ጩኸታቸውን የተዘረፉ ወገኖች – የትግራይ ወጣት ሴቶች

በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ሽረ ከተማ ውስጥ እየተንቀሳቀስን ሳለ ሁለት የትግራይ ወጣት ሴቶች ፈራ ተባ እያሉ ተጠጉን። እነኛ ከየትኛውም የሀገራችን ጥግ የመጣን ወታደር የወንድም ያህል በፍቅር የሚቀርቡት የትግራይ ሴቶች ጁንታው በሰራው ፀያፍ ተግባር በሙሉ አይናቸው እንኳን እኛን ለማየት ሲቸገሩ ስናይ ለነሱ ሀፍረት መልሰን እኛው አዘንን።

የወጣትነት ዕድሜያቸውን በትግራይ ክልል ምሽጎች ውስጥ የሳለፉት ሀገር ለመጠበቅ ሲሉ በብዙ ድካምና እንግልት ውስጥ ያለፉት የህዝብ ልጆች በጁንታው ከታፈኑ በኋላ ሚሊቴሪ እንደለበሱ በጭነት መኪና ተጭነው በዚህችው ሽረ ከተማ ውስጥ በየነዋሪው በራፍ መኪናው እየቆመ በህዝቡ ፊት ለአህዮች እንጀራ አዋጡ አየተባለ እንደተለመነባቸው ስለሰማን የሀፍረታቸው መነሻ ምን እንደሆነ መገመት አልቸገረንም።

ግና እኛ ፀባችን የሀገራችን ነቀርሳ ከነበረው ምናልባትም ዛሬ ራሱ ቁርጥ ስሟ ከአፉ እንደማትጠፋው እንሰሳ መሬት ከሚንደባለለው ጁንታውና አስተሳሰቡ ጋር ብቻ ነበረና ሀፍረታቸውን በፍፁም ፈገግታና ቅን ልብ ሰበርነው።

እህቶቻችን ምን እንታዘዝ? ምን እናግዛችው? ስንልም ጠየቅናቸው። የቀረቤታችንን ወንድማዊነት የተረዱት እንስቶቹ አንዲት የወለደች አራስ ጓደኛእንዳለቻቸው ነገር ግን ቤቷም ቤታቸውም ባዶ እንደሆነና የገንፎ እህል እንኳን እንደቸገራት ነገሩን። እስኪ መላ አምጣ በሚል አይነት አተያይ ጓደኛዬን ዞር ብዬ አየሁት። በዛው ቅፅበት ከአራት ቀን በፊት ያየነውን አንድ የጁንታው ልዩ ሀይል ዱቄት የተከማቸበት መጋዘንን አስታወሰኝ።

ወዲያዉኑም ለልጆቹ ተስፋ የሚሰጣቸውን ነገር ነግረን የምዕራቡን ግንባር ሎጀስቲክስ ወደ ሚመራው ጄነራል መኮንን አመራን። ጄነራል መኮንኑ ለሰማነው ነገር ስንነግራቸው ከልብ አዝነው ወዲያውኑ ሽረ ከተማ የጁንታው ልዩ ሀይል አከማችቶት የነበረው ዱቄት በሙሉ ወጥቶ ለችግረኞች እንዲከፋፈል አደረጉ

ይህ በጁንታው ልዩ ሀይል የተከማቸ ዱቄት ከዚህች አራስ ጀምሮ ከየቤቱ በማስፈራራት የተሰበሰበ ነው። ማን ያውቃል ምናልባትም ይህቺ ሴት ጓደኞቿ ለልመና የወጡላት ከዚሁ ክፍፍል ውስጥ የራሷን ሀቅ ያክል ለማግኘትም ይሆናል።

ደግሞም ይህም ባልከፋ ነበር። እንዲህ እንደዛሬው ለእርዳታ እጁን የሚዘረጋ በጎ አድራጊ ባልነበረበት በዚያን ጊዜ መከላከያው ህግን ከማስከበር ስራው ጎን ለጎን ወገናዊነት ተሰምቶት እንደ አራሷ አይነቶችን ለመርዳት እጁን በዘረጋ ጊዜም ፤ ጁንታው በከተማ ውስጥ አስፈፃሚዎቹ አማካኝነት ችግረኛ መስሎ ገብቶ ድጋሜ ከአፋቸው ነጥቆ መውሰዱ ነው ሌላው ጭካኔ።

እዚሁ ሽረ ከተማና አካባቢው ላይ ማህበረሰቡ ቢያንስ በቀን ሁለት ሌባ እየያዘና ከተማ ውስጥ የአህያ ጋሪ እያስጎተተ ሲያስዞርም በተደጋጋሚ ተመልክቻለሁ። እነኚህ እጅ ከፍንጅ የሚያዙ ወንጀለኞች መነሻቸው የት እንደሆነም ጠይቀን አብዛኞቹ የሚያውቋቸውና በተለያየ ጊዜ ወንጀል ሰርተው በህግ ቁጥጥር ስር የነበሩ ስለመሆናቸው ራሱ ማህበረሰቡ ነግሮናል።

በጊዜውም እኔና ጓደኛዬ ሰው እንዴት የገዛ እናቱን ቤት ለማስዘረፍ ወንጀለኛን ፈቶ ይለቃል? ስንል በግርምት ጠይቀናል። ኋላም ላይ የአስገድዶ መድፈር ሙከራውና የስርቆት ወንጀሉ ሲበረታ ይኸው የሽረና የአካባቢው ነዋሪ ተወካዮችን በመምረጥ ለሰራዊቱ አመራሮች ይህ መልዕክት እንዲደርስ አድርጎ ነበር

በወንጀለኞች እየተደፈርን ያለነው መከላከያው ከከተማ ውጪ እንጂ ከተሞች ውስጥ አይንቀሳቀስም ተብሎ ነው እባካችሁን አንድም ሁለትም ቢሆን ወታደሮችን መድቡልንና ሰፈር ውስጥ አብረን እየዋልን አካባቢያችንን በጋራ እንጠብቅ

እኔ አሁን ያንን ስፍራ ለቅቄ ወጥቻለሁ ። በወቅቱ ከሰራዊቱ አመራሮች እኛ ስራችን የእናንተን ሰላም መጠበቅ ነው” አብረን እንሰራለን የሚል መልስ እንደሰጧቸው ባውቅም ተግባራዊ ሲሆን የማየት ዕድሉ ግን አልገጠመኝም ።

ብቻ ግን የገንፎ እህሏን በጁንታው ሰዎች የተነጠቀችውን አራስ መቼም አልረሳትም። ደግሞም ያ ሁሉ አልበቃ ብሎ ይህችው ሴትና ሌሎች ልዩ ልዩ ችግሮች የገጠማቸው ወገኖች በየማህበራዊ ሚዲያው ጩኸታቸውንም በጁንታው ርዝራዦች ተዘርፈው ሳይ ይበልጥ አዘንኩ።

ለመሆኑ ከበደሉ ወዲያም የተበዳይን ጩኸት ቀምቶ መጮህን እንደ ጁንታውና ናፋቂዎቹ የተካነበት በምድራችን ላይ ይኖር ይሆን? እንጃ! ሻምበል ነፃነት ሸዋንግዛው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *