ኢትዮጵያዊ ፌሚኒዝም

ሴቶች እንኳን ለሴቶች ቀን አደረሳችሁ ይሄን ፅሁፍ ስታነቡ አንዳንዶቻችሁ ፈገግ ሌሎቻችሁ ኮስተር እንደምትሉ አውቃለሁ እነሆ ቆምጠጥ ያለ መልዕክት አለኝ! ብዙ ሰዎች ፌሚኒስት ነሽ ብለው ይጠይቁኛል አይደለሁም ሴት ነኝ ያውም ብርቱ ሴት ብርታቴን ለማሳየት ከማንም ጋር ሳይሆን ትላንትናዬን ከዛሬ ጋር ዛሬዬን ደግሞ ከመድረሻዬ ጋር እለካለሁ!

ለኔ ምሳሌ ሴት ማለት በሁሉም የህይወት ዘርፋ የላቀች ችግሮችን ወደ ከፍታዋ ለመድረስ የምትጠቀም የራሷን ሩጫ የምትሮጥ ከውጫዊው አካሏ በላይ ለውስጣዊ ማንነቷ እጅግ የምትጠነቀቅ!

ለልጆቿ ምክር ሳይሆን አርአያ ፣ለባሏ ህልሙ እውን እንዲሆን የምታግዝ #ረዳት፣ ለማህበረሰቡ የለውጥ ሀሳብ ምንጭ፣ እለት እለት በሙያዋ ፣በእውቀቷ፣ በመንፈሳዊ ህይወቷ ለማደግ የምትታትር ሴት ናት!እኩል አይደለሁም!

በፈሳሽ መለኪያ(በሊትር) ሙቀት እንደማይለካው በሚዛን በኪሎ መንገድ እንደማይሰፈረው እኔ ከወንድ ጋር ራሴን የማነፃፅርበት ሚዛን የለኝም ሴትን ልጅ መደገፍ የሚገባው ከወንድ እኩል ለማድረግ ነውን?

ሴት ልጅ እድል ስታገኝ ስትማር ስትሰራ ታኮራለች በዙሪያዋ ያሉትንም ታሸንፋለች ! በየትኛውም መለኪያ ቢለካ ግን ሴት በአለም ላይ በስራዋ ወንዶችን ሁሉ ብትበልጥ በቤቷ ውስጥ ግን ከባሏ ልትበልጥ ወይም እኩል ልትሆን አትችልም የእኩልነት ሀሳብ ወደ ትዳር ውስጥ ሲገባ የማያሻግተው እንጀራ አይኖርም

በአንድ መኪና ላይ መሪ ከሌለ መኪና አይነዳም ነገር ግን ሞተር ይቅርና ሁለት መሪ ይሁን አይባልም ወይም አንድ ቦታ ለመድረስ ፍትሀዊ እንዲሆን ለአንድ መኪና ሁለት ሹፌር እና ሁለት መሪ ይሁን እንደማይባል በሁለት ሰዎች ፍቅር እና ስምምነት የተመሰረተ ትዳር ሁለታችንም ትዳሩን እኩል ልንነዳ ይገባል በሚል ሀሳብ መሪው እንዳይበጠስ ልንጠነቀቅ ይገባል

አልበልጥም አላንስም እኩልም አይደለሁም! ሴቶችን ለማበርታት እና እነሱን ከብዙ ጥቃቶች ለመጠበቅ መብታቸውን ለማስከበር ውስጣቸው ያለውን ሀይል አውጥተው አንዲጠቀሙ ማድረግ ፤ምሳሌ የሚሆኑ ሴቶችን መደገፍ እና ህብረተሰቡን ማስተማር ብሎም ህግ ማስከበር መልካም ነው!

በሴቶች መብት እና እኩልነት ሰበብ ብዙ ሴቶች ያለባል ልጅ ማሳደግ እንደሚችሉ ትዳር ባይኖራቸውም ብቸኛ እናት መሆን ቀላል እንደሆነ ሲያወሩ እሰማለሁ

በቤት ውስጥ ሴት እናት እንጂ አባት መሆን አትችልም! ብቻዋን ማሳደግ እንጂ ብቻዋን ልጅ በፅንሷ መፍጠር አትችልም አንበሳ፣ጦጣ አሳ እባብ ደርድረን ውድድሩ ፍትሀዊ እንዲሆን ዛፍ ላይ ቀድሞ የወጣ ያሸንፋል ብለን ፊሽካ ብንነፋ ውድድሩ ፍትሀዊ ሊሆን አይችልም ሁላችንም ልንሮጥ የሚገባው በራሳችን የመሮጫ ትራክ ላይ ነው!

ፌሚኒዝም “ሴቶች ከወንዶች ዕኩል መብት እና ዕኩል ዕድል እንዲያገኙ የሚጥር እንዲሁም ደግሞ የሚደርስባቸውን ጥቃት ለማስቆም የሚደረግ እጅግ መልካም እና ጠቃሚ ንቅናቄ ነው

ሆኖም ግን ይሄ ንቅናቄ ልክ በብሄርተኝነት እና በዘር እንደሚታየው ፅንፍ ጥግ ይዞ ለሴቶች መብት የሚመስል ግን ሀገርንም ዜጋንም የማይረዳ እና የማይበጅ የፆታ አክራሪነት ሲመስል አልፎ አልፎ አየዋለሁ!

ይሄ የተጨቋኝ እና የጨቋኝ አስተሳሰብ ያለው ደግሞ በሁለቱም ጾታ አስተሳሰብ ውስጥ በመሆኑ እንደ ሀገር እንደ ማህበረሰብ ሊሰራበት የሚገባ የአስተሳሰብ ችግር ሆኖ አግኝቼዋለሁ አንድ ሰው እንዳለ

“አንዳንድ ‹ፅንፈኛ ፌሚኒስቶች›፣ የፆታ መድልዖን ሲተረጉሙት በመደብ ይለዩታል፤ ‹ወንዶች ጨቋኝ መደብ፣ ሴቶች ተጨቋኝ መደብ ናቸው› በማለት፡፡ መፍትሔው ጨቋኙን መደብ መታገል ይሆናል፡፡ ሴቶች ወንዶችንም ሴቶችንም ጠቅልለው መግዛት ካልጀመሩ ለውጥ እንደማይመጣ የሚናገሩ አሉ፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሴትን ያሳንሳል ብለው ያሰቡትን አቀራረብ በመቀየር የሴቷን መጽሐፍ ቅዱስ (Woman’s Bible) ያዘጋጁ ሴቶች አሉ፡፡ ባስ ሲል ከወንድ ዕኩል የማያየኝን ሃይማኖት አልቀበልም በሚል ሃይማኖታቸውን እርግፍ አድርገው የተዉ አሉ ከዛም አልፎ ከወንድ ጋር አልተኛም እስከሚሉ ‹ፅንፈኛ ፌሚኒስቶች› አሉ”

ለማንኛውም ለኔ ምሳሌ ሴት ማለት ወደ የትኛውም የሀሳብ ፅንፍ እና ጨለማ ውስጥ ያልገባች አስተዋይ አመዛዛኝ ብልህ እና አርቆ አስቢ ሴት ናት አንቺ ብርቱ ሴት ውስጥሽ ያለውን ታላቅነት አውጥታሽ ለብዙዎች አንድታበሪ ውስጣዊ ማንነትሽ ላይ ብዙ ስሪ አታንሺም አትበልጪም አኩል አይደለሽም
ሀና ሀይሉ (ሀና ሀይሉ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *