ለኢትዮጵያውያንና ለአፍሪካውያን ፈር ቀዳጅ ድል ያስመዘገበችው ፋጡማ ሮባ
By: Date: February 23, 2021 Categories: Uncategorized Tags:

ፋጡማ ሮባ የመጀመሪያውን የሴቶች ማራቶን ፈር ቀዳጅ ድሏን በ1996 በሞሮኮ ማራክሽ ነበር የተቀዳጀችው። በመቀጠልም ከሁለት ወር በኋላ በሮም ማራቶን አሸናፊ ሆነች። ከሮም አሸናፊነት በኋላም በ1996 በአትላንታ አሜሪካ በሚደረገው የኦሊምፒክ ውድድር በ2:26:05 በሆነ ሰዓት አንደኛ በመሆን አጠናቀቀች።

በወቅቱ ፋጡማን በመከተል ሁለት ደቂቃ ዘግይተው የሩሲያዋ ቫለንቲና ይጎሮቫና ጃፓናዊቷ ዩኩ አርሞሪ 2ኛና 3ኛ በመሆን ተከታትለው ገብተዋል። ከ1997 እስከ 1999 የተካሄዱ የቦስተን ማራቶን ውድድሮች በተከታታይ ያሸነፈችውን ፋጡማ የ’ቦስተኗ ንግሥት’ የሚል ቅጽል ስም አግኝታበታለች።

ለአትሌት አበበ ቢቂላ ትልቅ ፍቅር እንደላት የምትናገረው አትሌት ፋጡማ ሮባ “አቤን በደንብ እወደዋለሁ፤ አደንቀዋለሁ። አቤን እኔ ብቻ ሳልሆን መላው ዓለም ያደንቀዋል” ትላለች።

ለዓመታት ከአገርና ከአትሌቲክሱ መድረክ ርቃ የቆችው የኦሊምፒኳ ኮከብ አትሌት ፋጡማ ከቢቢሲ ጋር ባደረገችው ቆይታ ስለ ህይወቷ እንዲህ ብላለች። [የተጠቀሱት ዓመታት በሙሉ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ናቸው]

ስለ አትሌቲክስ ምንም የማውቀው ነገር የለኝም

በ1970 ዓ.ም በአርሲ ዞን ሌሙና ቢልቢሎ ወረዳ፣ ሁሉሌ ካራ በሚባል ስፍራ ተወለድኩ። ገጠር ውስጥ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ነው የወጣሁት። ኑሮዬና ትምህርቴም እንደ ማንኛውም የገጠር ልጅ ነበር።

በገጠር እንዳደጉት ልጆች ከብቶችን ስጠብቅና ቤተሰብን ስረዳ ስለቆየሁ ቶሎ ትምህርት ቤት አልገባሁም። ትምህርት ቤቱም ከቤተሰቤ ርቆ ስለሚገኝ በደንብ ካደግሁ በኋላ በደርሶ መልስ 14 ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዤ እማር ነበር።

ያደግኩበት ገጠር ቴሌቪዥንም ሆነ ሬዲዮ አልነበረም።

ስለዚህ ስለአትሌቲከስ የማውቀው ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ በትምህርት ቤት ውስጥ እኣወዳደሩ ነጥብ ይይዙልን ነበር።

አስተማሪያችን መሃረብ ይዞልን “ማን ቀድሞ ይነካል” እያለ ያወዳድረን ነበር።

እኔ ከሴቶች ጋር ተወዳድሬ አሸንፋለሁ። ወንዶችንም ቢያመጡ አሸንፍ ነበር። ከዚያ በኋላ ከትምህርት ቤቴ ተመርጬ በወቅቱ አውራጃ ወደሚባለው፣ ከዚያ ደግሞ ክፍለ አገር ለሚባለው ተወክዬ መወዳደር ጀመርኩኝ። በዚሁ ነው እንግዲህ ወደ አዲስ አበባ መጥቼ የተለያዩ የስፖርት ቡድኖች መኖራቸውን ያወቅኩት።

ክፍለ አገርን ወክዬ በተወዳደርኩበት ጊዜ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ቡድን አይቶኝ ሃጂ ቡልቡላ የሚባለል ሰው ላከብኝ።

እርሱም ቡድኑ እንደሚፈልገኝ፣ ትምህርቴንም እንድማር፣ ደሞዝም እንደሚከፍሉኝ ነገረኝ።

እኔም ቤተሰቤን ሳማክር ብዙም ደስተኛ ስላልነበሩ ሊከለክሉኝ አሰቡ። ይሁን እንጂ ሃጂን ካዩ በኋላ ፈቀዱልኝ፤ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ መጣሁ።

በ1994 እኤአ ቤልጂየም አገር ነበርኩኝ። እዚያም በአገር አጭር ውድድሮች ላይ በመሮጥ ተሳተፍኩኝ።

ቤልጂየም በቆሁበት ወቅት አንድ ማራቶን የምትሮጥ ሴትን በፓሪስ ማራቶን ለምን ካንቺ ጋር አልሮጥም ብዬ ጠየቅኳት።

እርሷም ነይ አብረን እንሂድ አለችኝ። ከዚያም በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1994 በተካሄደው የፓሪስ ማራቶን ሳልዘጋጅ ተወዳደርኩ።

ውድድሩ ሲጀመር ከሌሎች አትሌቶች ጋር መሮጥ አቃተኝ። ጥለውኝ ሄዱ፤ ይሁን እንጂ ወደ 35ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ደረስኩባቸው።

ከእነርሱ ጋር ግን መቀጠል አልቻልኩም ጥለውኝ ሄዱ። በጣም ደክሞኝ ስለነበር ውሃ ጠጣሁ። ውሃውም ሆዴን ወጥሮ ያዘኝ።

ውድድሩንም ብጨርስም ሁለተኛ አልሮጥም ብዬ ነበር።

ወደ አገር ቤት ስመለስ ግን ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ማራቶን እንድሮጥ ጠየቁኝ።

ከዚያ በኋላ ስልጠና ወስጄ እንዴት ማራቶን እንደምሮጥ ተማርኩ። ወደ ሞሮኮ ሄጄም ማራካሽ ላይ ማራቶን ተወዳደርኩ።

በ1996 የማራካሽ ማራቶን ላይ ብዙም ስልጠናና ልምምድ ሳላደርግ ነበር የተሳተፍኩት።

በውድድሩም ‘ቢ ካታጎሪ’ የሚባለውን አምጥቼ ተመለስኩ።

ከሁለት ወር በኋላ በሮም ማራቶን ተወዳድሬ፣ ‘ኤ ካታጎሪ’ የሚባለውን ውጤት አምጥቼ በኦሊምፒክ ውድድር ለመሳተፍ የሚያስችለኝን ነጥብ አገኘሁ። በዚሁ ልምምድ አድርጌ በ1996 በተካሄደው የአትላንታ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ሄድኩኝ። ኦሊምፒክ ትልቅ ውድድር ነው። የአትላንታ ኦሊምፒክ ለእኔ ከተሳተፍኩባቸው ሁሉ ትልቁ ውድድር ነበር።

ለውድድሩ በበቂ ተዘጋጅቼ ነበር። ግን ፍርሃት በውስጤ ስለነበረ አሸንፋለሁ የሚል ግምት አልነበረኝም። ካሸነፍኩ በኋላ ግን ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ። አሰልጣኞቼም በውድድሩ ታሸንፋለች ብለው አልጠበቁም ነበረ።

በኦሊምፒክ ማራቶን ውድደድር ላይ በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ሴት አፍሪካዊት መሆኔ በጣም አስደሰተኝ። የሚረሳም አይደለም። ከአትላንታ በኋላ በ1997፣ 98፣ 99 በቦስተን ማራቶን ውድድሮች በተከታትዬ ለሦስት ጊዜ አሸንፌያለሁ።

በ2004 ነበር ሩጫ ያቆምኩት።

በዚያ ጊዜ ለመውለድ ብዬ ነበር ሩጫ ያቆምኩት፤ ከዚያ በኋላ ግን አልተመለስኩበትም።

አሁን የሁለት ልጆች እናት ነኝ። የመጀመሪያው ልጄ 15 ዓመት ሁለተኛዋ ደግሞ 13 ዓመቷ ናቸው።

ሩጫ ካቆምኩ በኋላ ምንም እየሰራሁ አልነበረም። ልጆቼን እያሳደኩ ነበር።

ይሁን እንጂ እነርሱ ካደጉልኝ በኋላ አንደንድ ሥራዎችን ለመስራት እያሰብኩ ነው።

የአሁኑን አትሌትክስ ብዙም አልከታተልም። ይሁን እንጂ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ስመለከት ጠንካራ አትሌቶች አሉ። እኛ ስንገባበት የነበረውንም ሰዓት እያሻሻሉ ነው።

ከአሰልጣኞቻቸው ጋር ከተስማሙ እና በደንብ ከሰሩ ከዚህ የበለጠ ነጥብ ማምጣት እንደሚችሉ ተስፋ አደርጋለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *