ኦፌኮ እና ኦነግ በዘንድሮው ምርጫ ባንሳተፍም ሰላማዊ ትግላችንን እንቀጥላለን አሉ

መንግስት በፓርቲያቸው ላይ የሚያደርገውን ማዋከብ እና እስር እስካላቆመ ድረስ በምርጫው ለመሳተፍ እንደማይሞክሩ ኦነግና ኦፌኮ ተናግረዋል በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚወዳደሩ የእጩዎች ምዝገባ ከየካቲት 08 እስከ 21 ድረስ ተካሄዶ ባሳለፍነው ቅዳሜ መጠናቀቁ ይታወሳል።

ይሁን እንጂ ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ሂደትን በመገምገም የምርጫ ክልል ቢሮዎች ለመከፈት በመዘግየታቸው፣ የትራንስፓርት መጓተት የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ላይ የምዝገባ ቀንን በማራዘሙ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች እጩዎችን ለመመዝገብ ችግር ስላጋጠመን ይራዘምልን ብለው መጠያቃቸውን ተከትሎ ለአራት ተከታታይ ቀናት አራዝሚያለሁ ሲል አስታውቋል፡፡

በዚህ የመጀመሪያ ዙር እጩዎችን ካላስመዘገቡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ና የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ይገኙበታል፡፡ ኢትዮ ኤፍ ኤም በጉዳዩ ላይ ፖርቲዎቹ ምን እንደሰሩ ጠይቋል፡፡

የኦፌኮ ተቀዳሚ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ቀናቱ ቢጨመሩም ባይጨመርም ለውጥ አይመጣም ብለዋል፡፡ መንግስት የጠየቅናቸውን ነገሮች ከግምት እስካላስገባ ድረስ ምን ይዘን ነው የምንገባው ብለው ጠይቀዋል ፡፡

“እጩዎቻችን በእስር ላይ ሆነው ቢሮዎቻችንም ቢሆኑ ሆን ተብሎ እየተዘጉ መወዳዳር አንችልም” ሲሉም ፕሮፌሰር መረራ ተናግረዋል፡፡ከበርካታ ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርጫ ለመወዳደር የተዘጋጀው ኦነግ ፤ በአባሎቹ ላይ የእስር እና የእንግልት ዘመቻው እንደቀጠለ ተናግሯል፡፡

ምንም ለውጥ ባለመኖሩ የተነሳም በዚህ ምርጫ ላይ ለመሳተፍ ከእኔ ይልቅ መንግስት ወሳኝ ሆኗል ብሏል ኦነግ፡፡ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የነበረው ኦነግ በውስጣዊ ችግሮቹ እና በፓርቲ አመራሮች እስር ታጅቦ ምርጫውን ሲጠብቅ እንደነበር ተናግሯል፡፡

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ቃላ አቀባይ የሆኑት አቶ በቴ ኡርጌሳ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ እስርን ጨምሮ ጽህፈት ቤቶቻችን ተዘግተው አልቀዋል ብለውናል፡፡

ሁኔታው ገዢው ፖርቲ ብቻውን ለመወዳር መወሰኑን አሳይቷል ይላሉ አቶ በቴ፡፡ ኦነግ በመንግሥት ይደርስብኛል በሚለው ጫናና በአመራሮቹ መካከል የተፈጠረው ቅራኔ በምርጫ ተሳትፎው ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረበትም ተናግሯል፡፡

የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ በቴ በዚህ ምርጫ ባንሳተፍም ሰላማዊ ትግላችን ግን ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ምርጫ አንዱ የትግል መንገድ እንጂ ብቸኛ አይደለም የሚሉት ቃል አቀባዩ መሳሪያችንን ጥለን ወደ ሀገር የገባነው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ነው ብለዋል፡፡

ይህንንም እያደረግን ነው የሚሉት አቶ በቴ ደጋፊዎቻችንም ሆኑ አባሎቻችን ይህንን ተገንዝበው ሰላማዊ ትግሉን እንዲቀጥሉ አድርገናልም ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ምክትል ቢሮ ሀላፊው አቶ ግዛቸው ጋቢሳ በበኩላቸው ፓርቲዎቹ እያሰሙ ያሉት ቅሬት ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ የተዘጋ የማንኛውም ፓርቲ ጽህፈት ቤትም ሆነ አባል የለም የሚሉት አቶ ግዛቸው ህግ ከተጣሰ ግን የብልጽግና አመራር እና አባላትን ጨምሮ ማንኛውም ግለሰብ በህግ ይጠየቃል ብለዋል። በክልሉ ቅሬታ ካላቸው ፓርቲዎች በተጨማሪ ሌሎች ፓርቲዎች የምርጫ ዝግጅታቸውን በማካሄድ ላይ እንደሆኑም አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *