Press "Enter" to skip to content

«የዘንድሮውን ምርጫ ለየት የሚያደርገው አሸናፊውን ቀድመን ማወቃችን ነው»

«የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያዋጣዉ የራሳቸዉን ፕሮግራም ለህዝቡ ማሳወቅ እንጂ ገዢ ፓርቲን መተቸት ብቻ ዉጤት አያመጣም ። የብልፅግና ፓርቲ ምርጫ ቅስቀሳ እስካሁን በተግባር የፈፀማቸዉ ልማቶች ተጀምሯል።» በማለት የገዢውን ፓርቲ እንቅስቃሴ ለማሳየት ሞክረዋል።

ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ እና የለውጥ አመራር ለተባለው የገዚው ፓርቲ መሪዎች ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች የድጋፍ ሰልፎች እየተደረጉ መሆናቸው እና የምርጫ እንቅስቃሴ መጀመሩ፤ በትግራይ ክልል በርካታ አካባቢዎችን የኤሌክትሪክ አገልጎሎት ያስተጓጎለው የሰሞኑ ጥቃት እንዲሁም የኤርትራው ፕሬዚዳንት በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ቀርበው በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ተናገሯቸው በተባሉ ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶች በዛሬው ዝግጅታችን ተዳሰዋል።

ባለፉት ሳምንታት ለጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እና «የለውጥ አመራር» ለተባሉ ባለሥልጣናት በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የድጋፍ ሰልፎች ሲደረጉ ቆይተዋል። ከትግራይ ክልል እና ከሁለቱ የፌዴራል የከተማ አስተዳደሮች ውጭ ሁሉንም ክክልሎች ያሳተፈው የድጋፍ ሠልፍ ገዚው ፓርቲ በተናጥል የምርጫ ዘመቻ ጀምሯል የሚሉ አስተያየቶችን ሲያስተናግድ፣ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ ሰሞኑን የምርጫ ቅስቀሳ የሚመስል እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተስተውሏል። «የምርጫ ቅስቀሳ ተጀመረ» የሚሉ እና በሰሞንኛ እቅስቃሴዎች ላይ የተለያዩ አስተያየቶች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲንሸራሸሩ ነበር።

ሙሉጌታ አሰጌ «አዎ አዝማሚያው ሲያዩት የምረጡኝ ዘመቻ ይመስላል አንደኛ የፀጥታ አካላት ሁሉንም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል ማስተናገድ አለባቸው ፤ ሁለተኛ ህዝቡ የሚመራውን ሳይሆን የሚሆነውንና የሚወክለውን መምረጥ አለበት ብዬ አስባለሁ » የሚል አስተያየት ሲያሰፍሩ «ኢትዮጵያዊ ነኝ» በሚል መጠርያ አጭር አስተያየታቸውን ያሰፈሩት « የዘንድሮውን ምርጫ ለየት የሚያደርገው አሸናፊውን ቀድመን ማወቃችን ነው» ብለዋል።

ሴና ኢፋ በበኩላቸው «የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያዋጣዉ የራሳቸዉን ፕሮግራም ለህዝቡ ማሳወቅ እንጂ ገዢ ፓርቲን መተቸት ብቻ ዉጤት አያመጣም ። የብልፅግና ፓርቲ ምርጫ ቅስቀሳ እስካሁን በተግባር የፈፀማቸዉ ልማቶች ተጀምሯል።» በማለት የገዢውን ፓርቲ እንቅስቃሴ ለማሳየት ሞክረዋል። ተሜ ሸበላው የተባሉ አስተያየት ሰጪ «በእዉነት ዉስጥ የተደበቀ ዉሸት አንድ ቀን መዉጣቱ አይቀርም » ሲሉ እንዲሁ በደፈናው አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

ግርማ አሰፋ በበኩላቸው መጪውን ምርጫ በተመለከተ ባሰፈሩት ሃሳባቸው «ዲሞክራሲያዊ እንደሚሆን እና የአንድ መንደር ሰው የበላይነት እሚቀርበት፣ ጉልበተኞች አርፈው ቁጭ እሚሉበት፣ በፍትህ አደባባይ ብቻ የማንነት ጥያቄዎች የሚመለሱበት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ» ሲሉ ገልጸዋል።

በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሰፈሩ አስተያየቶች ውስጥ ስጋትም ነበረበት ። ሰላም ዘመዴ የተባሉ አስተያየት ሰጪ « ኸረ ያስፈራል ፤ እኔንጃ ብቻ የ97ቱ ምርቻ እንዳይደገም በበኩሌ ፈርቻለሁ» ሲሉ የስጋታቸውን ምክንያት ያልገለጹበትን ሀሳባቸውን አስፍረዋል።

«አንተ ሰው አድርገኝ» በሚል መጠርያ ሀሳባቸውን ያካፈሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ተስፋ አላቸው። «እንደ መጥረቢያ እንጨት የተጣመመ ፓርቲ የመመረጥ እድሉ ዘንድሮ ያካትማል ህዝቡ አንድነት ፈልጓል ለሀገር አንድነት የሚወዳደሩ ፖርቲዎች ያሸነፋሉ።» ሲሉ ሀሳባቸውን አካፍለዋል።

በትግራይ ክልል ሰሞኑን በርካታ አካባቢዎችን ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጭ ያደረገ በኤሌክትሪክ መስመር ላይ ጥቃት መድረሱ ተነግሯል መንግስት «ህግ የማስከበር ዘመቻ ባለው ዘመቻ» ወቅት ተመሳሳይ ጥቃት ደርሶ ትግራይ ለሳምንታት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጭ ሆና ነበር።ሰሞኑን ደረሰ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየቶች ሲንሸራሸሩ ተስተውለዋል።

አለማየሁ ፍቅሬ «እየወደመ ያለው የሀገር ሀብት ስለሆነ ህብረተሰቡ አምኖበት የራሱ መሆኑንና ሊጠብቀው የሚያስችል ደረጃ ላይ ሲደርስ ይጠገንላቸው እንጂ ነገም ተመልሶ ስላለመውደሙ ዋስትና የለውም » ሲሉ መንግስት የደረሰውን ጉዳት ቢጠግን በድጋሚ ጥፋት ላለመድረሱ ዋስትና የለውም ሲሉ ስጋታቸውን የገለጹበትን ሀሳብ አካፍለዋል።

ይቅደም አቡ በበኩላቸው«ትግራይ ሙሉ በሙሉ መቼ መብራት ነበረ? ከመቐለ ተቋረጠ ቢባል ይሻላል።ሌሎች ወረዳዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠባቸው ከአራት ወር በላይ ሆኖታል::» በማለት ችግሩ ቀደም ሲልም እንዳልተቀረፈ ሲገልጹ

ሰዒድ ዳውድ በበኩላቸው። «ይቀጥላል !አንድ እና ዋና የትግል ሥልት ግብግብ ነው ድልድይ መናድ፣ መብራት ማውደም፣ የህዝብ መገልገያዎችን በተቻለ መጠን ማቃጠል ፤ ነዳጅ ሌላም ሌላም የህዝብ ጥቅም የዕለት ተዕለት እንቅሥቃሤ ላይ ሥውር ጥቃት አደጋ አሥመሥሎ መፈጸም፣ መንገድ መዝጋት ፣ከተቻለ ከባድ መኪና በመገልበጥ ፣የነዳጅ ቦቴ ባፍጢሙ በመድፋት ሸቀጣሸቀጥ ላይ የዋጋ ንረትን በማባባሥ ሥፍር ቁጥር የሌለው ዘዴ በመጠቀም መፋለም ይቻላል ፣ ኮክቴል ግብዣም አለ ይቻላል፡፡ ግን ግን ህዝብን ማጉላላት ጾም ማሣደር ምን ይጠቅማል ሲሉ ደረሰ የተባለውን ጥቃት የተቃወሙበትን ሀሳብ አካፍለዋል።

ራፋ ጃፎ ራቦ በበኩላቸው «ጦርነቱ በድጋሜ ተፋፍሟል ማለት ነው? ወይስ ትላንት አቶ ጌታቸው ቃለመጠየቅ ስለ ሰጠ እሱ እንዳይተላለፍ ተፈልጎ ነው? ሲሉ ጠይቀዋል። ሙሉቀን ተሾመ የተባሉ አስተያየት ሰጭ እንዳሉት ደግሞ «ይሔ ነው እንግዲሕ ለትግራይ ህዝብ መታገል መጀመሪያ ይህን የጥፋት ሀይል የወንጀለኛ ስብስብ ማውገዝ ከነዋሪው ይጠበቃል ከደበቀበት አውጥቶ እስከመስጠት ድረስ ከዛ መንግስት እንደቀድሞው ሀላፊነቱን ይወጣል ካልሆነ ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ በሀገር ሀብት መቀለድ ይሆናል፡፡» የመሰረተ ልማቱን የማስጠበቅ ሀላፊነት የማን እንደሆነ የገለጹበትን አጋርተዋል።

ንጉሴ መኮንን ደግሞ «ድልድይ ማፍረስ መሰረተ ልማት ማውደም የኖረበት ነው ህወሃት 46 አመት። ገና ይቀጥላል።« ብለዋል። ኤርሚያስ መለሰ በበኩላቸው «የትግራይ ህዝብ ሆይ ከማንም በላይ ተጎጂ መሆንህን አውቀህ ለዚህ ሃይል ከለላ በመሆን ወንጀለኞችን አታበረታታ ተቃወማቸው ንብረትህን ጠብቅ አውሮፓና አሜሪካ በሞቀ ኑሮ ላይ እየኖሩ በስምህ እና በጥቅምህ ላይ እንዲነግዱ አትፍቀድላቸው ንቃ ወዳጄ “የነቃ አይጥልም እቃ”ይባል የለ ተረቱ» በማለት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

ሰሞኑን በማህበራዊ መገናኛ በስፋት ከተንሸራሸሩ ጉዳዮች ውስጥ የኤርትራው ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ በተለይም ትግራይ ክልል ውስጥ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ እና የሕወሃት አመራሮችን በተመለከተ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን ባደረጉት ቃለ ምልልስ ኤርትራ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የቻሉትን እያበረከቱ » መሆኑን የተገለጸበት አንደኛው ነው። የፕሬዚዳንቱ ቃለምልልስ በመገናኛ ብዙሃን ከተሰራጨ ቦኋላ በሁለት ጎን የሚለጠጡ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አስተያየቶችን አስተናግዷል።

ማርኮን ማርክ የተባሉ አስተያየት ሰጭ«ምን እንዲል ጠበቃችሁ የ 30 ዓመት ታሪክ አይደለም ኢትዮጵያን እና ኤርትራውያን ያለን ግንኙነት ኢትዮጵያ ጠል በሆኑ ሰዎች ሳንፈልግ ብንለያየም ደማችንም ማንነታችንም አንድ ነው የኢትዮጵያ ደህንነት ኤርትራዊያን ይመለከታል የኤርትራ ደህነት ኢትዮጵያዊን ይመለከታቸዋል ከዚያ ሁሉ ደም መፍስ በዋላም የሁለቱም ጠላት ሲወድቅ እና ወደ ሰላም ሲመለሱ በሁለቱም ህዝብ ዘንድ የነበረው ደስታ ትልቅ ማረጋገጫ ነው። ያን ጊዜ ከረሳችሁት» ሲሉ፣ ህሉፍ ጸጋለም በበኩላቸው «የሰው በር በድጅኖ በመስበር እና የድሐ ልጅ በመግደል እየተሳተፈ ነው ኤርትራ የግሉ አድርጎ ኢትዮጵያውያን ግን እያፋጀን ነው በምትዋከብ ኢትዮጵያ የበለፀገች ኢትዮጵያ እየፈጠረ ነው » የሚል አስተያየት አጋርተዋል።

የሸክላ ሰሪው ልጅ በሚል አስተያየታቸውን ያሰፈሩ ሰው « ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በትላንቱ ንግግራቸው የተረጋጉ መሪና አስተዋይ ሰው መሆናቸውን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥልቅ ፍቅር እንዳላቸው ተገንዝቤያለሁ፣ ተገንዝበናል።» ሲሉ ሚኬ ጥበቡ የተባሉ አስተያየት ሰጭ በተቃራኒው «ችግር ውስጥ ያለች ሃገር ችግሯን ከማካፈል ውጭ ምንም አትፈጥርም ኤርትራ ልትረዳን እምትችለው ትግራይ ክልል ያሉትን ወታደሮች በማስወጣት ብቻ ነው» ብለዋል።

ዞሮ ዞሮ በሚል መጠርያ አስተያየታቸውን ያሰፈሩ ሰው በበኩላቸው « የአካባቢዉ ጉዳይ የጋራችን ነዉ በጋራ በመስራት ምስራቅ አፍሪካን ወደፊት ማሰቀጠል ነዉ።» ብለዋል። እስሮም ቲኬ የተባሉ አስተያየት ሰጭ ለፕሬዚዳንቱ ንግግር « የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች » የሚል አስተያየት በደፈናው አካፍለዋል። እንግዲህ አድማጮች ላዛሬ ያልነው የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅንት ዝግጅታችን የዛሬው ይህን ይመስላል ። የዶቸቨለ ዘገባ ነው

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//daichoho.com/4/4057774