የኤርትራን ወታደራዊ መለዮ ለብሰው ጁንታው የፈጠራቸው ወንበዴዎች ናቸው
By: Date: February 22, 2021 Categories: ዜና Tags:

በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች ስለ ትግራይ ክልል የሚሰራጨው መረጃ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በትክክል እንደማያሳይ በትግራይ ክልል የሰሜናዊ ዞን ጊዜያዊ አስተዳደር ገለጸ። የሰሜናዊ ዞን ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሙሉብርሃን ኃይሉ “የኤርትራን ወታደራዊ መለዮ ለብሰው የህዝቡን ንብረት የሚዘርፉትና ሴቶችን የሚደፍሩት የጁንታው ስርዓት የፈጠራቸው ወንበዴዎች እንጂ የኤርትራ ወታደሮች አይደሉም” ብለዋል።

በትግራይ ክልል ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ የነበራቸው አቶ ሙሉ ብርሃን ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን በእብሪተኝነት በለኮሰው እሳት ራሱም ተለብልቦ ለበርካታ ዜጎች ሞትና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል። ከዚህም ባለፈ በውጭ አገር ያሉና በእግራቸው ጫካ ለጫካ የሚኳትኑ ቀሪ የጁንታው አባላት በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾች የሀሰት ፕሮፖጋንዳ በመንዛት የትግራይን ህዝብ ለማታለል እየሞከሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዳለ የገለጹት አቶ ሙሉብርሃን የክልሉን ወቅታዊ ሁኔታ በአካል ተገኝቶ መዘገብ ለሚፈልግ የመገናኛ ብዙሃን በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል። በክልሉ ሳይገኙ በርቀት ሆኖ የሀሰት መረጃ ማሰራጨት ተገቢ እንዳልሆነም አስገንዝበዋል።

ህወሓት ባለፉት 46 ዓመታት የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያዊነት ለመነጠል የሀሰት ትርክት እየደረሰ ከማወናበድ ውጭ ምንም ጥቅም እንዳላስገኘለት ህዝቡ ተገንዝቧል ብለዋል አቶ ሙሉብርሃን። አክሱማዊያን ኢትዮጵያዊያን አልነበሩም የሚል የሀሰት ድርሰት ተዘጋጅቶ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመነጠል የመሞከረ የራስ ወዳዶች ስብስብ መኖሩንም ጠቁመዋል።

የትግራይ ህዝብ ህወሃት የራሱን አጀንዳ ብቻ የሚያስፈጽም የማፍያ ስብስብ መሆኑን በመረዳት የመከላከያ ሰራዊቱ የተጠናከረ ህግ የማስከበር እርምጃ እንዲወስድ መረጃ በመስጠትና አቅጣጫ በመጠቆም እየተባበረ መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ሙሉብርሃን እንደሚሉት የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል ሀብት እየዘረፉ ነው ሴቶችን እየደፈሩ ነው በሚል የሚሰራጨው የተሳሳተ መረጃ መሬት ላይ ያለውን ሀቅ አያሳይም።

የጁንታው ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ካደረሰ በኋላ አጸፋውን መቋቋም ሲሳነው በስርቆትና በተለያዩ ወንጀሎች ማረሚያ ቤት የነበሩ ወጣቶችን በመልቀቅ ለዘረፋ አሰማርቷቸዋል ብለዋል። ስርዓቱ የፈጠራቸውን ስራ አጥ ወጣቶች መሳሪያ በማስታጠቅና የኤርትራን ወታደራዊ መለዮ በማልበስ ሴቶችን እንዲደፍሩ በማድረግ በኤርትራ ወታደሮች ላይ ለማሳበብ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አመልክተዋል።

የኤርትራ ወታደሮች ህወሓት ባሰማራቸው ዘራፊዎች ወደ ኤርትራ ድንበር ሄዶ የነበረ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት ለትግራይ ህዝብ አስረከቡ እንጂ የትግራይን ህዝብ ንብረት አልዘረፉም ያሉት አቶ ሙሉብርሃን ድርጊቱ በህዝቡ መካከል ልዩነት ለመፍጠር የተደረገ የህወሃት የተለመድ ሴራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የህወሃት ቡድን የትግራይን ህዝብ ከሁሉም ጋር በማጋጨት ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ ለማድረግ ያደረገውን የ46 ዓመታት ስብከት ለማጥፋት ከአማራና ከኤርትራ ህዝብ ጋር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ውይይት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል። አቶ ሙሉብርሃን እንደሚሉት የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ገመድ በሌሊት መቁረጥ ወይም አንድን ሰው በድንገት መግደል ህወሃት ዛሬም በትግራይ ምድር የፈለገውን ማድረግ ይችላል ማለት አይደለም። ህወሃት በትግራይ ክልል ጥቃት መፈጸም ቀርቶ ራሱን መከላከል በማይችልበት ሁኔታ ጫካ ለጫካ ራሱን ለማዳን የሚኳትን አካል ሆኗል ብለዋል። ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *