣ የት ትሄዳለህ? ገብረ ጉራቻ

ታዳጊው ማሞ ይንበርበሩ ገና በጨቅላ እድሜው አባቱ አቶ ይንበርበሩ በሥራ ምክ ንያት ወደ ኢሊባቦር ጎሬ ሲዛወሩ አብሮ ሄደ። ብዙም ሳይቆይ አባቱ የጣልያንን ወራሪ ኃይል ለመከላከል ዘምተው በማይጨው ጦርነት የተሰው ሲሆን እናቱ በህመም ምክንያት ቀደም ብለው ሞተው ስለነበር ገና በ12 ዓመት እድሜው ያለ ወላጅ ቀረ። ወላጅ አልባውን ታዳጊ፤ ለግዜው የኢትዮጵያን ሠራዊት አሸንፈው ከገቡት የጣልያን የጦር መኮንኖች አንዱ አግኝቶት ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ይዞት መጣ።

ታዳጊው ማሞ አንበርብር አዲስ አበባ በመምጣቱ የዕለት ጉርሱን የማግኘት እድሉ ቀለል አለለት። እዛው አካባቢ የሚገኝን ሻይ ቤት ተጠግቶ ብርጭቆ እያጠበና እየተላላከ በክፍያ መልክ ምግቡን እየሰጡት ኑሮውን ጀመረ።

ብልህና ፈጣን ልጅ የነበረው ማሞ አንበርብር በሻይቤቱ ሥራ ብዙም ሳይቆይ፤ በራሱ ሠርቶ ገንዘብ የሚያገኝበትን መንገድ ማሰብ ጀመረ። አስቦም ያገኘው ዘዴ፤ አራት ኩሽኔታ የተገጠመለት መቀመጫ ያለው ተሽከርካሪ ሠርቶ፤ ህጻናትን አሳፍሮ እየጎተተ ከሠይጣን ቤት (ከቴዎድሮስ አደባባይ) እስከ ቴሌኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ድረስ እያንሸራሸረ ገንዘብ ማስከፈል ነበር። ቀስ በቀስ ሳንቲሙ እየተጠራቀመ ሲመጣ አሁንም ሌላ የሕጻናት ማንሸራሸሪያ ተሽከርካሪ አዘጋጀ። ይህ ተሽከርካሪ ሳይክል ሲሆን ፔዳልም ሆነ ካቴና የሌለው አሮጌ ነበር። በሁለቱ ጎማዎች ምትክም ማሞ ራሱ ቆራርጦ የሠራቸው ተሽከርካሪዎች ተገጥመውለት አሁንም እሱን እየጎተተ ሕጻናትን በማንሸራሸር የተሻለ ገንዘብ ማግኘት ጀመረ።

ይህን የማሞን ጥረት ያስተዋለ አንድ የጣልያን ጦር መኮንን ወደ ምፅዋ በሚሄድበት ጊዜ ማሞን ይዞት ሔዶ፤ ከምፅዋ ሃያ የሚሆኑ ትክክለኛ ሳይክሎችን ገዝቶ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ረዳው። አሁን የሃያ ሳይክሎች ባለቤት የሆነው ማሞ ሳይክሎቹን እያከራየ ከበፊቱ የተሻለ ገንዘብ ማጠራቀም ጀመረ።

በዚህ ሁኔታ ገንዘቡ እያደገለት እያለ የጣልያን ጦር በተራው ተሸነፈና እንግሊዞች ተተኩ። ለውጡን ተከትሎ ጣልያኖች ኢትዮጵያን ለቅቀው ሲወጡ መኪኖቻቸውን በችኮላ እየሸጡ ነበርና ወጣቱ ማሞም አንዲት ፎርድ ፒክ አፕ በ108 ብር ገዝቶ ከአዲስ አበባ ወሊሶ እና ወልቂጤ ሕዝብ ማመላለስ ጀመረ።

ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው እንግዲህ አቶ ማሞ አንበርብር አውቶቡስ በመግዛት የሕዝብ ማመላለስ አገልግሎታቸውን ማጠናከር የቻሉት። ከዛ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የሶስት ቀኑን መንገድ በሁለት ቀንና በአንድ ቀን ተኩል በመግባት ሕዝቡን ማስደነቅ ጀመሩ። የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የነበረው ህብረተሰብም ለጉዞ ቀዳሚ ምርጫው የአቶ ማሞ አንበርብር አውቶቡስ ሆነ።
የዚህ አስደናቂ ስራቸው ውጤት የአባታቸውን ስም አስትቶ ከስማቸው ቀጥሎ ‘ካቻ’ በሚል ቅፅል ስም እንዲጠሩ ምክንያት ሆነ። ብሎም እጅግ ታዋቂ ሊሆኑ ቻሉ። ‘ካቻ’ ማለት የጣልያን ፈጣን መትረየስ ተኳሽ አውሮፕላን መጠሪያ ነበር። አሁን ተዋጊ ጀት እንደ ሚባለው።

ይህ ድርጅት ከሌሎቹ ሻል ያሉ መንገዶች እየተመረጡ ስለሚሰጡት አቶ ማሞና ሌሎቹም ግለሰቦች ለእነሱም እንዲህ አይነት መስመር እንዲሰጣቸው ከመጎትጎት አልፈው በየስማቸው ማህበር በማቋቋም የአውቶቡሳቸውንም ቁጥር በመጨመር በሁሉም መስመር ለመሳተፍ ጥረት ማድረጉን ቀጠሉ።

በዚህ ጊዜ የድርጅታቸውን ስም በታወቁበት ስም ‘ማሞ ካቻ’ ብለው ሰየሙት። ይህን ሁሉ ተግባር የፈፀሙት አቶ ማሞ ማንበብና መጻፍ እንኳን የማይችሉ ነበሩ። አንድ ቀን ከእሳቸው ጋር ጭቅጭቅ የነበረው ሰው ሞቶ በመገኘቱ ተጠርጥረው ማስረጃ ባይገኝባቸውም አስራ አምስት አመታት ተፈርዶባቸው ወህኒ ወረዱ። በዛን በእስር ጊዜአቸው ነበር አብረው የታሰሩ ምሁራንን እየጎተጎቱ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋ ማንበብ የቻሉት። እንዲሁም መደበኛ ሒሳብም መሥራት ቻሉ።

የሚመሩት የትራንስፖርት ድርጅት ያለው አስተዋፅኦ ታይቶ በእስር ጊዜአቸው ከእስር ቤት በሳምንት ሁለት ቀን እየወጡ ሥራቸውን አከናውነው እንዲመለሱ ተደርጎ ነበር። በ 1960 ዎቹ መግቢያ ላይ ከእስር ቤት ወጡ። እንግዲህ ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ ነው አንድ አስደናቂ ተግባር ያከናወኑት። ነገሩ እንዲህ ነው

የንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ንብረት ነው የሚባለው የአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት ሰላሳ አውቶቢሶች እንዲሠሩለት ለፊያት ካምፓኒ ያዝዛል። ከሰላሳዎቹ ግማሹ ተሠርተው አዲስ አበባ ደርሰው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተመሳሳይ ችግር ያስተናግዱ ጀመር። ሕዝብን ጭነው በሚጓዙ ጊዜ የፊት ጎማቸው እየፈነዳ መገልበጥ ወይም ከመስመር እየወጡ መጋጨት ተግባራቸው ሆነ። ገናም አምስት እና ስድስቱ ተመሳሳይ አደጋ እንደደረሰባቸው፤ አቶ ማሞ ጭንቅላት ውስጥ “ለምን ይሆን?” የሚል ጥያቄ ተነሳ።
አንድ ቀን ማሞ ካቻ ከሻሸመኔ ወደ አዲስ አበባ እየነዱ ሳለ፤ አንድ አውቶቡስ ጥሩምባ ነፍቶ አለፋቸው። ይህ ጥሩምባ ነፍቶ ያለፈው አውቶቡስ አዲስ ከመጡት አንዱ በመሆኑ የማሞ ካቻን ትኩረት ሳበ። እናም ‘ለምን ይሆን?’ የሚለው ጭንቅላታቸው ውስጥ ያለው ጥያቄ ምናልባት መልሱ ቢገኝለት ብለው በማሰባቸው፤ መኪናቸውን አዙረው አውቶቢሱን መከተል ያዙ። አውቶቢሱ ሻሸመኔ ደርሶ ወደ ጎባ መንገድ ታጠፈ ተከተሉት፣ ዶዶላን አለፈ፣ ማሞ ካቻም አለፉ አውቶቢሱ ዶዶላን አልፎ ሲገሠግስ ድንገት ቁልቁለት ላይ የፊቱ ጎማ ፈነዳና ከመንገድ ወጥቶ ከአንድ ቋጥኝ ጋር ተጋጭቶ ቆመ።

ማሞ ካቻም መኪናቸውን አቁመው፤ ዱብ! ብለው ወረዱና ወደ አውቶቢሱ ተጠግተው ሁኔታውን መመርመር ጀመሩ፤ እናም ችግሩን ደረሱበት። ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ ጊዜ ሳያ ጠፉ ወደ ጣልያን (የፊያት ኩባንያ ወደሚገኝበት ወደ ቶሪኖ) በረሩ። እንደደረሱም በቀጥታ ወደ ኩባንያው አምርተው ፕሬዚዳንቱን እንዲያገናኟቸው ጠየቁ። ከብርሃኑ አስረስ (የታህሳስ ግርግርና መዘዙ መጽሐፍ) የተወሰደ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *