ትግራይ በዲያስፖራ ለሚገኙ ትግራዋዮች ጥሪ አቀረበች

“የትግራይ ተወላጅ ዳያስፖራዎች ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ ይገባቸዋል” ሲሉ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ጥሪ አቀረቡ። ዶክተር ሙሉ ነጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በትግራይ ክልል የተደረገውን የሕግ ማስከበር ተልዕኮ ተከትሎ በትግራይ ህዝብ ዘንድ የደረሰውን ችግር ለመፍታት የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። በዚህም የፌዴራልና የክልል መንግስታት በክልሉ መልሶ ግንባታና ሰብዓዊ ድጋፍ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል። በአንጻሩ የትግራይ ተወላጅ ዳያስፖራዎች የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስራ የሚያደናቅፍና ህዝቡን ወደባሰ ችግር የሚከት እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን በመግለጽ “ወደ ህሊናቸው ሊመለሱ ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የህግ ማስከበር ስራው የትግራይን ህዝብ ነጻ የሚያወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ “የሕወሃትን ጁንታና የትግራይን ህዝብ ለይቶ ማየት ይገባል” ብለዋል።
የትግራይ ህዝብ ለችግር የተዳረገው ውስን የህወሃት ሰዎች በፈጠሩት ችግር እንደሆነም ገልጸዋል። በመሆኑም የትግራይ ዳያስፖራዎች “የትግራይን ህዝብ የሚወዱ ከሆነ ከፖለቲካ ጩኸት ወጥተው ድጋፍ ማድረግ አለባቸው” ብለዋል። የትግራይ ህዝብ በዚህ ሰዓት የሚረዳው እንጂ የትግራይ ዳያስፖራዎች የሚከተሉት አካሄድ እንደማይጠቅመው ገልጸዋል። በመሆኑም ቀሪ የጥፋት ሃይሉን መደገፍና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልሉን መልሶ ለመገንባት እያደረገ ያለውን ጥረት ማደናቀፍ ህዝቡን ለከፋ ችግር መዳረግ እንደሆነ አስገንዝበዋል። ሰብዓዊነት የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም” የሚሉት ዶክተር ሙሉ፤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ ለትግራይ መልሶ ማቋቋም እጁን እንዲዘረጋ ጥሪ አቅርበዋል። ኢኘድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *