በቢጫ ለባሾቹ ምክንያት የእነ ጃዋር ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠበት

ቢጫ ቀለም ልብስ በለበሱ ግለሰቦች ምክንያት የእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የዛሬ ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠበት። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ አንደኛ ችሎት ዛሬ ማለዳ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሊቀበል ቀጠሮ ይዞ ነበር።

ይህን ተከትሎ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በዚህ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ተከሳሾች ፍርድ ቤትየቀረቡ ቢሆንም ችሎቱ ግን ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት አሰናብቷቸዋል።
ይሀህ ሊሆን ቻለው የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል ቢጫ ልብስ ለብሰው በፍርድ ቤት የተገኙ ሰዎች ወደ ፍርድ ቤቱ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ተከትሎ ተከሳሾች እና ጠበቆች ባሰሙት አቤቱታ ነው።

ከተከሳሾች መካከል አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሐምዛ አዳነ ሰዎች ቢጫ ቀለም ያለው ልብስ በመልበሳቸው ወደ ፍርድ ቤት እንዳይገቡ መደረጉ አግባብ አይደለም፤ ቢጫ ልብስ በመልበሳቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ አሉ ሲሉ ቅሬታቸውን ለፍርድ ቤት አቅርበዋል።

ባለ ቢጫ ቀለም ልብስ የመልበስ ዘመቻ ከሰሞኑ በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በርካቶች ቢጫ ልብስ የመልበስ ዘመቻ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ይህም ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እና ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የሚለብሱትን ባለ ቢጫ ቀለም ቱታ ለመወከል ነው።

ተከሳሾች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፤ ለተከሳሾች የሞራል ድጋፍ ለመስጠት ቢጫ ቀለም ያላቸውን ልብሶች በመልበስ በፍርድ ቤት እንደሚገኙ የዘመቻው አካል የሆኑት ይናገራሉ። ባለፉት ሁለት ቀጠሮዎች በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥራ የተከሰሱ ተከሳሾች ፍርድ ቤት በቀረቡብት ወቅት ቢጫ ቀለም ያለው ልብስ ለብሳ ከፍርድ ቤት የተገኘችው መሠረት ዳባ፤ ይህ ዘመቻችንን ለተከሳሾች የሞራል ብርታትን ለመስጠት ነው ትላለች።

“እነሱ ከሚለብሱት የልብስ ቀለም ጋር ተመሳሳይ ልብስ በመልበስ ‘እኛም ከእናንተ ጋር ነን’፣ ‘ከእናንተ ጋር ታስረናል’ የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ፈልገን ነው” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች። ባለ ቢጫ ቀለም ልብስ የመልበስ ዘመቻ አስተባባሪ የሆነው ወቢ ቡርቃሳ የጀመሩት ዘመቻ በርካቶችን በማሳተፍ ከታሰበው በላይ ብዙ ሰዎች ጋር መድረሱን ይናገራል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *