Press "Enter" to skip to content

የለውጡ ፍሬ ግን ገና ወደፊት የምናየው ነው – ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ

ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ በፖለቲካው ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የመግባት አጋጣሚን አግኝተውም መንግሥትን ቢያሻሽል ያሉትን ለህዝብ ይበጅ የመሰላቸውን ሃሳብ ሲሰጡ ቆይተዋል። ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልን እንደ አማራጭ ከያዙ ጥቂት የአገራችን የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ውስጥም ስማቸው ይጠቀሳል። አሁንም ከለውጡ ወዲህ አገርን ያሻግራል ያሉትን ሃሳብ ፓርቲያቸውን የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ(ኢሶዴፓ)ን ወክለው በየመድረኩ ይናገራሉ። በሌላው ጎን ደግሞ ባላቸው የትምህርት ዝግጅት እንዲሁም የሥራና የምርምር ልምድ አገርን ያገልግሉ በሚል በለውጡ አመራሮች ታምኖባቸው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ተሹመዋል። ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ።

ለውጡና የለውጡ ኃይል በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያመጡትን አዲስ ባህል እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን አንስተንላቸው ተወያይተናል።

አዲስ ዘመን፦ ከለውጡ በፊት የነበረው የኢትዮ ጵያን ፖለቲካ እንዴት ይገልጹታል?

ፕሮፌሰር በየነ፦ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በተለይም ከለውጡ በፊት በራሳቸው በፖለቲካ መሪዎቹ በህዝቡ ጭምር ተገምግሞ ብቃት ያጣ ፣ የወደቀ ፤ በአገሪቷና በህዝቦቿ ላይ ጉዳት ያደረሰ፣ የአገሪቷን ሀብት የመዘበረ ፣ያስመዘበረ፤ ሙሰኞችን ያበቀለ ፍትህ የተጓደለበት ነበር። ይህንን ለመቀየር ደግሞ 28 ዓመት ፈጅቶብናል። እኔ እንኳን ባሳለፍኳቸው ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ባሉ የፖለቲካ ሂደቶች ብናይ ለአገሪቱና ለህዝቦቿ የፈተና ጊዜ ነው የነበረው። ይህም ቢሆን ግን በኢትዮጵያ ጉዳይ ተስፋ አንቆርጥም ብለን በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ጥረት ስናደርግ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያስገቡንም ሲያስወጡንም እንዲህ እያልን የቆየን ነን። ያለፈው ስርዓት ውድቀቱ የሚጀምረው ከውጭ ባለው ግፊት እንዲሁም በራሱ መፍረክረክና የለውጥ ሰዎች የተባሉት ደግሞ የበላይነት ይዘው የኢትዮጵያ ህዝብም እሰየው ወዳለበት ለውጥ ተሸጋግረናል።

አዲስ ዘመን፦ ለውጡ ግን ይዞት የመጣው አዲስ የፖለቲካ ባህል አለ ማለት እንችላለን?

ፕሮፌሰር በየነ፦ ከመሪዎቹ ዘንድ ከፍ ያለ ግልጽነት ለውጥ እናመጣለን የሚል ድፍረትንና ልበ ሙሉነትን እናያለን፤ በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በተደጋጋሚ ብዙ ለመለወጥ ጉጉትና እቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ። እንደውም የአመለካከታቸውንም አቅጣጫ መደመር በሚል ብዙ ገጽ ባለው መጽሐፍ አስቀምጠው ጉዟቸውንም በዚያው መንገድ እየሄዱ ነው፤ ይህንንም አይተናል።

ከዚህ ቀደም ማለትም ፖለቲካው ላይ በንቃት መሳተፍ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ ያየሁት ነገር አይደለም። ለነገሩ የቀድሞ ኢህአዴግን ሲመሩት የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም እንዲሁ ዝም ብለው የዋህና አላዋቂ ሰው አይደሉም፤ ብልጠትም እውቀትም ያላቸው ነበሩ። ነገር ግን አሁን አንደምናየው አሳታፊ አይደሉም፤ እንደውም አንድ ነገር ብያለሁ ብያለሁ ብለው በአራት ነጥብ የሚዘጉም ነበሩ። ከዚህ የወጣ ሰው እንግዲህ ከስርዓቱ ጋር ተጣላ ማለት ነው።

አሁን ከለውጡ ወዲህ ደግሞ አሳታፊነትም ይታያል፤ በተለይም በከፍተኛው የአመራር ደረጃ። በዚህም ወጣቱንም ልምድ ያለውንም ሴቶችንም የማሳተፍና የማብቃት ወደኃላፊነት እንዲመጡ የማድረግ ይሁንታ አለ። ይህ ደግሞ እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም ሁሉ ያደነቀው ነገር ነው።

ለምሳሌ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን ሰላምም ጦርነትም የሌለውን አካሄድ በድፍረት መፍትሔ ለመስጠት ያንቀሳቀሰ የለውጥ ኃይል ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ቀደም ሲል የነበሩትም ተነጋግረውበት ያውቃሉ። መፍትሔ እንሰጣለን ከሚል ነገር ውጪ ግን የፈየዱት ነገር የለም። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስቴር በነበሩበት ጊዜ የምክር ቤት መክፈቻ ንግግራቸው የመጀመሪያ ሥራዬ ለኤርትራ ችግር መፍትሔ መስጠት ነው፤ በፈለጉት ጊዜ አሥመራ እመጣለሁ ማለታቸውን አስታውሳለሁ። ምናልባት እሳቸው ይህንን ካሉ በኋላ ጥሪ ይሆናል የሚጠብቁት ፤ የለውጡ አመራሮች ግን ትንፍሽ ሳይሉ ነው አሥመራ ላይ የወረዱት። እነዚህ ነገሮች እንግዲህ ፖለቲካዊ እንደምታዎች ናቸው።

በኢኮኖሚውም ዘርፍ አገር በቀል ኢኮኖሚ እቅድን አውጥቶ ላሉት ችግሮች መፍትሔ በራሳችን ባለሙያዎች እንዲቀርብ ለማድረግ የሚያስችል ልበ ሙሉነት የታየባቸው ናቸው። የእነዚህን ለውጦች ፍሬ ግን ገና ወደፊት የምናየው ነው።

ነገር ግን አሁንም ለውጡ ወደታች ህብረተሰቡ ጋር ዘልቆ አልሄደም የሚል ሂስ እኔም ፓርቲዬም ስናቀርብ ቆይተናል። እንደውም በመጀመሪያ ቀን ከዶክተር አብይ ጋር የመገናኘት ዕድል ያጋጠመኝ እለት የተጠየኩት ጥያቄ እስከ አሁን ድረስ የምንወስዳቸው ዕርምጃዎች ምን ይመስልዎታል የሚል ነበር? እኔም መልሴ ለውጡ መሬት ይርገጥ የሚል ነበር። ተጠቃሚውም ጉዳቱ የሚበዛበትም ታች ያለው ሰው ነው፤ በመሆኑም በቀበሌ፣ በገበሬ ማህበሩም ሁሉም ድረስ ወርዶ ይፈተሽ ብቃት ያላቸው አመራሮች ይሾሙበት የሚል ነበር ።

አዲስ ዘመን፦ ለውጡን እየተፈታተኑ ያሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ምንጫቸው ምንድን ነው ብለው ያምናሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፦ ኢትዮጵያዊነትንና ህዝቡን በተለያየ እይታ መሳል የተለመደ ነው። ኢትዮጵያን የፍቅር ፣የደስታ ፣ የትብብር እና የአንድነት አገር ብለው የሚስሉ ወገኖች በስፋት አሉ። በአንጻሩ ደግሞ ይህ ነገር በመሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አይጣጣምም የሚሉ አሉ። እንግዲህ ብዝሀነታችን ውበታችን ነው ያልነውን ያህል በራሱ ደግሞ ተግዳሮቶች ይዞ እየመጣ ነው፤ ለነገሩ በቤተሰብም ውስጥ እኮ ሁለት ልጅ የወለደና አስራ አምስት ልጆች የሚተራመሱበት ቤት እኩል ሰላም የሚኖር አይመስለኝም።

መቀናናቱ አባቴ እከሌን ነው የሚወደው ያዳላሉ የሚለው ነገር ይፈጠራል። ይህንን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ስናመጣው ተግዳሮቶቹ ዋዛ አይደሉም። በምንም መልኩ ቢሠራ ሁሉንም ወደ መካከል ማምጣት ይቻላል የሚለው ደግሞ በቀላሉ የሚሳካ አይደለም። ስለዚህ አገራችን ውስጥ የምናያቸው የመቀናቀን፣ ከዚህ ውጣልኝ የእኔ ነው አገሩ የሚለው የአካባቢ ባለቤትነት ስሜት በራሱ እንዲሁም በመንግሥትም በኩል በፍትሐዊነት እየተስተናገድን አይደለም የሚሉ ጉዳዮች በጣም ብዙ ናቸው። ይህንን ችግር አንድ በአንድ ለመመለስና ለመፍታት ደግሞ ፋታ ማግኘትም ያስፈልጋል። ግን ደግሞ ባለው ቀዳዳም መታገል የመንግሥት ትልቅ ሥራው ነው፣ እያደረገውም ነው።

አዋቂዎች ነን የሚሉ ኃይሎች አገሪቷን ትልቅ ችግር ውስጥ የከተቱበት ሁኔታ አለ ፤ እነሱ እኮ አገሪቱን ከ30 ዓመት በላይ የመሩ ናቸው ፣ አገሪቱ በእነሱ እጅ ነበረች እንዴ የሚያሰኝ እኮ ነው የሚታየው ነገር። ይህንን

ስርዓት ያጋጠመው ትልቁ ችግርም ይኸው ነው። አንድ የአገራችን ተረት አለ “ላም እሳት ወልዳ እንዳትልሰው እሳት እንዳትተወው ልጅ ሆነባት” ይባላል፤ አገሪቱ ላይም እነሱ ያመጡት ችግር ይኸው እስከ አሁን እየፈተነን ነው።

በወቅቱም እኮ ይህ እንደሚመጣ አውቀን ተዉ እባካችሁ ይህ አካሄድ ኋላ ችግር ውስጥ ይከታል ፣ መሻሻል አለበት ስንል ነው የኖርነው። ያም ሆኖ ግን ዛሬ ላይ ያደረጉትን ነገር አድርገው የሆኑትንም ሆነዋል አገሪቱንም ከፍ ወዳለ ተግዳሮት ውስጥ ጨምረዋታል።

ሁሉም የራሴ እውነት አለኝ ይላል ግን ደግሞ ሁሉንም መመርመር ሲቻል ግን ችግሩን ለውጡ ያመጣው ሳይሆን ታምቆ የቆየ መተንፈሻ ቀዳዳ ሲያገኝ እየወጣ ያለ ነው። በመሆኑም ችግሮቹን በስልት እየፈቱ ለመሄድ ፋታም አልተገኘም። ነገር ግን ይህም ቢሆን በለውጡ ቀጣይነት ላይ በግሌ ተስፋ አልቆርጥም።

አዲስ ዘመን፦ እነዚህን ችግሮች አሸንፎ ለመው ጣት ምን መደረግ አለበት ይላሉ ?

ፕሮፌሰር በየነ፦ እኔ የከብት እረኛም ነበርኩ እና አንድ በረት ውስጥ ባሉ ከብቶች መካከል አንድ ወይም ሁለት ረባሽ ከብት ካለ የቀሩትን ሁሉ ዕረፍት ይነሳል ይወጋቸዋል፣ ያሸብራል። በረቱን ኢትዮጵያ በይው በቃ አሁን እያየን ያለነውም ይህንኑ ነው።

የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው አንዱ ሰላም ወዳድ ሌላው አደፍራሽ ሆኗል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያውያን ብሶታቸውን በወቅቱ መታረም በሚችልበት ጊዜ አውጥተው አይናገሩም ከዚያ ይልቅ ሆድ የፍጀው ብለው አምቀው ይቀመጣሉ፤ ይህ ደግሞ ይጠራቀምና ክፍተት ሲገኝ ሁሉም እሳቱን ይዞ ይነሳል።

ህዝቡ ግልጽ ሆኖ ቸግሩን እና ብሶቱን በወቅቱ መግለጽን መለማመድ አለበት፤ ይህ ደግሞ ለመፍትሔውም ቅርብ እንድንሆን ያደርገናል። በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም ነገር በአንድ ጀንበር ካልሆነ ብሎ ከመተናነቅ ይልቅ ትዕግስት ማድረግ ችግሩን አሸንፎ ለመውጣት መንገዱ ነው።

በተለይም ተማርን ፖለቲካውን እናውቀዋለን የሚሉ አካላት በአንድ ጀንበር መፍትሔ እንደማይመጣ እያወቁ ህዝቡንም ወዳልሆነ መንገድ ከመምራት ይልቅ እነሱም ሰከን ብለው ህዝቡም ተረጋግቶ የሚጠቅምና የሚጎዳውን ነገር እንዲያውቅ ማድረግ መቻል አለባቸው።

ኢትዮጵያውያን እኮ በጣም ልዩዎች ነን ፤ ኢትዮጵያዊ መባል የሚፈልግ እኮ ብዙ አለ። ይህ ደግሞ ውሸት አይደለም። ጃማይካውያን እና ሌሎችም ኢትዮጵያዊ ለመምሰል ጥረት ሲያደርጉ እናያለን። ለኛ ምናልባት በእጅ የያዙት ወርቅ ሆኖብን ይሆናል እንጂ ከኢትዮጵያዊነት ውጪ አስቦ የተከበርኩ ህዝብ ነኝ ማለት የማይሆን ነገር ነው። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ነው ሁሉም የሚከበረው፤ የሚጠቀመው።

አዲስ ዘመን፦ የለውጡ ሦስት ዓመት አንደኛው ሥራ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማቀራረብ ለመንግሥትም እርስ በእርሳቸው እንዲቀራረቡ ማድረግ ነውና በዚህስ ላይ ያልዎት ሃሳብ ምን ይመስላል?

ፕሮፌሰር በየነ፦ እኔ የምለው የበላይ አመራሩ የመጀመሪያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አነጋግራለሁ ብሎ በጠሩበት ስብሰባ ተገኝቻለሁ እና እራዕያቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ከመቶ በላይ የሆነው የፖለቲካ ፓርቲ ምን ያደርጋል የሰለጠኑ አገሮች ጥቂት ፖለቲካ ፓርቲዎች ሲፎካከሩ የመንግሥት ስልጣንንም ተራ በተራ ሲቀባበሉ ይታያል፤ እና ለምን ወደእሱ አንመጣም የሚል ነበር።

ነገር ግን የሰለጠኑት አገራት የሚሄዱበት አካሄድም ፍጹም ነው ማለት አይቻልም እንደ ትራምፕ አይነቱ እብድ መጥቶ ያተራምሳል ፤ምንም ፍጹማዊ የሆነ ነገር የለም። ግን በአንጻራዊነት የሚፎካከሩት የተወሰኑ ፓርቲዎች ናቸው ይባላል፤ እሱም ቢሆን ፍጹም እውነት አይደለም። አሜሪካን አገር ከ50 በላይ ፓርቲዎች አሉ በየ ጊዜው ምርጫ ሲመጣ ውድድር ውስጥ ዕጩዎቻቸውን የሚያቀርቡት ከእነዚህ ፓርቲዎች ነው። አንዳንድ ጊዜ 10 ሚሊዮን ድምፅ የሚያገኙ አሉ በአብዛኛው ጊዜ እስከ 5 ሚሊዮን ድምፅ ያገኛሉ ።

ይህ እንግዲህ በእነሱ ባደጉት አገራት ነው ወደእኛ ስንመጣ ደግሞ ፓርቲዎቹ በጣም ብዙ ናቸው ማለቱ ልክ ቢሆንም በፖለቲካ አደረጃጀት ታሪክ ውስጥ ረጅም ዓመት በፓርቲነት ቆይተው ሁሉም ሰው የሚያውቃቸው ግን በጣም ጥቂት ናቸው።

ለምሳሌ በኢትዮጵያ ባለፈው ታሪክ ውስጥ ከ1966 ዓ.ም ለውጥ በኋላ በተከሰተው ሁኔታ ኢህአፓና መኢሶን የሚባሉ ፓርቲዎች ነበሩ ፤ከዚያ ደግሞ የደርግ ፓርቲም አለ ለምሳሌ በወቅቱ ፓርቲዎቹ ለመንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታ ቢኖር ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢህአፓ የሚባል ፓርቲ መኢሶን የሚባል ፓርቲ ሦስተኛው የ ደርጉ መጨረሻ ላይ የመሰረተው አንድ ፓርቲ አለ፤ እነዚህ እየተፎካከሩ ቢመጡ አሁን ላለንበት የፖለቲካ ፓርቲዎች አመሰራረትና አካሄድ መነሻ ይሆን ነበር። ከዚያም እንደ አሜሪካና ሌሎች አገሮች የፓርቲዎቻችንን ቁጥር መጥነን ዕጩዎችን ከእነሱ እየመዘዝን እንሄድ ነበር ገን አልሆነም።

ይሄ የለውጡ ኃይል ፓርቲዎችን አሰባስቦ የበኩሌን ድጋፍ እሰጣለሁ ግን ደግሞ እንደዚህ መብዛት የለባችሁም ወደ አንድ ተሰባሰቡ ብሎ መከራከሪያ አቀረበ፤ በበኩሌ ይሄ በፖለቲካል አካሄድ የዋህ የሆነ አስተሳሰብ ነው። በሌላ በኩልም ፓርቲዎቹ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲበዙ ያደረገውን መሰረታዊ ጉዳይ ያላገናዘበ ንግግር ነው። በሌላ በኩልም ፓርቲዎቹ እታገልለታለሁ የሚሉትን ብሔረሰብ የሚደፈጥጥ ይመስለኛል። በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ብዙ ጊዜያቸውን አጥፍተዋል። ከእነዚህ ፓርቲ ከተባሉ ቡድኖች ጋር ልክ እንደ ግለሰብ እርሳቸውም እንደ ገዥው ፓርቲ መሪ በመሆን ክርክር ውስጥ ተሳትፈዋል።

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተካሄደው ስብሰባ ጥናታዊ ጽሑፍ ሁሉ አቅርበው ሁላችንም ትላልቅ አንኳር የሆኑ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች አቅርበን ውይይት እንዲካሄድበት ሁሉ ሲያስደርጉ ነበር። ከዚያም የጋራ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ወይም ምክር ቤት እንዲቋቋም ሆኗል። የመግባቢያ ሰነድ እንዲፈረም እራሳቸውም ፓርቲያቸውን ወክለው መጥተው በመፈረም ብዙ ጥረት አድርገዋል።

የማንነቴ ጥያቄ ቢመለስልኝ ዛሬውኑ ፓርቲዬን አፈርሳለሁ የሚሉ ፓርቲዎች ያሉበት አገር እኮ ነው። የማንነት ጥያቄ መመለስ ማለት ምን መሰለሽ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ስም ዝርዝር ውስጥ አልገባንም እዚያ ዝርዝር ውስጥ እስካልገባ ድረስ እንታገላለን ማለት ነው። ስለዚህ ምክንያታቸው በደንብ መታወቅ አለበት። ካልሆነ ሁላችሁም አንድ ላይ ሁኑ እንዲህ ሁኑ የሚለው ምክር አይሠራም። ሕዝቡ ነው እሱን የሚለየው።

ሌላው መንግሥት ፓርቲዎችን ለማቀራረብ እራሱንም ቅርብ ለማድረግ ሠርቷል። ይህ የማይካድ ሀቅ ነው። ግን ደግሞ ከላይ እንዳነሳሁት ፓርቲዎች ለምን አንደዚህ በዙ የሚለው ነገር ጊዜ ተሰጥቶት ተፈትሾና ተመርምሮ መፍትሔም ማግኘት ያለበት ይመስለኛል።

አዲስ ዘመን፦ ፖለቲካል ምህዳሩን ከማስፋት አኳያ የለውጡ አመራር እየሄደበት ያለው መንገድ ለምሳሌ እንደ እርስዎ ዓይነት ምሁርንም ወደ መንግሥት ኃላፊነት ማምጣት ለውጥ አይደለም ብለው ያስባሉ?

ፕሮፌሰር በየነ፦ እኔ እንግዲህ በግሌ እንደ አንድ የሚሞከርብኝ ሰው አድርጌ ወስጀዋለሁ። የፖሊሲ ምርምር ተቋም ውስጥ ምክትል ኃላፊ ሆነህ እንደው አገርህን ብታግዝ? የሚል ጥያቄ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ከራሳቸው ነው የቀረበልኝ። አይ ይሄ አስተሳሰብ አዲስ ነው መደገፍ አለበት ምክንያቱም በኢትዮጵያ ውስጥ የዚህ ዓይነቱ ታይቶ አይታወቅም። ምናልባት በሽግግሩ ወቅት ሚዛን የሚደፋ ፓርቲ አባል ሳንሆን ኃላፊነቱን ወስደናል። የሽግግሩ መንግሥት ግን የጣምራ መንግሥት ነበር እንጅ የኢህአዴግ መንግሥት ብቻ አይደለም። ኦነግ ፣ ከደቡብ አካባቢም የተደራጀን የፖለቲካ ፓርቲ ነበርን፣ ሌሎች ሌሎችም ነበሩበት። ያ የሚታወቅ የጥምር መንግሥት ስለሆነ ነው። የአሁኑ መንግሥት በምርጫ አሸንፌ ስልጣን ይዣለሁ የሚለው ኢህአዴግ ወራሽ የሆነ ነው። ስለዚህ ከኢህአዴግ ጋር ወደ ሃያ ስንት ዓመት እኛ ተቃዋሚ ተብለን እነርሱ ደግሞ ገዥ ፓርቲ ተብለው በቆየንበት ወቅት በመንግሥታዊ ስርዓት ውስት መድረስ የቻልነው ጥቂቶች ብቻ ነን።

ጥቂቶቻችን ፓርላማ ገብተናል ከዚያ አላለፍንም። ፓርላማ ሆኖ ዕድል ሲሰጥ አስተያየት መስጠት ነው ፤ሌላ ምንም የለውም። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ይችን ከፓርቲ መስመር ወጣ ብሎ ለምን በዚህ አሁን እኔ የተመደብኩት ምሁራን በሚለው እንጅ ፖለቲካዊ ይዘት የለውም። ምንም እንኳን መሪዎችን መንግሥት የሚመድብ ቢሆንም ሥራው ግን ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ሆኖ ቁጭ በል ተነስ የሚባልበት አይነት አይደለም። ቀጥሎ ደግሞ ዶክተር አረጋዊ በርሔም የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ዳይሬክተር ሆኗል።

ይሄ ለኢትዮጵያ አዲስ ፖለቲካዊ ታሪክ ነው። ይህንን ስልጣን ላይ ያለው አካል ይችን መስመር ጥሶ እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ማድረግ ሲፈልግ እኛ ደግሞ ውጭ ያለነው ሞቼ እገኛለሁ በማለት አዲስ አስተሳሰብና አሠራር እንዳይመጣ እንዴያው ደንቃራ መሆን አያስፈልግም። ከዚህ ስሜት ተነስተን ነው። እኔ አሁንም ብዙ ሸክም አለብኝ በየነ ሄዶ ብልጽግና ገባ፣ ለራሱ ጥቅም ፈልጎ ምናምን የሚሉ አሉ። መንግሥት አንድ መኪናና ሾፌር ነው የመደበልኝ ልዩ ነገር እንኳን ቢባል። ለራሱ ጥቅም አገኘ እንግዲህ ተቃውሞውን ትቶታል ይላሉ። ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር በዚህ የምርምር ተቋም በመለስተኛ ኃላፊነት እንዲሠሩ መድበናል ፤ሲባል ያው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪነቴም ስሜም እየተጠቀሰ ነው። ስለዚህ ያችን እስካልሳቱብኝ ድረስ ጥሩ ልምድ ነው ብዬ ተቀላቅያለሁ። ይህ መለመድ አለበት ከመሆኑም በላይ በግሌ የተሰጠኝን በቅን ኃላፊነት ለመወጣት እየሞከርኩ ነው። ግን የፓርቲዬን መስመር የሚያስክድ አይደለም። አሁንም ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ አጀንዳ የምንለውን ይዘን ወደ ምርጫ ገብተን ለመመረጥ ጥረት እያደረግን ነው።

አዲስ ዘመን፦ ትውቅልዱን አገር ተረካቢ ከመሆን አንጻር እንዴት ይገልጹታል ? ምንስ ነው መደረግ ያለበት?

ፕሮፌሰር በየነ፦ ትውልዱ ሰከን ማለት አለበት ዝም ብሎ ጫፍ ይዞ መሮጥ የመለበትም። ማህበራዊ ሚዲያውና ሌላውም ላይ የሚጻፈውን እየተመለከተ አቅሙን እና እምነቱን ከሚሸረሽር ወደቀ ሲሉት ተሰበረ ብሎ የሚሮጥ እሳት ተቀጣጠለ ሲባል ቤንዚን ጨምሮ የሚያራግብ ከመሆን መውጣት አለበት።

አውቆ መረጃ ይዞ የሚናገር ነው መሆን ያለበት። ስነ ምግባሩንም መጠበቅ አለበት፣ ችግሮች ሲያይ ሰከን ብሎ መፍትሔ መፈለግ ያስፈልግል። ነገር ግን በተለይም በእኩይ ተግባር ላይ ያሉ ወጣቶች ስለ አገራቸው ብሎም ስለራሳቸው ነገ ቆም ብለው ማሰብን ቢለማመዱና ረጋ ቢሉ መልካም ነው።

እነሱ እንደሚከሱት አገሪቱ ላይ የተነሱ ችግሮች በአንድ ጀንበር ማዳፈን አይቻልም። ከዚያ ይልቅ ብዙ ስልት ጥበብ ጊዜ ገንዘብና የሰው ኃይል አንደሚያስፈልግ ማስተዋል ያስፈልጋል። የችግር ምንጭ ከመሆን መፍትሔ መሆንን ይጠይቃል።

በሌላ በኩል ደግሞ ወጣቱ ማንበብ መመራመር ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎቹን ማጥናትም ይገባዋል። ይህ ሲሆን አገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆን ነገ ሌላውንም ለመምራት የሚችል ኃይል ይሆናል። አዲስ ዘመን

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//phaurtuh.net/4/4057774