ኢዜማ የቀድሞው የአዲስ አበባ ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ በህግ ሊጠየቁ ይገባል አለ

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በነበሩት 2 ዓመታት ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባን በም/ከንቲባነት ያስተዳደሩት ኢ/ር ታከለ ኡማ በህግ መጠየቅ አለባቸው የሚል አቋም እንዳለው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ ኢ.ዜ.ማ አስታውቋል፡፡

ፓርቲው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ አዳነች አበቤ፣በከተማይቱ ስለተፈፀመው የመሬት ወረራ፣የቤቶች ዕደላ እና በሌላም ህገ-ወጥ ተግባር ዙሪያ ትናንት መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው ይህን ያለው፡፡

የኢዜማ የኮሚዩኒኬሽን ሀላፊ አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ ሲናገሩ፣ከዚህ ቀደም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በአዲስ አበባ ስለተፈፀሙ ተመሳሳይ ህገ-ወጥ ተግባራት ፓርቲያቸው በዝርዝር ሪፖርት አቅርቦ እንደነበር አስታውሰው፣ለዚህ ደግሞ የቀድሞው የከተማይቱ ም/ከንቲባ ታከለ ኡማን ጨምሮ በጊዜው በሀላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ሁሉ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ኢዜማ ፅኑ አቋም ይዟል ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ትናንት ም/ከንቲባ አዳነች አበቤ ያቀረቡት ሪፖርት፣ከለውጡ ወዲህ በተፈፀሙት ህገ-ወጥ ተግባራት ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ችግሩን ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ከነበረው ሂደት ጋር ይበልጥ ለማያያዝ መሞከሩ አግባብነት የለውም ነው ያሉት የኢ.ዜ.ማ የኮሚዩኒኬሽን ሀላፊ አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እራሱ ባደራጀው ቡድን አካሄድኩት ባለው ጥናት፣322 ባለቤት አልባ ህንጻዎች፣ከ13 ሚልየን ካሬ ሜትር በላይ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ቦታዎች እና ከ21ሺ በላይ ባልተገባ ወገን ባለቤትነት ስር የሚገኙ የጋራ-መኖሪያ ቤቶች መገኘታቸውን፣የከተማወ ም/ከንቲባ አዳነች አበቤ ትናንት በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር፡፡ ብስራት ሬዲዮ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *