የጤና ሚንስቴር መረጃ እንደሚያሣየው በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካይ ከ14 ሺህ በላይ እናቶች በወሊድና ከወሊድ ጋር በተገናኘ ችግር ህይወታቸው ያልፋል፡፡በአለም ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው እናቶች ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ምክንያት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ከእዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት እናቶች ለህልፈት የሚዳረጉት በደም መፍሰስ ሳቢያ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የእናቶች ሕጻናትና ስርዓተ ምግብ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በተለይም ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ ፣ ወደ ጤና ተቋማት ሄደው የማይወልዱ እናቶች መኖር የመሰረተ ልማት እና የህክምና ግብዓቶች እጥረት እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ስነ-ምግባር ችግር ለእናቶች ሞት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
አሁን ላይ 51 በመቶ የሚሆኑ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት እንደሚሄዱ ዶ/ር መሰረት የተናገሩ ሲሆን ይሁን እንጅ አሁንም ቢሆን ከእርግዝና እና ከወሊድ ጋር ተያይዞ በርካታ እናቶች ህይወታቸው ያልፋል ሲሉ አንስተዋል፡፡
የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል ተብሏል።የጤናማ እናትነት ወር ዘመቻ ከጥር አንድ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ በደም መፍሰስ ምክንያት እናት ለምን ትሙት በሚል መሪ መልዕክት እየተከበረ ይገኛል።