ጀርመንና አስደናቂዋ መሪ አንጌላ ማርኬል

ረጃጅም ህዝቦች ናቸው፡፡ በራስ መተማመናቸው ድንቅ ነው፡፡ ዓለምን ጠፍጥፎ የመስራት ብዙ አጋጣሚዎችን አግኝተዋል፡፡ እሱንም በሚገባ ተጠቅመው በታል። ከባድ ተፅህኖ ፈጣሪዎች ናቸው፣ 99% የሚሆነው ህዝባቸው በደንብ ቀጥቅጦ የተማረ ነው፣ በአውሮፓ ቁጥር አንዱን እና በዓለማችን ደግሞ አራተኛውን ግዙፍ ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱት እነሱ ናቸው፣ ለታሪካቸው የሚሰጡት ግምት የሚደንቅ ነው። የዓለማችን ቁጥር አንድ አሳቢዎች ጠበብቶች፣ ገጣሚዎች፣ ሰአሊዎች፣ የሂሳብ እና ፊዚክስ ሊቆች እና ፈላስፎች ናቸው።

እራስህን ሲያምህ የምትውጠው አስፕሪን የነሱ ነው፡፡ የቡና ማጣርያ ማሽንህ የነሱ ነው፡፡ የምንጠቀምባቸው ማተምያ ማሽኖች የእነሱ ፈጠራ ነው፡፡ እኤክስ ሬይ ማሽኖቻችን የነሱ ናቸው፡፡ የምንለብሳቸው ጅንስ ሱሪዎች መነሻቸው ከነሱ ነው፡፡ ጥርስህን የምታፀዳበት የጥርስ ሳሙና ሳይቀር የነሱ ፈጠራ ነው፡፡ እንደ ተራ ነገር በማርቸዲስ ታክሲዎች እና የህዝብ ባሶች የምትሄደው እነሱ ሃገር ነው። የምታደርጋቸው የአዲዳስ እና ፑማ ምርቶች የነሱ ናቸው፡፡ የምትቀባው “ሁጎ ቦስ ሽቶ የነሱ ነው። ቮልስ ዋገን፣ ቢኤም ደብሊው፣ ማርቸዲስ፣ አውዲ እና ፖርሽ የሚባሉ ድንቅ መኪናዎችን ለዓለም ያበረከቱት እነሱ ናቸው፡፡

ታላቁን የሙዚቃ ሊቅ ቤትሆቨንን የሰጡን እነሱ ናቸው። የሪላቲቪቲ ቲዎሪን ሰጥቶን ዓለምን የቀየረው አልበርት አንስታይን የነሱ ዜጋ ነው። ታላቁን ፈላስፋ ኢማኑኤል ካንትን የለገሱን እነሱ ናቸው። ዓለምን በፖለቲካዊ ርዕዮተ ዓለም ፍልስፍናቸው የናጡት ካርል ማርክስ እና ፍሬድሪክ ኤንግልስ እና የነሱ ስጦታዎች ናቸው። በርግጥ አዶልፍ ሂትለር ወደ 6 ሚልዮን አይሁዳዊያንን አስገድሎ አሸማቋቸዋል፣ ታሪካቸውም ላይ ጥላሸት ቀብቷል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ቆሻሻ ታሪካቸው ተምረውበት አልፈውታል፡፡ በዚህች ሃገር ይህንን ታሪክ “አልተፈፀመም” ብሎ መከራከር እና መካድ ብቻ ከፍተኛ ወንጀል ሆኖ እስከመደንገግ ደርሷል፡፡

ህዝባቸው ገራሚ ነው። ቢራ እንደ ውሃ የሚጠጣባት እና ከ 5000 በላይ የተለያዩ የቢራ አይነቶች ያሉባት የጉድ ሃገር ናት። አንድ የነሱ ሃገር ዜጋ በአማካይ በአመት እስከ 100 ሊትር ቢራ ይጠጣል፡፡ ጠጪዎች ብቻ ግን አይደሉም!ለዓለም ባበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ 108 የኖቤል ሽልማት ተሸላሚ ዜጎች ያሏት ብቸኛ ሃገር ናት። ህዝቦቿ የዓለማችን ቁጥር አንድ ቀጠሮ አክባሪዎች ናቸው፡፡ ማንበብ ባህላቸው ነው። 2000 መፅሃፍ አሳታሚ ድርጅቶች ያሉት እዛ ነው፡፡ ከ”94 ሺህ” በላይ መፅሃፎች በየዓመቱ ለህትመት የሚበቁባት ሃገር ናት። 50% የሚሆኑት ህዝቦቿ በትንሹ በሳምንት ውስጥ አንድ መፅሃፍ አንብበው ይጨርሳል፡፡

እነዚህ ሁሉ አሳቢዎች፣ ጠበብቶች፣ ገጣሚዎች፣ ሰአሊዎች፣ የሂሳብ እና ፊዚክስ ሊቆች፣ ፈላስፎች፣ ሙዚቀኞች፣ ኢንጅነሮች፣ አርክቴክቶች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ዶክተሮች እና ኢኮኖሚስቶች የነበሯት እና ያሏትን ድንቅ ሃገር የምትመራው ሴቷ ደግሞ የ”German” መራሂተ መንግስቷ ወይም ቻንስለር አንጌላ ማርከል ናት፡፡

አማርከል እናት ናት። ጀርመናዊያን ሙቲ እያሉ ይጠሯታል፡፡ “እናት” እንደማለት ነው። ቆራጥ ናት፣ የውሳኔ ሰው ናት፣ ታጋሽ ናት፣ ቅን ናት፡፡ የተማረችው ብዙዎች እንኳን ሊደፍሩት ሊያስቡት እንኳን የማይፈልጉትን “Physics” ነው፡፡ ከዛም እጅግ ውስብስብ እና ከባድ የሚባለውን “ኳንተም ኬሚስትሪ ተምራ ዶክትሬቷን መውሰድ የቻለች ብርቱ ሴት ናት። ማርከል በፎርብስ መፅሄት ብቸኛዋ በተለያዩ አመታት ለ12 ግዜ “የዓለማችን ቁጥር አንድ ተፅህኖ ፈጣሪ ሴት” መሆን የቻለች ሴት ናት። የሴትየዋን ታላቅነት መስክረው 10 ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬቶችን ሰጥተዋታል። ጀርመን የአውሮፓ ተፅህኖ ፈጣሪ ሃገር መሆኗን በማስቀጠሏ ብዙዎች ሴትየዋ የጀርመን መሪ ብቻ ሳትሆን የአጠቃላይ አውሮፓ አለቃ ናት ይሏታል።

አምስት የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚንስትሮች ሲሰናበቱ እሷ አለች፣ አራት የፈረንሳይ ፕሬዝዳንቶች መጥተው ሲሄዱ እሷ አለች፣ ሰባት የጣልያን ጠቅላይ ሚንስትሮችን ሸኝታለች፡፡ አሁን ደግሞ ከአራተኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጋር እየሰራች ነው፡፡ ለ16 ዓመታት የጀርመን ቻንስለር ሆና መቆየት የቻለችው ብቸኛዋ ሴት አንጌላ ማርኬል የዲፕሎማሲ ጥበብን እና የድርድር ብቃትን የተካነች ናት። እብዱን ትራምፕ እና መሬውን ፑቲን በብልሃት ማስተናገድ በራሱ ከባድ ስራ ነው። እሷ ግን ችላዋለች! እሱ ብቻ አይደለም፡፡ ወደ ስልጣን በመጣችበት ወቅት የሃገሪቷ ኢኮኖሚ ተዳክሞ ወደ ቀውስ እየተንደረደረ እና የስራ አጥ ቁጥሩ ከ 11% በላይ አሻቅቦ ነበር፡፡ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በብልሃት መምራት በመቻሏ አሁን ላይ ጀርመን ውስጥ የስራ አጥ ቁጥሩ ከ 3.2% በታች ነው፡፡ ሃገሪቱም የአውሮፓ ቁጥር አንድ ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆን ችላለች፡፡ 74% የሚሆነው የጀርመን ህዝብ በሴትየዋ ደስተኛ ነው፡፡ በሃገሪቱ የተቀጣሪ ሰራተኞች ዝቅተኛ የክፍያ ጣራ (Minimum wage) “1498 ይሮ” ደርሷል። በኛ እንዳታሰላው አባዬ፡፡

በቀን ለአራት ሰዓታት ብቻ እንቅልፍ እንደምትተኛ የምትናገረው “Angela Merkel” ውሳኔ ለመወሰን ትዘገያለች ተብላ ስትወቀስ “ብዙ ሰዎች ውሳኔ አሰጣጥ ላይ ትዘገያለች፣ ብዙ ግዜዋን በማሰብ ታጠፋለች፡፡ እያሉ ይወቅሱኛል፡፡ ያልገባቸው ውሳኔ መስጠት ቀላል አይደለም፡፡ ብዙ ግምቶችን አስቀድሜ እወስዳለው፡፡ ብዙ አሰላስላለሁ፡፡ ብዙ አስብበታለሁ፡፡ ከዛ በኃላ ግን የምወስነው ውሳኔ አንድም ግዜ ስህተት ሆኖ አያውቅም፡፡” ትላለች፡፡

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2015 ላይ ብዙ የአውሮፓ ሃገራት ለስደተኞች በራቸውን ሲዘጉ ሴትየዋ ግን “ጀርመን ሁሌም ለስደተኞች በሯ ክፍት ነው፡፡” በማለት ወደ 900 ሺህ ስደተኞችን በአንድ አመት ውስጥ ብቻ የተቀበለች ሰው ናት፡፡ ከዛም አልፋ የዲፕሎማሲ ብቃቷን በመጠቀም ብዙ የአውሮፓ ሃገራትን አሳምና ስደተኞችን እንዲቀበሉ አድርጋለች፡፡ አሁን ላይ በአጠቃላይ ከ1ነጥብ3 ሚልዮን በላይ ስደተኞች ጀርመን ውስጥ ይኖራሉ፡፡

አንጌላ ማርኬል ያልተፃፉ ህግች አሏት ይባላል፡፡ የመጀመርያው እና ከሁሉም የሚበልጠው ህጓ እምነት ነው። አጠገቧ ያሉ ባለስልጣናት መታመን አለባቸው። ከሷ እውቅና ውጪ የሃገርን ጉዳይ አንጠልጥሎ ወደ ሚድያ መውሰድ ወይም ቃለ መጠይቅ መስጠት አይቻልም፡፡ ይሄንን ካደረክ ድጋሚ አጠገቧ ላትገኝ ትችላለህ፡፡

ይህንን የሚያክል ትልቅ ሃገር፣ ትልቅ ኢኮኖሚ እና ትልቅ ህዝብ የምትመራው አንጌላ ማርኬል የምትኖረው እንደ ተራ ዜጋ ነው። መኮፈስ፣ መጀነን፣ ማጌጥ፣ መልበስ ምናምን አይመቻትም፡፡

ስልጣን ስትይዝ ከአሜሪካው ኋይት ሀውስ ሁለት እጥፍ የሚበልጥ የተንቆጠቆጠ ቤተ መንግስት ውስጥ እንድትኖር ጥያቄ ቢቀርብላትም አሻፈረኝ ብላ በፊት ትኖርበት የነበረው መንደር ውስጥ የሚገኝ አንድ ተራ አፓርትመንት ውስጥ ብዙም የጥበቃ ጋጋታ ሳይኖር መኖርን መርጣለች፡፡ መኖርያ ቤቷ አካባቢ የሚገኙ ሱፐርማርኬቶች ውስጥ በነፃነት ገብታ ዳቦ፣ ወተት፣ ቡና ምናምን ስትገዛ ልታያት ትችላለህ! ሴትየዋ “ቤተ መንግስት ውስጥ ለምን አትኖሪም?” ስትባል “ህዝብ አገልጋይ እንጂ ንግስት አይደለሁም” ትላለች፡፡

ታዋቂው ጀርመናዊ ዲዛይነር ካርል ለገርፊልድ ሴትየዋን “አብዛኛውን ግዜ የምትለብሳቸው ልብሶች ለወንድ የተሰሩ ነው የሚመስሉት ሱሪዎቿ ሰፊ እና ረጅም ከመሆናቸው የተነሳ መሬት ላይ ይጎተታሉ! የልብሶቿን ቀለም ምርጫዎች አታውቅም፡፡ ክፈይኝና እኔ የግል ዲዛይነርሽ ልሁን ብዬ ስጠይቃት “እኔ ብዙ የማስቀድማቸው ጉዳዮች አሉኝ፡፡ አንተ ያልከኝ ከነዚህ ቅድሚያ ከምሰጣቸው ጉዳዮች ዝርዝር ውስጥ የለም ብላ መልሳኛለች” ይላል፡፡

ሴትየዋ እጅግ ድብቅ የግል ህይወት ነው ያላት፡፡ ከ20 አመታት በላይ በትዳር አብራው ያለችው ባለቤቷ አንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ፕሮፌሰር ሲሆን እሱም በኳንተም ኬሚስትሪ ዶክትሬቱን ሰርቷል፡፡ ሚድያ ላይ መታየት ካለመፈለጉ የተነሳ ባዕለ ሲመቷ ላይ ሳይቀር አልተገኘም፡፡ አንድም ቃለ መጠይቅ ሰጥቶም አያውቅም፡፡ አብሯት በአንድ አውሮፕላን እንኳን አይሄድም፡፡

አንጌላ ማርኬል ደሞዟ እንደ አንድ ሃገር መሪ የተካበደ አይደለም፡፡ እንደውም ከአብዛኛዎቹ የአውሮፓ መሪዎች ያነሰ ነው፡፡ ልታይ ልታይ ማለት ከመጥላቷ የተነሳ ማህበራዊ ሚድያ ላይ እንኳን ብዙም የለችም፡፡ (ተጻፈ በወንድዬ እንግዳ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *