ኢዜማ አዲስ አበባን በሚገባ የሚወክሉ ሦሥት ፕሮፌሰሮችን አሰልፏል

ሦሥቱ ፕሮፌሰሮች የአዲስ አበባ ወኪሎች በይመስገን መሳፍንት፡፡ ኢዜማ በምርጫ ወረዳዎች ተደራጅቶ ለምርጫው ዝግጅቱን ሲያቀጣጥል በምክንያት ነበረ፡፡ በውስጠ ፓርቲ ምርጫ እጩዎቹን ወደ ፊት ያመጣው ፓርቲያችን በወረዳው ነዋሪ የተመሰከረላቸው፣ ጉምቱ፣ የበቁ፣ የነቁ እና የሚያነቁ ሆነው ያገኛቸውን እጩዎች ለተወካዮች ምክርቤት እና ለክልል ምክርቤት እነሆ ብሏል፡፡ ከነዚህ መሀከል አዲስ አበባን በሚገባ የሚወክሉ እና በህግ ማውጣት እና ማስፈጸም ግንባር ቀደም የሚሆኑ ሦሥት ፕሮፌሰሮችን አሰልፏል፡፡ በዛሬው ጽሁፌ ማስተዋወቅ የማይፈልጉትን ኃያላን በጨረፍታ ላሳይ እወዳለሁ፤ ተከተሉኝ

1 ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ፤ የኢዜማ መሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ በምርጫ ወረዳ 23 ለተወካዮች ምክርቤት የኢዜማ እጩ ናቸው፡፡ ፕሮፍን ማስተዋወቅ ለቀባሪው ማርዳት ነው፤ ሆኖም ግን ይህን የልጅነት አርአያዬን በመድረክ ያገኘሁበትን አጋጣሚ አስታውሼ ልጽፍ ወደድኩ፡፡

ቀኑ ታህሳስ 8 ነው፤ 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ፣ በጌትፋም ሆቴል ኢዜማ ለወራት የደከመበትን ፖሊሲዎች ለስራ አስፈጻሚ እና ለዘርፉ ምሁራን የሚያቀርብበት ሁለተኛ ቀን ነው፡፡ ታህሳስ 7 እና 8 በነበረን አጠቃላይ ውሎ 8 ፖሊሲዎች የቀረቡ ሲሆን እኔ የምመራው የማህበራዊ ከለላ ፖሊሲ ግን የቀረበው በሁለተኛው ቀን ከሰዓት በኋላ በመሆኑ ዝግጅቴን አጠቃልዬ ከመድረክ ወጣሁ መድረኩን አቶ ጫኔ ተመስገን እና አቶ አማንይሁን ረዳ ተጋርተውኛል፡፡

በሁለት ቀናት ውሎ የተሰላቸውን ታዳሚ ዘና አድርጌ ልጀምር በማለት እንደ ማሳያ የሚያገለግል የአንድ ቤተሰብ ታሪክን በልብወለድ መልክ አዘጋጅቼ በንባብ አሰማሁ፡፡ የባለ ታሪኬ ስም አቶ ብሩ ነበር፡፡ የአቶ ብሩ ቤተሰብ በሴፍቲ ኔት ድርጎ የሚሰፈርለት አካል ጉዳተኛ፣ አቅመ ደካማ፣ ባልቴት እና ስራ ፈት ወጣት በቤቱ ያለው ቤተሰብ ያለበትን ጣጣ የሚወከል አድርጌ ታሪኬን ቀንብቤው ነበር፡፡

የፖሊሲውን መርሆች፣ አቅጣጫዎች እና የትግበራ ማዕቀፍ አስከትዬ አቅርቤ አመስግኜ ቁጭ አልኩ፡፡ መድረኩ ለጥያቄ እና መልስ ክፍት ሆነ፡፡ አከታትለው ጥያቄ ያሰሙ ቢኖሩም የማልረሳው ገጠመኝ ከመሪያችን ተሰነዘረልኝ፡፡ እሳቸውም ጥያቄ ሲጀምሩ “አቶ ብሩ በመንግስት የሚረዱበት ምክንያት እና እኛ የማህበራዊ ከለላን የምንሰጥበት ምክንያት በፖሊሲ ሰነዱ… ” ተካቶ እንደሆነ ጠየቁኝ፡፡ በማስታወሻዬ ጥያቄውን ጽፌ ተሰናዳሁ እድሉ ሲሰጠኝ መሪዬን ፈገግ ያሰኘ ሀሳብ ይዤ መልሴን አንድ አልኩ፡፡

አቶ ብሩ የሚለውን ሀሳብ ራሱ ከራሱ ከፕሮፍ የወሰድኩት እንደሆነ አስታወስኩት፡፡ ወቅቱ የሚሊኒየሙ አከባበር የጦፈበት ጊዜ ነበር 2000 ዓ.ም፡፡ በእስር የተፈቱት የቅንጅቱ መሪዎች በሰሜን አሜሪካ የፖለቲካ ጉዞ እያደረጉ ነው፡፡ በዋሺንግተን ዲሲ በአዳራሽ ተሰብስቦ ለሚጠብቃቸው ኢትዮጵያዊ ንግግር ለማድረግ የተሰየሙት ዶክተር ብርሀኑ ነጋ በእስር አብረዋቸው ከማቀቁ ኢትዮጵያውያን መሀከል አንዱ የሆኑትን አቶ ብሩን አንስተው አወጉ፡፡ ስርዓቱ ኦሮሞን ሁሉ ኦነግ ሲል በእስር ያንገላታል ሲሉ መሬታቸውን ተቀምተው ከነልጃቸው የታሰሩትን አቶ ብሩን አነስተው ዘለግ ያለውን ጽሁፋቸውን ቀጠሉ፡፡ ከዚያ ወዲህ እንዲህ የማሳያ ታሪክ ስፈልግ እኔም አቶ ብሩን ለማስታወስ አቶ ብሩ ብዬ እጀምራለሁ አልኳቸው፡፡ ፕሮፌሰር የመደነቅ ፊት ከፈገግታ ጋር አሳዩኝ፡፡ እኔም ወደ መልሴ ገባሁና ማህበራዊ ፍትህን የፖለቲካ ፍልስፍናው ላደረገ ፓርቲ ማህበራዊ ከለላ ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን አጣቅሼ የእሳቸውን ሀሳብ ቀምሬ ሰነዱን እንደማስተካክል አስረዳሁ፡፡

ሁለት ጊዜ የሞት ፍርድ የተፈረደበት፣ እህቱን በፖለቲካ ትግል መስዋዕት ያደረገ፣ በኪስ ሳይሆን በሳምሶናይት የማይያዝ ወርሐዊ ደሞዝ ትቶ ለትግል ጫካ የወረደ፣ ኢሰመጉን እና የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበርን የመሰረት፣ የ97 ዓ.ም ትግል ፈርጥ፣ የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝ፣ የብሔራዊነት ስሜት ማሳያ የሆነ የፓርቲያችን መሪ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ቦንገር ማለት ይህ ነው፡፡ ካለኝ ጥልቅ ፍቅር ስሜት ይዞኝ ብዙ ባላስተዋውቀው እንኳን ስለ ትምህርት ዝግጅቱ አንዳንድ ልበል፡፡

ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የተወደለዱት ቢሸፍቱ ሲሆን አዳማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ተከታትለው ለዩንቨርሲቲ ትምህርት ቢበቁም እህታቸውን ባጡበት የኢህአፓ ትግል ውስጣቸው ተማርኮ በገጠርም በከተማም ትግል አድርገዋል፡፡ የዩንቨርሲቲ ትምህርት በአሜሪካ በማግኘት በኒው ፕላትዝ የሚገኘው ኒውዮርክ ስቴት ዩንቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በኒው ስኩል ኦፍ ሶሻል ሪሰርች የማስተርስ እና ፒ ኤች ዲ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ በበክኔል ዩንቨርሲቲ በማስተማር የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ከባለቤታቸው ዶክተር ናርዶስ ምናሴ ሁለት ወንድ ልጆችን አፍርተዋል፡፡

2 ፕሮፌሰር በፍቃዱ ደግፌ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ትምህርት የራቃቸው ታጋዮች የተማረ ሰው ሲያዩ ዓይናቸው ይቀላ ነበር፡፡ ምሁር ለህሊናው እንጂ ለሌላ ነገር አይገዛምና ይይዙት ይጨብጡት ሲያጡ ከ40 በላይ ምሁራንን ከአዲስ አበባ ዪንቨርሲቲ አሰናበቱ፡፡ በወቅቱ ከተባረሩት ጉምቱዎቸ መሀከል አንዱ የነበሩት የያኔው ዶክተር በፍቃዱ ደግፌ ኢኮኖሚስት እና የአደባባይ ምሁር ሆነው ዘለቁ፡፡ በ1997 መጀመሪያ ከሌሎች ሦሥት ጓዶቻቸው ጋር ሆነው ቀስተደመናን መሰረቱ እና የቅንጅቱን ብስራት አንድ አሉ፡፡

ፕሮፌሰር በፍቃዱ በገንዘብ ፖሊሲ እና በማክሮ ኢኮኖሚ ሰነዳችን ዝግጅት ላይ ያላቸው ሚና ጉልህ ነበር፡፡ ለወጣቶች ዕድል እንስጥ ብለው ከምርጫው ሊያፈገፍጉ ቢሞክሩም ጠንካራው የእጩ ምልመላ ክፍላችን ወትውቶ ለወረዳ 24 የተወካዮች ምክርቤት እጩነት ጠቆማቸው፡፡ ጠቅላላ ጉባኤው ፊት ቀርበው ራሳቸውን በ5 ደቂቃ ገለጹ ይሁንታንም አገኙ፡፡ እንዲህ ያሉ ጉምቱዎች ለእኛ ለወጣት ፖለቲከኞች ትምህርት ብቻ ሳይሆኑ የህይወት ምሳሌ ናቸው፡፡ በእሳቸው ላይ ያየሁት እርጋታ የሰከነ ፖለቲካ ለምናራምድ ለእኛ የሚነበቡ መጽሐፍ ናቸው፡፡

3 ፕሮፌሰር ዳዊት አባተ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህር ናቸው፡፡ የኢዜማን የትምህርት ፖሊሲ በማዘጋጀት የነበራቸው የቡድን መሪነት ሚና ነበር፡፡ ከምንም በላይ የሚወዳደሩት በአዲስ አበባ ከተማ ሰፊ በሆነው የምርጫ ወረዳ መሆኑ ገዝቶኛል፡፡ ወረዳ 17 ማለት ድፍን ቦሌን የያዘ ነው፡፡ ቦሌ ክፍለከተማ ደግሞ ከቦሌ ቡልቡላ፣ ቦሌ ሚካኤል፣ ቦሌ ርዋንዳ፣ ቦሌ መድሀኒያለም፣ ገርጂ፣ አያት፣ ጉርድሾላ፣ ሲኤምሲ፣ ሰሚት፣ አራብሳ፣ ጎሮ፣ መብራት ኃይል፣ ፊጋ፣ በሻሌን ይዞ እስከ መገናኛ የሚዘልቅ ነው፡፡ እዚህ ያልገለጽኳቸው ውብ ሰፈሮችም እንዳሉ ደምሩበት፡፡ እናም ፕሮፌሰር ዳዊት አባት ህዝን በማንቃት ያላቸውን ሰፊ የማስተማር ልምድ እንደሚተገብሩበት በማመን በወረዳ 17 ያገኙትን ይሁንታ መሬት አውርደው እንደሚያሳዩን አልጠራጠርም፡፡

ኢዜማ ቤት ያሉት ምሁራን እኝህ ብቻ አይደሉም፡፡ መች ቆነጠርንና ውቅያኖስን በጭልፋ ነው ነገሩ፡፡ ሌሎቹን በማስተዋወቅ እመለሳለሁ፡፡ በመጨረሻ ግን ፓርቲያችንን ለየት የሚያደርጉትን አራት ነገሮች ጠቁሜ ልሰናበት፡፡

1 የዜግነት ፖለቲካ፡ አገራዊ እሳቤ እንጂ የመንደር ስብስብ እና ዘውግ ማንነት ላይ ያልተንጠለጠልን መሆናችን፡፡ 2 ማህበራዊ ፍትህ፡ የሐብት ልዩነቱ በሰፋባት አገራችን እኩል እድል እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማስፈን የሚረዳ የፖለቲካ ፍልስፍናችን ነው፡፡

3 ዋናው ስልጣን የወረዳ ሆኖ መደራጀታችን፡-በአገራቀፍ ደረጃ በ434 ወረዳዎች አደረጃጀት ያለን መሆናችን እና ወረዳዎች እራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ መሻታችን በፕሮግራም እና በህግም ይህን ማቀንቀናችን 4 የመሪ እና የሊቀመንበር መዋቅር አበጅተን ፖለቲካ እና የመንግስት ስራን ለይተን መጀመራችን ናቸው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *