የሌፍተናንት ጄነራል ጃገማ ኬሎ 100 ኛ ዓመት የልደት በዓል

በ1954 ዓ.ም ደግሞ ጄኔራል ጃገማ እግሩን ተሰብሮ ጦር ሰራዊት ሆስፒታል ገባ። ንጉሰ ነገስቱ በየሆስፒታሉ ያሉ ህመምተኞችን ሄዶ የመጠየቅ ልምድ ስለነበራቸው በሄዱ ቁጥር ጄኔራል ጃገማን ይጠይቁታል። ጄኔራል ጃገማ የጦር ሰራዊት ሆስፒታል ተሽከርካሪ ወንበር(ዊልቸር) ጠበበውና “ይለወጥልኝ፤ ጠበበኝ” ብሎ ጠየቀ። “እዚህ ሆስፒታል ከዚህ የሰፋ ዊልቸር የለም፤ ግርማዊ ጃንሆይ ሲመጡ እሳቸውን ቢጠይቋቸው ከልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ያስመጡልዎታል>>አሉት። በሚመጡበት ቀን ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ፀሐይ እየሞቀ ጠበቃቸው። ጃንሆይ መጡ።

“ጃንሆይ! ዊልቸሩ ስለጠበበኝ ከልዕልተ ፀሐይ ሆስፒታል እንዲመጣልኝ እባክዎ ይዘዙልኝ>> አላቸው። <<ጃገማ! ቢታዘዝልህም አይበቃህም… አንተ እኮ ወፍረሃል" አሉት እይሳቁ። "ጃንሆይ መወፈሬን አይጥሉት…. የወፈረ ወታደር አይሸሽም" አላቸው ጄነራል። "እሱን ተወው ጃገማ! እኛ ብዙ አይተናል፤ ገና ጦርነት ሊጀመር ኋላ እንዳይቀር ቀድሞ የሚሸሸው እሱ ነው" አሉት። ሁለቱም በጥያቄና መልሱ ፍርስ ብለው ሳቁ ከዚያ ለተሽከርካሪ ወንበሩም፣ ለ’ፊዚዎቴራፒ’ም ወደ ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ተዛውሮ እንዲተኛ ተፈቀደ። በሆስፒታሉ አንዲት ፈረንሳዊት ‘ፊዚዎቴራፒስት’ ነበረች። አምስት ወር እግሩ ላይ የቆየው ብረት እግሩን ሲያንቀሳቅስ እንደሚያመው ነገራት። አልሰማችውም፤ የእሷን ትዕዛዝ የሚቀበሉት ረዳቶቿም በግድ አነቃንቅ እያሉት ተሰቃየ። አንድ ቀን ፈረንሳዊቷ መጣችና "እግርህን አንቀሳቅሰው!" አለችው። <<ያመኛል>> አላት።
<<አያምም፤ አንቀሳቅሰው! >> አለችው።
<<እሺ ወደ እኔ ጠጋ በይ>> አላት። ጠጋ ስትል በቀኝ እጁ ፅጉሯን ጭምድድ አድርጎ ያዛትና << ያማል?>> አላት፤ እያቃሰተች <<…_ኦ! በጣም ያማል >> አለችው።
<<ይኸውልሽ ፤ እኔንም እንደዚህ ነው የሚያመኝ >> አላት። ፈረንሳዊቷ “ፊዚዎቴራፒስት” ገባት፤ በጣም ገባት! <<ከዛሬ ጀምሮ ያመዋልና ጅምናስቲክ ስራ ብላችሁ እንዳታስቸግሩት>> ብላ አዘዘች።

‹‹ገዳይ በልጅነቱ
ዶቃ ሳይወጣ ከአንገቱ
ጃጌ ጃገማቸው
እንደገጠመ የሚፈጃቸው
በአባት በእናቱ ኦሮሞ
ፍዳውን አስቆጠረ ከምሮ ከምሮ!›› ተብሎላቸዋል።

ጥር 20 1913 ዓ.ም. የተወለዱት አርበኛ ሌፍተናንት ጄነራል ጃገማ ኬሎ ዛሬ በህይወት ቢኖሩ 100 ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ያከብሩ ነበረ ። መልካም ልደት ለጀግኖች አባቶቻችን ይኹን! ምንጭ ጃገማ ኬሎ የበጋው መብረቅ (የሕይወት ታሪክ) ከ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ ገጽ 190-191

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *