ከደቡብ ክልል ለኮይሻ ፕሮጀክት ግንባታ ከ230 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ
By: Date: January 20, 2021 Categories: ዜና Tags:

የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካል የሆነው እና በደቡብ ክልል ለሚገኘው የኮይሻ ፕሮጀክት ግንባታ ከ230 ሚሊየን ብር በላይ ከክልሉ መንግስት ሰራተኞች እና የህብረተሰብ ክፍሎች መሰብሰብ መቻሉ ተገለጸ።

የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተጠናቀቁ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በታቀደለት አላማ ግቡን እንዲመታም ከገንዘብ ማሰባሰቡ በተጨማሪ የፕሮጀክትን ስራ ለሚያከናውኑ ባለሙያዎች ድጋፍ እየተደረገ ነው። የፕሮጀክቱ የጥናት ስራዎችም ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ከተቋቋመው ብሄራዊ ኮሚቴ ጋር በጋራ የማጠናቀቅ ስራን ክልሉ እየሰራ መሆኑን እና የጥናት ሁኔታው ያለበትን ደረጃ በተመለከተም አቶ እርስቱ ተናግረዋል።

የቱሪዝም መዳረሻ ይሆናል ተብሎ በታመነበት በዚህ ፕሮጀክት የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ የማድረግ ስራዎችም ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት። ባለሀብቶች ወደ ፕሮጀክቱ እንዲገቡ ለማድረግ እና ከወዲሁ የማስተዋወቅ እና የማፈላለግ ስራ እንዲሁም ባለሃብቶቹ ሲገቡም ምቹ መሰረተ ልማት እንዲኖር ማድረግ እና መሰል ለፕሮጀክቱ ድምቀት የሚሆኑ ተግባራትም በስፋት እየተሄደባቸው እንደሚገኝም አቶ እርስቱ ገልጸዋል።

ከዚህ ባለፈም ትልቅ ሆስፒታልም በፕሮጀክቱ አቅራቢያ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩም ተገልጿል። ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት የታደለና እምቅ የቱሪዝም ሀብት ያለው ከመሆኑ የተነሳ በዚህኛው ፕሮጀክት ያልታዩ የጎብኚ መዳረሻዎችን ለማሳየት እና በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ እንደሚያስችልም ነውየተናገሩት።

አያይዘውም ከክልሉ አልፎ ለአጎራባቸ ክልል ወጣቶች በፕሮጀክቱ ሰፊ ጊዜያዊ እና ቋሚ የስራ እድል እንደሚፈጠርም ጠቅሰዋል። የኮይሻ ፕሮጀክት ለክልሉም ሆነ ለሀገር የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ በኩል ትልቅ ሚና የሚጫወት እና የቱሪዝም ከተማን ለመፍጠር የሚያስችል እንደሚሆን ታምኖበታል። ገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ግንባታው በተጀመረ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዟል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *