ኤርትራ ሱዳንና ኢትዮጵያ የድንበር ውዝግባቸውን በሠላም እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበች

የኤርትራው ፕሬዝዳንት በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ችግር በሠላማዊ ሁኔታ በመግባባት እንዲፈታ ለሱዳን ባለስልጣናት ጥሪ አቀረቡ።

ይህ የተገለጸው የኤርትራ መንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት የልዑካን ቡድን በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን ግንኙነት በሚመለከት ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የተላከ መልዕክት ለሱዳን መሪዎች ባደረሱበት ወቅት ነው።

የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳሌህ እና የፕሬዝዳንቱ አማካሪ የማነ ገብረአብ ረቡዕ ዕለት ወደ ካርቱም በማቅናት ውይይት አድርገው የፕሬዝዳንቱን መልዕክት እንዳደረሱ የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

የኤርትራ መልዕክተኞች የሱዳን ሽግግር ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የሆኑትን ሌፍተናንት ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክን በየጽህፈት ቤታቸው በተናጠል አግኝተው እንዳናጋሯቸው የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የኤርትራ ልዑካን ለሱዳን ባለስልጣናት ባደረሱት መልዕክት ላይ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ “በሁለቱ ጎረቤት አገራት መካከል የተከሰተውን ልዩነት በትዕግስትና በሠላም መፍታት” እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን የማስታወቂያ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ልዑካኑ የፕሬዝዳንት ኢሳያስን መልዕክት ከማድረሳቸው በተጨማሪ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ መወያየታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንት አል ቡርሐን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ “የተፈጠረውን ጊዜያዊ ችግር በሠላም በመፍታት ከኢትዮጵያና ከአካባቢው አገራት ጋር ጠንካራ ትስስር እንዲኖር” እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

ፕሬዝደንቱ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ካለው የድንበር ውዝግብ በተጨማሪ በአገራቸውና በሱዳን መካከል ያለውን ግንኙነትና ትብብር የበለጠ ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት መስጠታቸው ተጠቁሟል።

ሱና እንደዘገበው ሁለቱ የሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኩል የቀረበውን ሐሳብ ማድነቃቸውንና ኤርትራ እያደረገችው ባለው ጥረት እንድትቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የኤርትራ የቅርብ ወዳጆች የሆኑት ኢትዮጵያና ሱዳን የዘለቀ የድንበር ወዝግብ ውስጥ ከገቡ ወራት ተቆጥረዋል።

ሱዳን ለረጅም ጊዜ በኢትዮጵያ ተይዞብኝ ነበር ያለቻቸውን የድንበር አካባቢዎችን ሠራዊቷን አሰማርታ በቁጥጥሯ ስር ማስገባቷን በይፋ የገለጸች ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ ሉአላዊ ግዛቷ በሱዳን መወረሩን አሳውቃለች።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት የሱዳን ሠራዊት የያዛቸውን ቦታዎች ለቅቆ በመውጣት ጉዳዩ ሁለቱ አገራት ባቋቋሙት የድንበር ኮሚሽን አማካይነት ሠላማዊ መፍትሔ እንዲያገኝ በተደጋጋሚ ጠይቃለች።

ሱዳን በበኩሏ ሠራዊቷ የያዘው ሕጋዊ ግዛቷ መሆኑን በመግለጽ ከአወዛጋቢዎቹ የድንበር አካባቢዎች እንደማትወጣ መግለጿ ይታወሳል። ቢቢሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *