Press "Enter" to skip to content

አቶ ጌታቸው አሰፋ በሚያውቋቸው አንደበት

ስለ የቀድሞ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ የሚታወቀው ነገር እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ስለግለሰቡ መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ የቀድሞ የትግል አጋሮቻቸውን እና የሥራ ባልደረቦቻቸውን ጠይቋል። በተጨማሪም ከቢቢሲ ዜና ክትትልና ክምችት ክፍል ሞኒተሪንግ እንዲሁም ዊኪሊክስ ላይ የወጡ መረጃዎች ዋቢ ተደርገዋል።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት መረጃዎች የተሰበሰቡት ከቢቢሲ ሞኒተሪንግ ነው። ቢቢሲ ሞኒተሪንግ የብሪቲሽ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቢቢሲ አካል ሲሆን ከ1931 ጀምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃንን ዘገባዎች በመከታተል መዝግቦ ያስቀምጣል።

አቶ ጌታቸው አሰፋ 1940ዎቹ መጨረሻ ላይ በመቀሌ ከተማ፤ ቀበሌ 14 በተለምዶ ‘እንዳ አቦይ ፍቐዱ’ የሚባል ሰፈር ነው የተወለዱት። እስከ 8ኛ ክፍል እዚያው መቀሌ ከተማሩ በኋላ 9ኛ ክፍል ወደ አዲስ አበባ ሄዱ።

ትምህርታቸውን በዊንጌት ትምህርት ቤት መከታተል ጀመሩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማቋረጥ 1969 ላይ የትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ። ትጥቅ ትግሉን ከተቀላቀሉ በኋላ በመሪዎቻቸው አማካኝነት በመንግሥት ላይ ድንገተኛ ጥቃቶችን የሚሰነዝር ቡድንን እንዲቀላቀሉ ተደረጉ። ትግል ላይ በነበሩበት ወቅት አቶ ጌታቸው በአልታዘዝም ባይነታቸው እና ግትር አቋማቸው ሦስት ጊዜ ከደረጃቸው ዝቅ ተደረገው እንዲሠሩ ተደርገው ነበር።

1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው መመረጥም ችለው ነበር። የደርግ መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ፤ 1983 ላይ አቶ ጌታቸው በአገር መከላከያ ኃይል ውስጥ የኦፕሬሽን ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። ከአምስት ዓመታት በኋላ ደግሞ የፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል።

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ለሚሰበስቡት የመከላከያ ማእከላዊ እዝ አዛዥ ሆነው ተሹመውም ነበር። ግንቦት 1993 ላይ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ክንፈ ገብረመድህን መገደልን ተከትሎ አቶ ጌታቸው አሰፋ የደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሾሙ።

ይህ ሹመታቸውም የጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ቀኝ እጅ አድርጓቸዋል ተብሎ ይታመናል። አቶ ጌታቸው አሰፋ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይከሥልጣናቸው እንዲነሱ እስከተደረጉበት ዕለት ድረስ የደኅንነት መሥሪያ ቤቱን ለ17 ዓመታት ያህል አስተዳድረዋል።

አቶ ጌታቸው ለረዥም ዓመታት የመሩትን ተቋም ለጄኔራል አደም መሐመድ ካስረከቡ በኋላ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የክልሉ የደኅንነት አማካሪ አድርጎ ሹመት ሰጥቷቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ አቶ ጌታቸው በአሁኑ ሰዓት የሕወሃት እና የኢህዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው። አቶ ጌታቸው የሁለት ሴት ልጆች አባት ናቸው። አቶ ጌታቸው አሰፋ በህወሓት የትግል አጋሮቻቸው እና የሥራ ባልደረቦቻቸው አንደበት

ወላጅ አባታቸው ሻለቃ አሰፋ በንጉሡ እና በደርግ ዘመን የትግራይ ክፍለ አገር የስለላና ምርመራ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ነበሩ። ሻለቃ አሰፋ በደረግ አደረጃጀቶች ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት በመቀሌ ከተማ ውስጥ ተገድለዋል።

የአቶ ጌታቸው የትግል አጋሮች እንደሚሉት ከሆነ አቶ ጌታቸው በልጅነት ዘመናቸው ጠንካራ ተማሪ ነበሩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በማቋረጥ 1969 ላይ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር የትጥቅ ትግል ከተቀላቀሉ በኋላ አፋር ክልል ውስጥ ካዳሓራ በተሰኘ ሥፍራ ነበር ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱት።

1970 ላይ ህወሓት ውስጥ የተከሰተው ‘ሕንፍሽፍሽ’ እየተባለ የሚጠራው የመከፋፈል ክስተት ላይ አቶ ጌታቸው ‘ተሳትፈሃል’ ተብለው ለእስር ተዳርገው ነበር። በምሕረት ከድርጅቱ እስር ነጻ የወጡት አቶ ጌታቸው፤ ከደርግ ሠራዊት ጋር በተለያዩ የጦር ሜዳዎች ላይ መፋለማቸውን የትግል አጋሮቻቸው ይናገራሉ።

በትግል ወቅት አቶ ጌታቸው በብዛት ይሰጣቸው የነበረው ተልዕኮ መረጃ ማሰባሰብ፣ ማደራጀትና መተንተን እንደነበርም ይናገራሉ። በግትር አቋማቸው የሚታወቁት አቶ ጌታቸው በህወሓት ፖለቲካዊ ፕሮግራሞች ላይ ጠንካራ አቋም በመያዝ በተለያዩ ጊዜያት ከፓርቲው ለመገለል ቢቃረቡም፤ በቅርብ ጓደኛቸው አቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት በትግሉ እንዲቀጥሉ ይደረጉ ነበር።

ለምሳሌ እነ ዶክተር አረጋዊ በርሀ ከድርጅቱ ጋር የተቆራረጡበት የማርክሳዊ ሌኒናዊ ሊግ ትግራይ ማሌሊት ምስረታ መድረክ ላይ እሳቸውም ኣላመንኩበትም ብለው አቋም ይዘው እንደነበር ይነገራል። በአቶ መለስ አግባቢነት ነበር በአባልነት ሊቀጥሉ የቻሉት።

አቶ ጌታቸውም የደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ከሆኑ በኋላ፤ ወደመጨረሻ አካባቢ ከጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ጋር የነበራቸው መልካም ግንኙነት ባልታወቀ ምክንያት ሻክሮ እንደነበረ ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ።

ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ሕይወት በኋላም አቶ ጌታቸው በህወሓት ስብሰባዎች ላይ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ጠንካራ አስተያየቶችን ይሰነዝሩ እንደነበረ ይነገራል። የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ ሆነው የተመረጡበት 12ኛው የህወሓት ጉባኤ ላይ በድርጅቱ አመራር የሰፈነውን ሥርዓተ አልበኝነትና ሙስና ጠቅሰው አመራሩን በድፍረት ወርፈዋል ተብሎ ይነግርላቸዋል።

ከወራት በፊት ኢህአዴግ አካሄድኩ ባለው ጥልቅ ተሃድሶ ላይ ከግንባሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ እንደነበረ እርሳቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው የሥራ ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ።

አቶ ጌታቸው በሌሎች አንደበት ሕዳር 3 ቀን 2011 የሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታን በማስመልከት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ወንጀሉን በዋናነት የመሩትና በገንዘብ የደገፉት የብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ ኤጀንሲ የቀድሞው ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ናቸው ብለዋል።

አቶ አብዲ ሞሃመድ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሆነው ሳሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን የመጀመሪያዎቹን 100 ቀናት አስመልክቶ ሐምሌ 5 ቀን 2010 በሰጡት መግለጫ ላይ ስለ አቶ ጌታቸው አሰፋ ሲናገሩ ጌታቸው ሙሰኛ፣ ሌባ እና ራሰ ወዳድ ነው። አዲስ አበባ ላይ ተቀምጦ የክልል መስተዳድሮችን ይሾማል። ሲሉም ተደምጠዋል።

”አቶ ጌታቸው አሰፋ በርካታ ነጹሐን እንዲገደሉ፣ እንዲጠለፉ፣ እንዲሰቃዩ፣ እንዲጉላሉ፣ እንዲታሰሩ እና ከአገር ተሰደው እንዲሄዱ አድርጓል። በየትኛውም መስፈርት አቶ ጌታቸው ወንጀለኛ እና የሰብዓዊ መብት ጣሽ ነው”፤ ይህን ያሉት የቀድሞ የኮንግረስ አባል ማይክ ኮፍማን ለአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ማይክ ፖምፔዮ እና ለግምዣ ቤት ኃላፊው ስቲአ ሙንሽን ጥቅምት 13፣ ቀን 2010 በጻፉት ደብዳቤ ነው።

አቶ ጌታቸው በራሳቸው አንደበት ”የኤርትራ መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የተጣለበትን ማዕቀብ ተከትሎ፤ የኢትዮጵያ እና ሱዳን አዋሳኝ ደንበርን የአሸባሪዎች መፈንጫ ለማድረግ እየጣረ ነው” ይህን ያሉት አቶ ጌታቸው አሰፋ ናቸው በማለት የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ድረ-ገጽ ታህሳስ 2002 ላይ ጠቅሷቸው ነበር።

አቶ ጌታቸው በወርሃ ሰኔ አዲስ አበባ ላይ ከአሜሪካው ልዩ መልእክተኛ ዶናልድ ያማማቶ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝተው ተወያይተው ነበር። አቶ ጌታቸው “እንደ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር የመሰሉ ሰርጎ ገብ አማጺያን ዙሪያ አሜሪካ ያላትን አቋም ኢትዮጵያ ማወቅ ትሻለች” ብለዋቸው ነበር።

አቶ ጌታቸው አሰፋ በዊኪሊክስ ሰኔ 1፣ ቀን 2001 ዓ.ም አቶ ጌታቸው አሰፋ በወቅቱ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ከነበሩት ኢረቭ ሂክስ ጋር ለአራት ሰዓታት የቆየ ውይይት አድርገው ነበር።

በውይይታቸው ወቅት የኦነግ እና ኦብነግ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ውስጣዊ ደኅንነት አስጊ ስለመሆኑ፤ የአሜሪካ ድምጽ ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ፣ የቀድሞ የህወሓት አባል እና የመከላከያ ሚንስትር የነበሩት የአቶ ስዬ አብረሃ በተቃዋሚነታቸው ውስጥ ተጽእኖ ፈጣሪነታቸው እየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰባቸው ለአምባሳደሩ መግለጫቸው ዊኪሊክስ አሳውቋል።

በተጨማሪም አቶ ጌታቸው ምርጫ 97ን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሆነው ተሹመው የነበሩትን ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ”ጽንፈኛ” ብለው መጥቀሳቸውን ዊኪሊክስ አጋልጧል። አፈትልከው የወጡ የዊኪሊኪስ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አቶ ጌታቸው አሰፋ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት አይዋጥላቸውም ነበር።

ጥቅምት 26፣ ቀን 2002 አቶ ጌታቸው አሰፋን የያዘ በወቅቱ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር በነበሩት በአቶ ስዩም መስፍን የሚመራ የልዑክ ቡድን ወደ አሜሪካ አቅንቶ ከውጪ ጉዳይ ሚንስትሯ ሂላሪ ክሊንተን ጋር ተወያይቶም ነበር።

በውይይቱ ላይ የጸጥታ ትብብር፣ ዲሞክራሲዊ አስተዳደር እና የምጣኔ ሐብት ሪፎርም ጉዳዮች ለውይይት ቀርበው የነበረ ሲሆን፤ ሂላሪ ክሊንተን የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት ለኢትዮጵያ ሌላ ጫና እንደሆነ በመጥቀስ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የጸጥታ ትብብር አድንቀዋል ይላል፣ ዊኪሊክስ።

ሂላሪ ክሊንተን ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ላቀናው የኢትዮጵያ ልዑክ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሶማሊያ ጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ስልጠናዎችን እንዲሰጥ እና ለሶማሊያ የሽግግር መንግሥት የማይቋረጥ ድጋፍ እንድትሰጥ አሳስበዋል ይላል ዊኪሊክስ። ምንጭ ቢቢሲ አማርኛ ከሶስት አመት በፊት ያወጣው

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//phaurtuh.net/4/4057774