የተቀናጀ የፋይናንስ መረጃ ሥርዓት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ይፋ ተደረገ

የመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር ለማሻሻል የበጀት፣ የፋይናንስና የሒሳብ አያያዝ ሥራዎችን የሚደግፍ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት (IFMIS) ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ይፋ መደረጉን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ይህ የተገለጸው አዲሱ የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ (2021-2025)፣ ለዋና ዋና ባለድርሻ አካላት፣ ሰኞ ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በቀረበበት ወቅት ነው፡፡

በሁለተኛው ስትራቴጂካዊ ዘመን ሊደረስባቸው የታለሙ ቁልፍ ውጤቶችን ያብራሩት የገንዘብ ሚኒስትር የመረጃ ሥርዓቱ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነጋ መንግሥቱ፣ የፕሮግራሙን ውጤታማነት ለማሳደግ የተሻሻሉ መሠረተ ልማቶች በመጠቀምና ተቋማዊ አሠራሮችን የበለጠ በማሳደግ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ተጨማሪ 760 ጣቢያዎችን ለመድረስ ገንዘብ ሚኒስቴር እየሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የመረጃ ሥርዓቱ ስትራቴጂካዊ ዕቅድ በሚኒስቴሩ እየተከናወኑ ከሚገኙ የተለያዩ የፋይናንስ አስተዳደር ማሻሻያዎች ጋር የተያያዘና ለኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል፣ ለበጀት አመዳደብ፣ የገቢ አሰባሰብና የወጪ አያያዝን ለማዘመን የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግሥት ፋይናንስ ሥርዓን ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

በመጀመሪያው የስትራቴጂክ ዘመን (2016-2020) በመረጃ ሥርዓት ፕሮግራሙ ወደ 156 ጣቢያዎች መከፈታቸውን የገለጹት አቶ ነጋ፣ ስለፕሮግራሙ ለ14,773 የመጨረሻ ተጠቃሚዎች ሥልጠና መሰጠቱንና የፕሮግራሙን ትግበራ ለመደገፍ የሚያስችል በቂ የውስጥ አቅም መገንባቱን አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ከፌዴራል መንግሥት በጀት ውስጥ 84 በመቶ የሚሆነው በፕሮግራሙ እየተዳደረ መሆኑን፣ በመጀመሪያው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ወቅትም ከ25 ሚሊዮን በላይ ግብይቶችን ማስተናገዱን አቶ ነጋ አስረድተዋል፡፡

ስትራቴጂካዊ ዕቅዱን ገንዘብ ሚኒስቴር ከሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ግዥና ገቢ ከመሳሰሉ የመረጃ ሥርዓቶች፣ ከብድር አስተዳደር፣ ከፋይናንስ መረጃ ትንተና፣ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ እንዲሁም ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር የማዋሀዱን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የተቀናጀ የፋይናንስ አስተዳደር መረጃ ሥርዓት (IFMIS) ስኬታማ ትግበራ፣ ወቅታዊ፣ ተገቢና አስተማማኝ የፋይናስ መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት እንደሚያስችል ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሪፖርተር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *