“አያቶቻችንን ያስከበራቸው፣ ኢትዮጵያ ከቡድን ፣ ከግለሰብ እና ከፖለቲካ ልዩነት በላይ መሆኗን ማመናቸው ነው” ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ

125ኛው የዓድዋ የድል በዓል በአዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ተከብሯል፡፡ በበዓሉ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በዳግማዊ ምኒልክ ሀውልት ስር የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።

ፕሬዝደንቷ በበዓሉ ዝግጅት ላይ ባደረጉት ንግግር “የአድዋ ድል መላው ጥቁር ህዝቦች ቅኝ ግዛትን አሽቀንጥሮ ከመጣል የሚያግዳቸው አንዳች ነገር እንደሌለ አይናቸውን የገለጠላቸው ነው” ብለዋል፡፡

ብዙዎች አንገታቸውን በደፉበት በዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን ቅኝ ገዢዎችን አንገታቸውን አስደፍተው ጉድ ማሰኘታቸውንም ነው ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ የተናገሩት፡፡

የአድዋ ድል “አያት ቅድመ አያቶቻችን አንድነታቸው የታየበት ነው” ያሉት ፕሬዝደንቷ የቀደምት ኢትዮጵያውያን የአንድነት ታሪክ በተቃራኒው ሆኖ በተለያዩ ጉዳዮች ተከፋፍለው ቢሆን ኖሮ “ዛሬ የጥቁር ህዝብ ሁሉ አንገቱን ቀና የሚያደርግበት ታሪክ አይኖረውም ነበር” በማለት ኢትዮጵያውያን በአንድ መንፈስ ተሰልፈው ያስመዘገቡት ድል የመላው ጥቁር የኩራት ምንጭ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የአድዋ ድል ሚስጢሩ ኢትዮጵያውያን ያላቸው አንድነትና መተባበር መሆኑን በመጥቀስ አያቶቻችንን ያስከበራቸውም ፣ ኢትዮጵያ ከቡድን ፣ ከግለሰብ እና ከፖለቲካ ልዩነት በላይ መሆኗን አምነው አንድ መሆናቸው ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ከቀደምት ኢትዮጵያውያን በመማር ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ልንከተለው የሚገባው የክተት ጥሪም “ተደጋግፈን በአንድነት ሀገራችንን ወደ ፊት ማስኬድ ነው” ብለዋል ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ በንግግራቸው፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ ከፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላትን እና በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ታድመዋል፡፡ የጉዞ አድዋ ተጓዦችም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በምኒልክ አደባባይ በነበረው የበዓሉ አከባበር ላይ ታድመዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *