አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ አረፈ
By: Date: January 21, 2021 Categories: ዜና Tags:

ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ ባደረበት ህመም ምክንያት በሀገር ውስጥና በጀርመን ሀገርም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ86 ዓመቱ ለረጅም ዓመታት በኖረባትና በሙያው በሠራባት ጀርመን ሀገር ፍራንክፈርት ከተማ ነው ሕይወቱ ያለፈው። ጌታቸው ደስታ ከቀደምት የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አንዱ ሲሆን በተለይ በዘርፉ ፈር ቀዳጅ ከሚባሉትና እጅግ ዝናን ካተረፉ ጋዜጠኞች አንዱ ነበር።

አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ ባሕላዊ ትምህርቱን ለድቁና በሚያበቃው ደረጃ ተምሯል: ዘመናዊ ትምሕርቱንም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እና በባሕር ዳር ፖሊቴክኒክ ትምሕርት ቤት ተከታትሏል፡፡ ከዚይም ተመርቆ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኢትዮጵያ ሬዲዮ በወጣው ማስታወቂያ ተወዳድሮ በመቀጠር ለረጂም ዓመታት አገልግሏል፡፡

እዚያ በሥራ ላይ እያለ የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ተወዳድሮ አብላጫ ውጤት በማግኘት ኒውዮርክ በሚገኘው የመንግሥታቱ ሬዲዮ ጣቢያ ላይ በትጋት ሠርቶ ኮንትራቱ በማለቁ ተመልሶ ወደ ነበረበት የኢትዮጵያ ሬዲዮ መጥቶ በማገልገል ላይ እንዳለ፤ እንደገና ወደ ጀርመን በመሄድ በቀድሞ አጠራሩ የጀርመን ድምፅ በአሁኑ ዶቼ ቬሌ ሬድዮ ለዓመታት ሲሠራ ቆይቶ በራሱ ጥያቄ የጡረታ መብቱ ተጠብቆለት ወደ ሀገሩ ተመልሷል።

ተወዳጁ ጋዜጠኛ ጌታቸው ከአብራኩ የተገኙ ሁለት ልጆች ሲኖሩት፤ ከእነሱ ሌላ እንደልጆቹ ያሳደጋቸውና በስስት አባታችን እያሉ እሱም ልጆቼ የሚላቸው በሕመሙ ሳይለዩት በሀገር ውስጥና ጀርመንም ከሄደ አንስቶ ካጠገቡ ያልተለዩ አምስት ልጆችም አሉት። ቤተሰብ ወዳጆቹ በህመሙ ወቅትና ወደ ውጭም ለህክምና በሄደበት ጊዜ በአካልም በስልክም በኢሜይልም ጥየቃችሁ ላልተለያቸው ሁሉ ምስጋናችን ይድረሳችሁ ብለዋል::

ከእናቱ ከወይዘሮ በላይነሽ ሀብተ ማርያምና ከአባቱ ከግራአዝማች ደስታ አርአያ አዲስ አበባ ፈረንሳይ ኤምባሲ አካባቢ የተወለደው የታዋቂው ጋዜጠኛ ጌታቸው ደስታ አስከሬኑ በዛሬው ዕለት ከጀርመን ወደ ሀገሩ የገባ ሲሆን የቀብር ስነ ስርአቱም ነገ ዓርብ ጥር 14ቀን 2013 ዓም ከቀኑ በ9.00 ሰዓት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሤ ካቴድራል እንደሚፈጸም ቤተሰቦቹ ገልጸዋል። ከቀብሩ ሥርአት በሁዋላ በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ባለው አዳራሽ የተዘጋጀውን ጠበል ጠዲቅ በመቅመስም ስንብቱ በዚያው እንደሚሆን ቤተሰቦቹ ገልጸዋል። ሠልስትም አይኖርም:: ዶቸቨለ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *