Press "Enter" to skip to content

የጎዳና ተዳዳሪው የወታደራዊ ደህንነትና መረጃ መኮንን ኮሎኔል ካሣሁን ትርፌ

እንደ አለመታደል ሆኖ ከቅርብ የታሪካችን ዘመን እንኳን ብንነሳ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ የሆነ፣ ብሔራዊ ስሜት ያለው፣ ጠንካራ የሆነ ሕዝባዊ መሠረት ያለው የመከላከያ ኃይል ለመፍጠር እየተደረገ የነበረውና አሁንም እያየነው ያለው ሙከራ መንግሥት በተለዋወጠ ቁጥር ሂደቱ እየተገታ ከዚህ ደርሰናል።

በአገሪቱ ዘመናዊ የመከላከያ ኃይል በመገንባት ረገድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያደረጉት ጥረት ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካና በኮርያ ልሣነ ምድር ድረስ ሳይቀር ዘልቆ ብቃቱንና ጥንካሬውን ያስመሰከረ፣ የኢትዮጵያዊነት ከፍተኛ ስሜት፣ ኩራትና ወኔ ያለው የመከላከያ ኃይል ሠራዊት ሊፈጥሩ መቻላቸውን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።

ይሁን እንጂ የዘውዱን ሥርዓት የገረሰሰው ወታደራዊው የደርግ መንግሥት አገሪቱ ገንዘቧንና ጥሪቷን አፍስሳ ያስተማረቻቸውን እነዛን ምርጥ የጦር መኮንኖች በአንድ ጀምበር ረሽኖ በጉድጓድ ውስጥ እንደ ጉድፍ ሲከምራቸው እንደምንም አልቆጠረውም ነበር።

ያ በሚሊተሪ ሳይንስ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ከፍተኛ የሆነ እውቀትን የቀሰመና በወታደራዊ ዲሲፕሊን ይህ ቀረው የማይባልና የማይታማው ሠራዊት ዕድል ፈንታው፣ ጽዋ ተርታው እንደ ቆሻሻ ተቆጥሮና ተጠርጎ የትም መጣል ነው የሆነው።

‹‹ኮዳ ትራሳቸው›› የሚል ስምና ዝናና ያተረፉትን፣ ከጥንት ከአባቶቻቸው የተረከቧትን የእማማ ኢትዮጵያን፣ የእናት አገራቸውን ዳር ድንበር በደማቸውና በአጥንታቸው ለማስከበር ዱር ቤት ብለው በምንም ዋጋ ሊተመን በማይችል ክቡር መሥዋዕትነት የከፈሉትን የጦር መኮንኖችን ደርጉ በተለያየ ጊዜ አድኃሪና ፊውዳል፣ ፀረ ሕዝብና ፀረ አብዮተኛ በሚል በአብዮታዊ እርምጃ ስም ረሸናቸው። ከደርግ የጭካኔ ሰይፍ ያመለጡትም በግፍ ተሰደዱ። ሌሎቹም በሰሜን ተራሮችና በረሃዎች ለእናት ምድራቸው ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው መሥዋዕት ሆነው በክብር አለፉ።

ከደርግ ሠራዊት ጋር ለ17 ዓመታት ያህል ተዋግቶ በለስ የቀናው ባለተራው ኢህአዴግም ያ ደርግ የተማመነበት፣ አፍሪካን ጭምር ያሠጋል የተባለውን ግዙፍ ሠራዊት ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሲያሸነፍና ሠራዊቱም እንዳልሆነ ሁኖ ሲበተን፣ የደርግ ሠራዊት ዕድል ፈንታ የሆነው በየሜዳው ላይ ልብሱንና ማእረጉን አንጥፎ መለመን ነበር። ቤተሰቤ፣ ልጆቼ፣ ሚስቴ፣ ዘመዶቼና ወገኖቼ ሳይል በረሃ ለበረሃ፣ ቆንጥር ለቆንጥር፣ ገደል ለገደል የተንከራተተው ሠራዊት በስተመጨረሻም ዕድሉ ያማረ አልሆነለትም ነበር።

የትላንትናው የከፍተኛ ወታደራዊ መረጃና ድህነት ከፍተኛ መኮንን የሆኑት፣ የዛሬው ባለ ታሪክ የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑት ግለሰብ በጃንሆይና በደርግ መንግሥት ከሶማሊያ የጦር ግንባር እስከ ኤርትራ- ኡምሃጁር፣ ከረን፣ ተሰነይና ናቅፋ የጦር ግንባሮች የተሳተፉ ናቸው። እንዲሁም በመከላከያ ሚኒስቴርና በማእከላዊ እዝ ከፍተኛ የወታደራዊ ደህንነትና መረጃ መኮንን በመሆንም የሠሩ ናቸው። እኚህ መኮንን ከባለቤታቸው ሞት በኋላ ከአንድ ዓመት በላይ በጎዳና ተዳዳሪነት የቆዩ ሲሆኑ፣ ሙሉ ስማቸውም ኮሎኔል ካሣሁን ትርፌ ይባላል።

ከኮሎኔል ጋር ስለ ውትድርና፣ ስለ ጦር አውድማዎችና በአጠቃላይ ስለ ሕይወት ታሪካቸውና እንዴት ለጎዳና ሕይወት ሊበቁ እንደቻሉ እየተጨዋወትን ለረጅም ሰዓታት አብረን ቆይታ አድርገናል። በማስታወሻዬ የዘገብኩትን የኮረኔል ካሣሁን ትርፌን ሰፊና መሳጭ የሕይወት ታሪክ ታነቡት ዘንድ እጅግ በጣም አሳጥሬ በዚህ መልኩ ላካፍላችኹ ወደድኹ።

ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ ተወለዱት በሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ከተማ በ1939 ዓ.ም. ነው። የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአፄ ዘርዓያዕቆብና በኃይለ ማርያም ማሞ ትምህርት ቤት ነው የተከታተሉት። በሁለተኛ ደረጃ መለቀቂያ ፈተና ከፍተኛ የሆነ ውጤት ያስመዘገቡት የ17 ዓመቱ ወጣት ካሳሁን ትርፌ በጊዜው የላቀ ውጤት ያመጡ ልጆች ወደሚላኩበት ወደ ሐረር የጦር አካዳሚ ለሦስት ዓመት ለወታደራዊ ስልጠና ተላኩ። በወቅቱ በሐረር አካዳሚ ወታደራዊና አካዳሚያዊ ስልጠና ጎን ለጎን በአንድነት የሚሰጥበት ደረጃውን የጠበቀ ተቋም እንደነበር ያስታውሳሉ ኮሎኔል ካሳሁን።

ኮሎኔል ካሳሁን ስለ ሐረር የጦር አካዳሚ ትምህርት ቤት የትምህርት አሰጣጥ ጥራት፣ ብቃትና በአካዳሚው ስለነበራቸው ቆይታ ሲያጫውቱኝ፣ ከሚሊታሪ ሳይንስ ውጭ እንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ ቋንቋ፣ ከሳይንስ ትምህርቶችም ሂሳብና ፊዚክስ፣ ከሶሻል ደግሞ ኢኮኖሚክስ፣ ኅብረተሰብና የታሪክ ትምህርት ጭምርም ይሰጥ እንደነበር አጫውተውኛል።

ኮሎኔል በዘመናቸው ከእርሳቸው ጋር የነበሩትን ሰልጣኝ ተማሪ ጓደኞቻቸውንና መምህራኖቻቸውን ሲያስታውሱም፣ ከፍተኛ የሆነ ኢትዮጵያዊ ስሜትና ወኔ ያላቸው፣ በሚሊታሪ ሳይንስና በወታደራዊ ዲሲፕሊን የታነጹ፣ ለአገርና ለወገን ክብር ተቆርቋሪ የሆኑ፣ ሰልጣኞችና መምህራን ነበሩ በአካዳሚው የነበሩት ሲሉ ያስታውሳሉ።

ኮሎኔል ከሐረር አካዳሚ ተመርቀው ከወጡ በኋላ በምክትል መቶ አለቃነት በጊዜው በተሰጣቸው ወታደራዊ ግዳጅ መሠረት ለሁለት ዓመት አገልግሎት ለመስጠት ወደ ኦጋዴን ነበር የሄዱት። በዛም የአንበሳው ክፍለ ጦር 22ኛ ሻለቃን ጦርን ተቀላቀሉ። በኦጋዴን የሁለት ዓመት ወታደራዊ ግዳጃቸውን ከጨረሱ በኋላም በወታደራዊ መረጃና ደህንነት ትምህርት ስፔሻላይዝድ ለማድረግ ወደ ሆለታ ገነት አካዳሚ ገቡ።

በሆለታ አካዳሚ ለአንድ ዓመት ስልጠና የወሰዱት ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ ከዚህ በኋላ ዋና ሥራቸው የነበረው የወታደራዊ መረጃና ድህንነት ሥራ ነበር። ኮሎኔል ከሆለታ ገነት ስልጠናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ዳግመኛ ወደ ኦጋዴን ገላዲ በመመለስ በ3ኛ ሻለቃ ውስጥ በመረጃ መኮንንነት ማገልገል ጀመሩ። በ1966 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢም ወደ ሐረር ክፍለ ጦር መምሪያ በመምጣት የክፍለ ጦሩ ሴኩሪቲ ኦፊሰር በመሆን ሥራቸውን ቀጠሉ።

በአገሪቱ የለውጥ ንፋስ እየነፈሰበት በነበረበት በዛን ወቅት በአገራችን ምስራቃዊ ክፍል ያለችው ሶማሊያ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በመግባት የደፈጣ ጥቃት በማድረግ ትንኮሳ ታደረግ እንደነበር አስታወሱኝ። ሶማሊያውያን አሉ ኮረኔል በሌላ በኩል ደግሞ በዲፕሎማሲው መስክ የግዛት ይገባኛል ጥያቄቸውን ለአፍሪካ አንድነትና ለዓለም አቀፉ መንግሥታት ድረጅት ድረስ በማሳወቅ በኢትዮጵያ ላይ ጫን በመፍጠር ታላቋን ሶማሊያን መፍጠር ቅዠታቸውን ዕውን ለማድረግ ሩጫውን ተያያዙት።

ከአሜሪካና ከራሺያ ባገኘችው ከፍተኛ የሆነ የጦር መሳሪያ እርዳታ ከ1966 አብዮትና ለውጥ በኋላ ሶማሊያ በምስራቅ አገራችን ክፍል እስከ ኦጋዴንና ሐረድ ድረስ ዘልቃ በመግባት የደፈጣ ጥቃት ሰነዘረች። ይህ የሶማሊያ ጥቃት በለውጥ ግርግርና ገና አለመረጋጋት ላይ ለነበረችው አገራችን ኢትዮጵያና የደረጉ መንግሥት እንደ ዱብዳ ነበር ይላሉ ኮረኔል፤ የሶማሊያን ወረራን ወደኋላ ተጉዘው ሲያስታውሱት።

በወቅቱ ይላሉ ኮሎኔል ካሣሁን በሐረር ግንባር የነበረው ጦር ያለውን ኃይል ሁሉ አስተባብሮ የሶማሊያን ወራሪ ኃይል ተቋቁሞ ለመመከት ችሎ ነበር። በኋላም ደርግ በክተት ዘመቻ ለሦስት ወራት ያሰለጠናቸው የሚሊሻ ሠራዊት ከሶሻሊስት ወዳጅ አገሮች ከየመንና ከኩባ በተገኘ የጦር መሳሪያ እርዳታና ወታደራዊ ኃይል ድጋፍ የሶማሊያ ጦር በኢትዮጵያውያን ጀግኖች አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ዳግም ላያንሰራረራ፣ አክርካሪውን ተመትቶ በመጣበት እግሩ ሽንፈትን ተከናንቦ ወደ አገሩ ተመለሰ። የሲያ አድባሬ ታላቋን ሶማሊያን የመፍጠር ከንቱ ምኞትም የቁም ቅዠት ሆኖ ቀረ።

ኮሎኔል በዚህ ጦርነት ወቅት ዋና ሥራዬ የነበረው ይላሉ የጦር መረጃ መሰብሰብና የአየር ላይ ቅኝት በማድረግ የጠላትን እንቅስቃሴና የማጥቃት እርምጃ ቀድሞ ለወገን ሠራዊት መረጃ በማቀበል፣ ለሠራዊቱ የማጥቃትና የመከላከል እቅድ መንደፍ እንደሆነ ይናገራሉ። ከሶማሊያው ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት በድል ከተደመደመ በኋላ ኮሎኔል ካሳሁን በሐረር ከቤተሰባቸው ጋር ለጥቂት ሳምንታት ቆይታ ካደረጉ በኋላ በቀጥታ የተላኩት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የኤርትራ የጦር ግንባር ነበር።

ኮሎኔል ይህ ወደ ኤርትራ ያደረጉትን ረጅም ጉዞአቸውን ሲተርኩልኝም፣ ከሐረር ተነስተው መቀሌ ከደረሱና በመቀሌ ለጥቂት ሳምንታት ቆይታ ካደረጉ በኋላ የሰሜኑ ጦርነት በመፋፋሙና እየገፋ በመምጣቱ የተነሣ ከመቀሌ ተነስተው ኡምኻጁርን፣ ተሰነይን፣ ባሬንቱ አልፈው ወደ አቁርደት ገቡ። በአቁርደትም በተለያዩ የወታደራዊ መረጃ ሥራዎችን በመሥራትና ጦሩን በማጠናከር ሥራ ለሦስት ወራት ከቆዩ በኋላ 3ኛውን ክፍለ ጦር በመቀላቀል በከፍተኛ መሥዋዕትነት ከረንን ከሻቢያ አስለቀቁ።

የሻቢያ ጦር ከከረን ሽንፈቱ በኋላ የመሸገው በናቅፋ ተራራ ላይ ነበር አሉኝ ኮሎኔል። ያን ደም እንደ ጎርፍ የተንዠቀዠቀበትን፣ የሰሜን ተራሮች፣ የኢትዮጵያ ምድር በደም አበላ የተመታበትንና ምድሪቱ አኬል ዳማ የሆነችበት፣ የአንድ እናት ማኅፀን ክፋዮች በገዛ ደማቸው በዋኙበት በሰሜኑ የጦር ግንባር ያሳለፉትን መሪር ትዝታ ወደኋላ ሄደው እያስታወሱት። ከከረኑ የጦር ግንባር በኋላ ኮሎኔል እንባ ባቀረረ ዓይናቸው አተኩረው እያዩኝ፣ ቀጣዩና ወሳኙ ጦርነት የተካሄደው በናቅፋ ግንባር ነበር አሉኝ።

ይህ በናቅፋ የጦር ግንባር የተካሄደውን እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነትና እልቂት የየትኛው ደራሲ ብዕር፣ የየትኛው የጥበብ ሰው ብሩሽ፣ የትኛውስ ደራሲ ምናብ በትክክል ሊተርከው፣ ሊስለው ይችል ይሆን በማለት ኮሎኔል ወደዛ ተወዳዳሪ የሌለው ወደሚመስለው የሰሜኑ ግንባር የእልቂትና የፍጅት የጦር አውድማ ሕሊናቸውን በትዝታ ሰደው ለጥቂት ደቂቃዎች በዝምታና በትካዜ ውስጥ ሆነው ቆዩ።

በኮሎኔሉ እንደ መርግ በከበደ ዝምታቸውና ትካዜያቸው ውስጥ የእኔ ሕሊና ደግሞ በሰሜን ተራራ የወደቁ የኢትዮጵያ የማኅፀኗ ክፋዮች፣ የውድ ልጆቿ የደም ጩኸታቸው፣ በተራረሮቿና በሜዳዎቿ የተከሰከሰው አጥንቶቻቸው፣ ለእናት ምድራቸው ዳርድንበር መከበር ደማቸውን ከቀይ ባሕር ጋር የቀላቀሉት የእልፍ ኢትዮጵያን ጀግኖች ታሪክ በዛች ቅጽበት በአእምሮዬ ጓዳ ይመላለስ ገባ።

የእነ አሉላ አባ ነጋ፣ የእነ አፄ ዮሐንስ፣ የምኒልክ፣ የጣይቱ፣ የእነ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ የእነ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ የኤርትራውያኑ ወጣቶች የእነ አብረሃ ደቦጭና ሞገስ አስግዶም ወኔና ጀግንነት፣ እስከ ሮም አደባባይ የዘለቀው የኤርትራዊው የዘርዓይ ደረስ የኢትዮጵዊነት ብሔራዊ ኩራት፣ ወኔና ጀግንነት፣ በርካታ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ለአንድ እናት ምድራቸው ለእማማ ኢትዮጵያ ከከፈሉት ታሪክ በደም ቀለም ከተጻፈው የመሥዋዕትነት ታሪካቸው ጋር ለአፍታ መነጋገር ያዝኩ።

ኮሎኔሉ እንደ መርግ ከከበደ የዝምታቸው ዓለም፣ ከገቡበት ከትካዜያቸው ባሕር ተመልሰው ቀና ብለው አዩኝ። እኔም ከተፋጠጡኩበት የአገሬ የተዥጎረጎረ ታሪክ እውነታ ትውስታዬን ተሰናብቼ ወደ ኮሎኔል ካሣሁን ትረካ ተመለስኩ። ኮረኔል በናቅፋ ጦር ግንባር የነበረው ጦርነት እጅግ ከባድና ብዙ እልቂት የተፈጸበመት ነበር አሉኝ ወደኋላ በትዝታ ተጉዘው ያን ዘግናኝና አስከፊ እልቂት እያስታወሱ።

በዚህ በናቅፋ ግንባር ከሻቢያ ጋር በተደረገ ትንቅንቅ ኮሎኔል ዘጠኝ ቦታ መመታታቸውንና እስካሁንም ድረስ በክንዳቸውና በታፋቸው ላያ ያለው ጥይት አለመውጣቱን በሰውነታቸው ላይ ቀረውን ጠባሳቸውን እያሳዩኝ የናቅፋ ግንባር የጦርነት ውሎአቸውን ልብን በሚነካ ሁኔታ ተረካቸውን ቀጠሉልኝ።

የሻቢያ ሠራዊት ከናቅፋ ሰንሰለታማና ሹል ተራራ ላይ ሆኖ በኢትዮጵያ ጦር ማዘዣ ጣቢያ ላይ በከፈተው መጠነ ሰፊ ማጥቃትና የከባድ ጦር መሳሪያ ድብደባ በዚህ ግንባር የጦሩ አዣዥ የነበሩትና በጦር ሠራዊቱ ውስጥ እጅግ የሚከበሩትና ተወዳጅነት የነበራቸው ጄኔራል ይልማ ግዛው ጭንቅላታቸውን ተመትተው በናቅፋው የጦር ግንባር መሞታቸውን የነገሩኝ ከባድ ሐዘን በተጫነው የሰቀቀን ድምፅ ነበር።

ኮሎኔል ካሳሁን የቅርብ የሥራ ባልደረባቸውና ወዳጃቸው የነበሩትን፣ በናቅፋ የጦር ግንባር የተሠዉትን የኮረኔል መርሻ አድማሱን ሞት ሲተርኩልኝ ፊታቸው ላይ መረበሽና ጥልቅ ሐዘን እየተነበበት ነበር። የቅርብ የሥራ ባልደረባዬና ወዳጄ ኮ/ል መርሻ ከሻቢያ በተተኮሰ የሞርታር ጥይት ነበር ከወገቡ በላይ ተቆርጦ ደሙ ከላይ እየተንጠባጠበ በአየር ላይ ግማሽ አካሉ እየተንሳፈፈ ነፍሱ ያለፈችው አሉኝ፤ በዛን ፃእረ ሞትና የእልቂት መናፍስት የናኙበት በሚመስለው የናቅፋው ጦር ግንባር የሆነውንና የደረሰውን ዘግናኝ እልቂት ኮረኔሉ ሊያስታውሱት ባይወዱም በዓይነ ሕሊናቸው እየተመላለሰባቸው።

በጦሩ ውስጥ ከነበርን 12 ከፍተኛ መኮንኖች አሉኝ ኮረኔል ካሳሁን ከ12ቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች መካከል ተመትቼ በተአምር የተረፍኩት እኔ ብቻ ነበርኩ። ሌሎቹ ጓደኞቼ በሙሉ በዛ መቅሰፍት በሚመሰል የጦር ግንባር ውስጥ ነበር ያለቁት። በእርግጥም ይላሉ ኮ/ል ያን የእልቂ ቀን ሲያስታውሱት፡- ያ ቀን በኢትዮጵያ ጦር ላይ ለእልቂት የታዘዘ የመቅሰፍትና የመዓት ቀን ነበር የሚመስለው። በርካታ የደርግ የዘመቻ ካድሬዎችና መኮንኖች ያለቁበት ግንባር ነበር የናቅፋ ግንባር። ዋ ናቅፋ አሉ ኮሎኔል ሐዘንና ትካዜ በዋጠው ድምፀት …!!

ኮሎኔል በናቅፋ ግንባር ከተመቱ በኋላ ወደ አስመራ እቴጌ መነን ሆስፒታል በመሄድ በህክምና እርዳታ ከቆዩ በኋላ ለተጨማሪ ህክምና እና ከቤተሰባቸው ጋር ሆነው ለማገገም እንዲችሉ ፈቃድ አግኝተው ወደ ሐረር ነበር የተጓዙት። ከሐረር መልስም ወደ አዲስ አበባ መጥተው በ1972 ዓ.ም. በማእከላዊ የመረጃ መምሪያ መኮንን ሆነው ሥራቸውን ቀጠሉ። በማእከላዊም እስከ 1978 ዓ.ም. ድረስ መቆየታቸውን ነግረውኛል።

በ1978 የበላይ አለቆቻቸውና አንዳንድ የደረግ ካድሬዎች በመሰረቱባቸው ክስ የተነሣ የጦር ወንጀለኛ ተብለው በዓለም በቃኝ እስር ቤት እንዲታሰሩ ተወሰነባቸው። ኮረኔል ያን ጊዜ ሲያስታውሱት እጅግ ከባድና ፈታኝ ወቅት ነበር ይላሉ። ኮሎኔል በወቅቱ የተወነጀልኩት በሐሰት ነው በሚል ተደጋጋሚ ይግባኝ በማሰማታቸው ከሁለት ዓመት መራር የእስር ጊዜ በኋላ በነፃ እንዲወጡ ተደረገ።

ኮሎኔሉ ከእስር እንደተለቀቁም አለቃቸው ጄኔራል ኃይሉ ገ/ሚካኤል እንደገና ወደ ኤርትራ ሰሜን ግንባር ሄደው በአልጌና እንዲያገለግሉ ነበር ያዘዟቸው። ይህን የበላይ አለቃዬን ውሳኔ ይላሉ ኮሎኔል የምቀበለው አለመሆኔን ለጄኔራሉ በድፍረት ነገርኳቸው፤ እሳቸውም መልሰው ይህን ውሳኔ የማትቀበል ከሆነ ሥራህን በፈቃድህ እንደለቀቀክ ይቆጠራል የሚል ምላሽ ሰጥተውኝ፤ ከፈለግህ ግን ሃምሳ ዓመት ሲሞላህ ጠብቀህ ጡረታህን ማስከበር ግን መብት ነው በማለት በኃይለ ቃል ተናግረው አሰናበቱኝ።

ኮሎኔል ካሳሁን ለአለቃቸው ለጄኔራል ኃይሉ እኔ ገና በልጅነቴ ከ17 ዓመቴ ጀምሬ በውትድርና ዓለም በምስራቅና በሰሜን የጦር ግንባር በረሃ ለበረሃ ተንከራትቼ አገሬን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ያገለገልኩ ወታደር ነኝ። በዛ ላይ ዘጠኝ ቦታ ተመትቼ የቆሰልኩ ነኝ። በእስር ቤትም ውስጥ እያለኹ ባጋጠመኝ የአእምሮ ጭንቀት ተነሣ አእምሮዬ በትክክል አይሰራም ቢሉም ሰሚ አላገኙም ነበር። የነበረኝ ዕድል አሉ ኮሎኔል የነበረኝ ዕድል ለመከላከያ ሚ/ሩ ይግባኝ ማለት ነበር።

መከላከያ ሚ/ሩ ጄኔራል ኃይለ ጊዮርጊስ የህክምና ቦርዱ የፃፈውን የህክምና ወረቀቴን ካዩ በኋላ በ1981 ዓ.ም. ጡረታ ተብዬ ከሠራዊቱ አሰናበቱኝ። ከዛ በኋላ የጤናዬን ሁኔታ እየተከታተልኩ የተለያዩ መጻሕፍቶችን የመተርጎም ሥራ ውስጥ ነበር የገባሁት አሉኝ። በዚህ ሥራ ውስጥም እያሉ እንደገና ደረግ አባት ጦሮችን ለዘመቻ ክተት ሲጣራ በካራማራ ክፍለ ጦር ወታደራዊ መረጃ መኮንን ሆነው ተመደቡ። ግንቦት 19 ቀን ለሥራ ትፈልጋለህ ወደ አዲስ አበባ ና ተብዬ እንደመጣሁ ነበር በማግሥቱ ግንቦት ሃያ ወያኔ አዲስ አበባን የተቆጣጠረው።

የወያኔ ኃይል አዲስ አበባ ከተቆጣጠረ በኋላ የመከላከያ ኃይሉን ዳግም ሲያዋቅር አንዳንድ የጦር መኮንኖችን እንድናግዛቸው ባደረጉልን ጥሪ መሠረት እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ ደርግ ይሰጠን የነበረውን ደመወዝ እየከፈሉን ኢህአዴግን ሰራዊት የማደራጀት ሥራ በመሥራት በመከላከያ ሚ/ር መቆየታቸውን ነግረውኛል ኮሎኔል ካሳሁን። በወቅቱ የመከላከያ ሚ/ር የነበረው ጄኔራል ጻድቃን ገ/ተንሣይ እኛን ለጦራቸው ሲያስተዋውቀን የተናገረው ነገር አሁንም ድረስ ትዝ ይለኛል።

እንዲህ ነበር ያሉት ጻድቃን፣ ‹‹እኛ የምናውቀውና የተካነው የጫካ ውጊያን ነው፣ ከእነዚህ ሰዎች ደግሞ ሚሊታሪ ሳይንስ ምን እንደሆነ በሚገባ መማር ይገባናል።›› በማለት ከጦራቸው ጋር እርሳቸውንና ሌሎች የደርግ መንግስት መኮንኖችን እንዳስተዋወቋቸው ኮሎኔሉ ያስታውሳሉ።

ከ1987 ዓ.ም. በኋላ ኮሎኔል ሙሉ ጡረታቸውን ይዘው ከመከላከያ ተሰናበቱ። ከዚህ በኋላ ወደ መጻሕፍት ትርጉምና ወደ ግሉ ፕሬስ ነበር ፊታቸውን ያዞሩት። የተለያዩ ከውጭ አገር ሚመጡ ዜናዎችን በመተርጎም፣ የወቅቱን ዓለም አቀፍ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ የሚወጡ ጽሑፎችን በመተርጎም በታሪክ፣ በዓባይ፣ በኢትኦጵ፣ በማኅበራዊና በፍቀር ነክ መጽሔቶችና ጋዜጦች በነበሩት በቸኮሌት፣ በጣዕመ ፍቅር፣ ሆሊውድ ላይ በጸሐፊነትና በተረጓሚነት መሥራታቸውን ያስታውሳሉ።

በተለይ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በስፋት ይጽፉ በነበሩት በሚኒልከ፣ በዓባይ ጋዜጣ ላይ በሰፊው መስራታቸውንና ከምርጫ 97 በኋላ እነዚህ ጋዜጣዎች በመዘጋታቸውና ባለቤቶቻቸውም አንዳንዶቹ በመታሰራቸው አንዳንዶቹም ከአገር በመሰደዳቸው ምክንያት ከነጻ ፕሬስ ወጥተው በመጻሕፍት መተርጎም ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ነግረውኛል። ኮሎኔል በዚህ የመጽሐፍ መተርጎም ሥራ ላይ እስካሁን በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጠኑ ረጃጅም ከሃያ በላይ የሚሆኑ የልቦለዶ ሥራዎችን ለሌሎች ሰዎች በመተርጎም ለገበያ ማብቃታቸውን ይገራሉ።

ኮሎኔል ባለቤታቸው ከብዙ ህመምና ስቃይ በኋላ ከዚህ ዓለም ከሞት ከተለየዋቸው በኋላ፣ ከባለቤታቸው ዘመዶች ጋር መግባባት በመጥፋቱ የተነሣና እንዲሁም አእምሮቸው በመረበሹና ጤናቸው በመቃወሱ በጃን ሜዳ ከሚገኘው ቤታቸው ወጥተው በአዲሱ ሚካኤል አካባቢ ከአንድ ዓመት በላይ ለጎዳና ተዳዳሪነት እንደተጋለጡ ነው ያጫወቱኝ። በዳጃች ገነሜ ትምህርት ቤት አጥር ስር ሰዎች በሠሩላቸው እንደነገሩ በሆነ የላስቲክ መጠለያ ውስጥ ነበር ኮረኔልን ያገኘናቸው።

የአካበቢው ሰው ምንም እንኳን ስለማንነታቸው ምንም ባያውቅም በዕድሜዬ አረጋዊ መሆኔን እያዩ በማዘን ምግብ፣ ልብስና ገንዘብ በመስጠት በጣም ይረዷቸው እንደነበር ያታውሳሉ ኮሎኔል። በጎዳና ላይ በነበሩበት ጊዜ ኮሎኔል ከፍተኛ የሆነ የአእምሮ ጭንቀትና መረበሽ እንደነበረባቸውና በየቀኑም በርካታ ሲጋራዎችን ያጨሱ እንደነበር በመኝታቸው አካባቢ የተጣለው የሲጋራ ቁጥራጭና በመኝታቸው ስር ያገኘነው በርካታ የሲጋራ ባኮዎች ምስክር ናቸው።

ኮሎኔል ከአስከፊው የጎዳና ሕይወት በኋላ በቅርቡ የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ማእከል ባደረገላቸው ድጋፍ ወደ ማእከሉ መጥተው እንክብካቤ እያገኙ ነው። ኮሎኔል ካሳሁን ከነርቭ በሽታና በጎዳና ላይ ሳሉም ከነበራቸው ያልተመቻቸ ሕይወት የተነሣ በእግራቸው መሄድ አይችሉም፣ እናም የሚንቀሳቀሱት በዊልቸር ነው። ከዚህ ዘገባ በኋላ ከሰሞኑ በማእከሉ ተገኝቼ እንዳየኋቸው ኮሎኔል የተጎሳቆለ ፊታቸው ተመልሶ፣ የነተበና የቆሸሸ ልብሳቸውን ለውጠው፣ ፊታቸው ላይ ደስታና ፈገግታ ተረጭቶ ወንበር ላይ ተቀምጠው መጽሐፋቸውን እያነበቡ ነው ያገኘኋቸው።

ከጎዳና ሕይወት ወደ ተሻለ መጠለያ፣ ምግብ፣ ልብስና ሰብአዊ ፍቅርና እንክብካቤ ወደሚያገኙበት ወደእዚህ ዓይነት ማእከል በመምጣታቸው ኮሎኔል በእጅጉ ደስተኛ ናቸው። ኮሎኔል እንደነገሩኝ ማእከሉን በበጎ ፈቃደኝነት ከሚያገለግሉ የአማኑኤል ሆስፒታል የሳይካትሪስት ነርሶች ሙያዊ ምክርና እገዛ ማግኘታቸው ጥሩ የሆነ ስሜትን እንደፈጠረባቸውም አጫውተውኛል።

ኮሎኔል ካሳሁን ማእከሉን በበጎ ፈቃደኝነት የሚያገለግሉ ወንድሞችና እህቶች፣ እንዲሁም አንዳንድ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር ማእከሉን ለመጎብኘት የሚመጡ እንግዶች የሚያመጡላቸው መጻሕፍትና ጋዜጣዎች የአልጋቸውን ራስጌና ግርጌ ከበውት ነበር ያየኹት። ኮሎኔል በአሁን ሰዓት እነዚህ ሰዎች ያመጡላቸውን መጽሐፍት በማንበብ ላይ ነው በአብዛኛው የተጠመዱት።

በማእከሉ ባገኘኋቸው ጊዜ ኮሎኔል አሁን እንዴት ነዎት ብዬ ላቀርብኩላቸው ጥያቄ ሲመልሱልኝ ወንድሜ አሁን ደህና ነኝ፤ አእምሮዬም በጣም ደህና ነው። እንደበፊቱ ወደ ንባብና ትርጉም ሥራዬ እየገባሁ ነው በማለት ከሰሞኑ እያነበቡት ያለውን በእጃቸው የያዙትን Among the Russians የሚለውን መጽሐፍ አሳዩኝ። እንዴት ያለ ግሩም መጽሐፍ መሰለህ በሚል የአድናቆት ቃል እያነበቡት ስላለው መጽሐፍም በጥቂቱ አወጉኝ።

ባለፈው ሳምንት ‹‹አፍሪካን ኔግሮስ›› የሚል አንዲት ከአፍሪካ በባርነት ተሸጠው ከሄዱ ቤተሰብ የተወለደች የአፍሪካ አሜሪካዊት ሴት የሕይወት ታሪኳን የተረከችበትን መጽሐፍ በተመስጦ አንብበው እንደጨረሱትም ጨምረው ነገሩኝ።

ምናልባት አሉኝ ኮሎኔል ካሳሁን በቅርቡ በራሴና በመቄዶንያ ድርጅት ስም የሚታተም መጽሐፍ ለመተረጎም ዝግጅት ላይ ነኝ። አንዳንድ ነገሮችን እንድታግዘኝ ስለምፈልግ እንዳትጠፋ አሉኝ ፊታቸው በፈገግታ ፈክቶ። አልጠፋም ኮሎኔል ብቅ እላለኹ ብያቸው ተጨባብጠን ተለያየን። ኮሎኔል ወደፊት የሕይወት ታሪካቸውን ለመጻፍ እንደሚፈልጉና ለዚህም የሌሎችን ኢትዮጵያን ወገኖቻቸውን ድጋፍና እገዛ እንደሚፈልጉ ጨምረው ገልጸውልኛል። ወደፊት ኮሎኔል ካሳሁን የሕይወት ታሪካቸውን የሚተርክ መጽሐፍ ጽፈው እንደሚያስነብቡን አንዳች እርግጠኝነት በልቤ ውስጥ እየተሰማኝ ተሰናበትኳቸው። (ፍቅር ለይኩን)

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//naucaish.net/4/4057774