ህወሓት በሥልጣን ዘመኑ የፈጠረው መርህ አልባ ግንኙነት የምዕራቡ ዓለም ጫና እንዲበረታ ምክንያት ነው – አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ

ህወሓት በሥልጣን ዘመኑ የፈጠረው መርህ አልባ ግንኙነት አሁን የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ጫናውን እንዲያበረታ ምክንያት መሆኑን የኢሳት ጊዜያዊ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና ፖለቲከኛ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አስታወቁ፡፡ ጫናውን ለመቋቋም በጋራ መቆም እንደሚገባ አሳሰቡ።

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ መንግሥት በህወሓት ላይ ሕግ የማስከበር እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ የምዕራቡ ዓለም መንግሥታትና ከነሱ ጋር ቅርበት ያላቸው ተቋማት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እውነታ አጣመው በማቅረብ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

የምዕራቡ ዓለም መንግሥታትና ከነሱ ጋር ቅርበት ያላቸው የፋይናንስ፣ የሰብዓዊ መብትና የሚዲያ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድሩ የሚገፋፋቸው በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው፤ ከነዚህ ምክንያች አንደኛው የሕግ ማስከበር እርምጃ የተወሰደበት አካል በመንግሥትነት ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከምዕራቡ ዓለም መንግሥታትና ተቋማት ጋር የነበረው ግንኙነት ነው ብለዋል።

እርምጃ የተወሰደበት አካል ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እና ጋዜጠኞች፣ በአገራት መንግሥታት ላይ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም ካላቸው ተማፃኞች (ሎቢስት) እንዲሁም ከደህንነት ሰዎች ጋር መርህ ላይ ያልተመሰረተ ግንኙነት እንደነበረው አንስተዋል።

እነዚህ አካላት በአሁኑ ወቅት ያልተጨበጡ መረጃዎችን ሆነ ብለው ማሰራጨታቸው የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ጫናውን እንዲያበረታ ምክንያት መሆኑን እንዳመለከቱ የኢፕድ ዘገባ ገልጿል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *