“ሱዳን ድንበራችንን አልፋ እንድትገባ የተደረሰ ስምምነት የለም” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ እንድትጠብቅም ሆነ መሬት እንድትይዝ የተደረሰ ስምምነት እንደሌለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጥር 12/ 2013 ዓ. ም በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

መንግሥት ህግ ማስከበር በሚለው ወታደራዊ ዘመቻ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባቀናበት ወቅት ድንበር አካባቢ ሊከሰቱ የሚችሉ የደህንነት ስጋቶችን በተመለከተ ከሱዳን ጋር መግባባት ተደርሶ ነበር ብለዋል።

“ድንበር አካባቢ የሁለቱን አገሮች ደህንነት የሚጎዳ እንቅስቃሴ እንዳይኖር በኛ አመራር ለሱዳን መንግሥት አደራ ተሰጥቷል” ያሉት ቃለ አቀባዩ አክለውም ሆኖም “ድንበሩን አልፈው አገራችን ግቡ መሬት ይዛችሁ ጠብቁልን የሚል አይነት ሊኖር የሚችል አይደለም፤ አልነበረም” ብለዋል።

ከሰሞኑ የሱዳን ምክር ቤት ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ሱዳን ሰራዊቷን ወደ ድንበር ያስጠጋችው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብይ አህመድ ጥያቄና ፈቃድ ነው መባሉ ተዘግቧል።

ለዚህም ምላሽ የሰጡት ቃለ አቀባዩ “ቅዠት ነው” ካሉ በኋላም “አጥፊ ኃይሎች የናንተን ድንበር ተጠቅመው ወደኛ ድንበር እንዳይገቡ ማለት ኑና ገብታችሁ ጭራሽ ያልተከለለና መቶ አመት በዚሁ ሁኔታ ይሁን ተብሎ የቆየውን መሬት ድንበር የኛ ነው በሉ ማለትም አይደለም” ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *