አሁን ያ ሁሉ ነገር አልፎ መቀሌ ላይ ህይወት ወደ ቀደመ ቅኝቷ እየተመለሰች ነው፡፡ መቀሌ ላይ አሁን ችግር የሆነው ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛው የኢንተርኔት አለመኖር ሲሆን፣ 2ኛው ደግሞ የሀገሬው ሌባ ነው፡፡ መቀሌ ላይ የሞባይል፣ የገንዘብና የንብረት ዘረፋው አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል (ብሩህ አለማየሁ)

በጦርነቱ ወቅት መቐለ ነበርኩ፡፡ በህይወቴ በጣም አስፈሪውን ጊዜ ነው ያሳለፍኩት፡፡ የሞትን ፍርሃት ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁበት ወቅት ነው፡፡ ‹‹መጤ ብለው ይገድሉን ይሆን?›› የሚል ፍርሃት “መድፉ እኛ ላይ ይወድቅ ይሆን?” የሚል ፍርሃት፣ ከእነዚህ ፍርሃቶች ስንገላገል ደግሞ የኢኮኖሚ ችጋር ውስጥ ወደቅን፡፡

14 ቀናት ያለመብራት (ከህዳር 20 – ታህሳስ 4/2013)፣ 39 ቀናት ያለስልክ አገልግሎት (ከጥቅምት 25-ታህሳስ 4/2013)፣ 18 ቀናት ያለ ቧንቧ ውሃ (ከህዳር 17-ታህሳስ 6/2013)፣ 53 ቀናት ያለ ባንክ አገልግሎት (ከጥቅምት 25-ታህሳስ 19/2013)፣ 90 ቀናት ያለ ኢንተርኔት (ከጥቅምት 25-እስከ አሁን ድረስ)

በእነዚህ ቀናት ውስጥ ቤተሰቦቻችን ‹‹ከሞት ተርፈው ይሆን?!›› እያሉ በየቀኑ ሲጨነቁ ነበር፡፡ በዙሪያችን ምን እየተደረገ እንደሆነ አናውቅም ነበር፤ ከሁሉም ጋር ተነጥለን ደሴት ሆነን ነበር፡፡ ከየአቅጣጨው ወደ መቀሌ ሲገቡ የነበሩ ምርቶች ሙሉ በሙሉ ቆመው ነበር፡፡ በዚያን ወቅት በምርት የአቅርቦት እጦት የተነሳ የሸቀጦች ዋጋ እስከ 400% ድረስ አሻቅቦ ነበር፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ4500 ብር ወደ 8000 ብር፣ አንድ ሻማ ከ4 ብር ወደ 10 ብር፣ አንድ ኪሎ ቲማቲም ከ20 ብር ወደ 95 ብር ተተኩሶ ነበር፡፡

በዚህም የተነሳ ኑሮ በጣም ከባድ ሆነ፡፡ ባንክ ተዘግቷል ብር የለም፡፡ ሰው በየቤቱ የነበረው አስቤዛ አለቀ፤ ያለው ለሌለው እያካፈለ መኖር ጀመረ፡፡ ሱቆች በዱቤ መሸጥ ጀመሩ፡፡ ከቤት የሚተርፍና የሚጣል እህል ጠፋ፤ ውሾችና ድመቶች ተራቡ፡፡ መብራት ላይ የተገነባው የሰው ልጅ ስልጣኔ አይናችን እያየ መቀሌ ላይ መንኮታኮት ጀመረ፡፡ ኑሯችን ሁሉ ወደ ጥንታዊ ሰው እየሆነ ሄደ፤

ማብሰያችን ከኤሌክትሪክ ምድጃ ወደ ከሰል፤ ከከሰል ወደ ዲንጋይ ምድጃ ተቀየረ፤ የምግብና የመጠጥ ውሃችን ከሃይላንድ ወደ ቧንቧ፣ ከቧንቧ ወደ ጉድጓድ ውሃ ተቀየረ፡፡ የጉድጓዱን ውሃ ሳያፈሉ የጠጡትም በጠና ታመሙ፡፡

ሰዓት መቁጠር አቆምን፣ ጊዜውም ተደበላለቀብን፡፡ ሰው ሁሉ እጁ ላይ ያለው ገንዘብ ማለቅ ሲጀምር ሸቀጦች ከተሰቀሉበት ዋጋ በአስደንጋጭ ፍጥነት ወረዱ፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ኪሎ ቲማቲም ከ95 ብር ወደ ሦስት ብር ወረደ፡፡ አንድ እንቁላል ከሰባት ብር ወደ አራት ብር ዝቅ አለ፤ ዶሮ ከ500 ብር ወደ 150 ብር ወረደ፡፡ በርካታ አትክልትና ፍራፍሬዎች የሚገዛቸው አጥተው ተበላሽተው ተጣሉ፡፡

አሁን ያ ሁሉ ነገር አልፎ መቀሌ ላይ ህይወት ወደ ቀደመ ቅኝቷ እየተመለሰች ነው፡፡ መቀሌ ላይ አሁን ችግር የሆነው ሁለት ነገሮች ናቸው፡፡ አንደኛው የኢንተርኔት አለመኖር ሲሆን፣ 2ኛው ደግሞ የሀገሬው ሌባ ነው፡፡ መቀሌ ላይ የሞባይል፣ የገንዘብና የንብረት ዘረፋው አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ገበያው ግን ተጧጡፏል፤ ትራንስፖርት ወደ ሁሉም የትግራይ አካባቢዎች ተጀምሯል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ከመቀሌ ወደ አላማጣ ለመሄድ እግረ መንገዴን መናኻሪያዎቹን ለማየት የመቀሌ-ላጨ መናኻሪያ ተገኝቼ ነበር፡፡ በእዚያም አዲግራት፣ አክሱም፣ ሽረ፣ ሽራሮ፣ አድዋ፣ ኣብይ ኣዲ እያሉ የሚጣሩ የሚኒባስና የሎንቺን ረዳቶችን አየሁ፡፡ ወደ ድሮው መናኻሪያ ስሄድ ደግሞ አላማጣ፣ መሆኒ፣ ማይጨው፣ ኣዲ ጉዶም፣ ሔዋነ፣ አብ አላ (አፋር)፣ አዲስ አበባ እያሉ የሚጣሩ ረዳቶችን አየሁ፡፡

እኔም የአላማጣው ሚኒባስ ውስጥ ገብቼ ሄድኩ፡፡ በመንገዴ አንዳንድ የጦርነቱ ቅሪቶችን (የተቃጠሉ መድፎችና ተሽከርካሪዎች፣ የተበጣጠሱ የኤሌክትሪክ መስመሮች) ተመለከትኩ፡፡ ጠንከር ያሉ የመከላከያ ፍተሻዎችም እንዳሉ አይቻለሁ፡፡ በዚህ አስፈሪ ወቅት በሀገር ውስጥና በውጭ ያላቹህ ወዳጆቼ ደህንነቴ አሳስቧቹህ በስልክ፣ በፌስቡክና በኢሜል ላደረሳችሁኝ መልዕክት ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *