የግብርና ሚኒስቴር የእንቁላሉን ነገር አስተባበለ

የግብርና ሚኒስቴር ከዩክሬን አገር እንቁላል ሊገባ ነው ተብሎ እየተሠራጨ ስለሚገኘው መረጃ የማውቀው ነገር የለም ብሏል፡፡ በትላንትናው እለት ዩኬ አር ኢንፎረም የተሰኘ የአገሪቱ ሚዲያ በድረ ገጹ ላይ ዩክሬን ከፍተኛ የሆነ የእንቁላል ምርትን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ላይ መድረሷን ዘግቦ ነበር፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ለሸገር ምላሽ የሰጡት በግብርና ሚኒስቴር ወደ ውጪ የሚላኩና ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እንስሳትን በተመለከተ የተቋቋመው ዳይሬክተር ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ወንድምአገኝ ደጀኔ ኢትጵያ ከዩክሬን እንቁላል ልታስገባ ነው ስለመባሉ የግብርና ሚኒስቴር የሚያውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት እዚህ ያሉ ሆቴሎች ፍላጎት ስላሳዩ ዶሮ እና የዶሮ ሥጋ በተገናኘ ከዩክሬን ጋር ስምምነት ለማድረግ ዩክሬኖች መስፈርታችሁ ምንድነው ብለው ጠይቀውን ነበር ያሉት ኃላፈው ከዚያ በኋላ ግን የተከናወነ ነገር የለም ብለዋል፡፡ በጉዳዩ የኢትዮጵያ የዶሮ አርቢዎች እና አቀናባሪዎች ማኅበርም ስለተወራው ወሬ ምንም እንደማያውቅ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ሚሊዮን ተናግረዋል፡፡ በትላንትናው እለት ዘገባውን ይዞ የወጣው ዩኬ አር ኢንፎረም ዩክሬን ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በሌሎች አፍሪካ አገራትም የእንቁላል ምርት በገፍ እንድምትልክ ገልጧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *