ምን በዛ? አደገኛ ባለስለት አጥር

ሃሳብ ከእውነታ ጋር ሲጣላ፣ ፖለቲካ ከህልውና ጋር ሲጣረስ፣ የቤቱን አጥር በእሾህ እየጠቀጠቀ ግቢውን ለመከርቸም ተፍተፍ የሚል ሰው ይበረክታል። በየከተማው፣ ከቤቱ አስበልጦ፣ አጥሩን ለማስረዘም፣ ቀና ደፋ የሚል ነዋሪ እየበዛ ይሄዳል። በላዩም ላይ፣ የጠርሙስና የብርጭቆ ስብርባሪ ያርከፈክፍበታል።

ዛሬ ዛሬ ደግሞ፣ የስለታማ አጥር ገበያ ደርቷል። ድሮ ድሮ በኤምባሲዎች ላይ ነበር የሚታየው። አሁን ግን፣ በየመኖሪያ ቤቱ፣ በትንሹም በትልቁም፣ የስለታማ አጥር መቀነት፣ በድርብ በድርቡ ሆኗል። በረዥሙ የተሰራ ግንብ አልበቃ ብሎ፣ ጥልፍልፍ ስለታማ አጥር እየተጨመረበት ነው። ባለ ኤሌክትሪክ የሽቦ አጥርም ይታከልበታል። የዘመናችን የአጥር ጥልፍና ጥለት በሉት።

ከእሾህና ከግንብ በተጨማሪ፣ አጥር ላይ፣ አደገኛ ባለስለት ጥልፍ ለመስራት የሚፍጨረጨሩ ሰዎች ቢበረክቱ፣ አይፈረድባቸውም። የሚሰሙትና የሚያዩት ነገር፣ ከእውነታና ከኑሮ ጋር ቢጣረስባቸው ነው። “ወሬ ሌላ፣ ኑሮ ሌላ” ቢሆንባቸው ነው።

በየዕለቱ፣ ነጋ ጠባ የምንሰማቸውን ዲስኩሮች ተመልከቱ። አንድ የጋራ ባሕርይ አላቸው። “ለግል ኑሮና ለግል ህልውና”፣ ቅንጣት ክብር አይሰጡም። እንዲያውም፣ “የግል” የተባለውን ነገር ሁሉ የማጣጣልና የማንቋሸሽ ስብከት ይመርቁበታል። ማለትም፣ እርግማንና ውግዘት ያወርዱበታል።

የግል ማንነንትና የግል ህልውናን ለማጣጣል፣ እሽቅድምድም ሞልቷል። “የጋራ ማንነት፣ የብሔር ማንነት” ምናምን እየተባለ፣ ያለእረፍት በጅምላ የሚጎርፈው ጭፍን ዲስኩር፣ እየተመነዘረ የሚቸረቸረው የተሳከረ የወሬ መዓት፣ ስፍር ቁጥር የለውም። የግል ማንነትን የሚያብጠለጥል የስካር ሃሳብ፣ በምሁራን ይሰበካል፣ በፖለቲከኞች ይደሰኮራል። ሙሉውን ጽሁፍ እዚህ ይመልከቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *