በትግራይ ክልል እየተካሔደ ያለው የሰብአዊ እርዳታ አበረታች ነው- ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ

በትግራይ ክልል መንግስትና አለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እያካሄዱት ያለው የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ አበረታች መሆኑን በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተወካይ አባ ጴጥሮስ ተናገሩ፡፡

በቤተ-ክርስቲያንዋ የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ ለኢዜአ እንደተናገሩት መቀሌ በነበራቸው ቆይታ ህዝቡ ለሃይማኖት አባቶች መልካም አቀባበል አድርጓል፡፡

“በትግራይ እየተካሄደ ያለውን የሰብአዊ እርዳታ ለማጠናከር በኒውዮርክና አካባቢው ያለው የሀገረ ስብከት ጽህፈት ቤት ከምእመናን የእርዳታ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ እያካሄደ ነው” ብለዋል፡፡

“ለትግራይ ሕዝብ ታላቅ አክብሮት አለኝ” ያሉት አቡነ ጴጥሮስ “ትልቅ ሕዝብ በመሆኑ ፈጥነንና ቀድመን ልንደርስለት ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡ “የትግራይ ህዝብ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን አይዞህ የሚለው የማረጋጊያ የስነ-ልቦና ድጋፍ ያስፈልገዋል” ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ በሀሰተኛ ወሬ ሳይደናገር የሰላሙ ባለቤት እራሱ መሆኑን ተገንዝቦ በተረጋጋ መንፈስ ለአካባቢው ሰላም ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባም ጴጥሮስ መክረዋል።

“ህዝቡ ሀሰተኛ ወሬዎችን በጥንቃቄ በማመዛዘን ትክክለኛውን ነገር መገንዘብ አለበት ያሉት አቡነ ጵጥሮስ ለሀገራችንና ለህዝባችን ሰላም ረድኤትና በረከት እመኛለሁ” ብለዋል፡፡

በትግራይ ቆይታቸው የመቀሌ ከተማ የተረጋጋችና በሰላም ድባብ ውስጥ መሆኑዋን መታዘባቸውን ጠቁመው ህዝቡ የእለት ተእለት ሃይማኖታዊና ማህበራዊ ተግባሩን ሲከውን መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

መተከልን ጨምሮ ሰብአዊ ቀውስ የተከሰተባቸውን አካባቢዎች ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን የገለጹት አቡነ ጴጥሮስ የመተከል አካባቢም ወደ ቀደመ ሰላሙ እየተመለሰ መሆኑን መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡

ፖለቲከኞች በትግራይ ህዝብ ላይ ምንም አይነት ነገር እንዳይጭኑበት እንማጸናለን፤ ህዝቡንም በፀሎታችን ምንጊዜም እናስበዋለን በማለት ሃይማኖታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ዋልታ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *