በሀላባ ከተማ ከጥምቀተ ባህር ወደየደብራቸው በሚመለሱ ታቦታት ላይ ድንገተኛ
By: Date: January 20, 2021 Categories: ዜና

በሀላባ ከንባታ ጠንባሮ ሀገረ ስብከት በሀላባ ከተማ በትላንትናው ዕለት ታቦታቱ ከባህር ጥምቀት በመንሳት ወደየደብራቸው ሊለያዩ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀር ሆን ተብሎ የድንጋይ ውርወራ በመጀመሩ ጉዟቸውን ያደርጉ የነበሩ ታቦታት ወደደብራቸው ሳይደርሱ ጉዟቸውን አቋርጠው በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን እንዲገቡ ተደርጎ ጉዞው ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ መቆየቱ ተገለፀ።

ለበርካታ አመታት የማርያምና የቅዱስ ገብርኤል ታቦታት ኑር መስጊድ አቅራቢያ በሚገኘው አደባባይ ስብሐተ እግዚአብሔር (ወረብ ) በማቅረብ የሚለያዩ ሲሆን ነገር ግን ይህ ከመሆኑ በፊት ህዝበ ክርስቲያኑ ባላሰበው ሁኔታ አንዳንድ አክራሪዎች የድንጋይ ውርወራ አድርገዋል። በዚህም ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ያልታወቁ ምዕመናን የተጎዱ ሲሆን አንዳንዶችም በግፊያና በመረጋገጥ ሳይጎዱ እንዳልቀረ ተገምቷል።

ይህ ሁኔታ ተባብሶ በመቀጠሉና የከተማው ፓሊስ አባላት ከአካባቢው በመሸሻቸው የቃልኪዳኑን ታቦት ያከበሩት ካህናት ጉዟቸውን ከቀኑ ስድስት ስዓት በማቋረጥ ወደ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊገቡ ችሏል ።

ጥር 10 ቀን ከየመንበረ ክብራቸው በመውጣት በጥምቀተ ባህሩ ቦታ የቆዩት ታቦታት በካህናትና በምዕመናን ታጅበው ጥር 11 ሲመለሱ ለሌሎች ኃይማኖቶች የረጅምልዩ ክብር በመስጠት የሰዓት ገደብ ጭምር በማድረግ ለረጅም ጊዜ የሃይማኖት መቻቻል ማሳያ መሆኑ ቢታወቅም ጠብ አጫሪ የሆኑ ግለሰቦች ተቀናጅተው በሀገሪቱ ብሔራዊና ሃይማኖታዊ በዓል ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

የችግሩን መከሰት ተከትሎ የከተማውን ፖሊስ ተክቶ የሰላም ማስከበሩን ስራ የደቡብ ክልል ልዩ ኃይልና የፌድራል ፖሊስ አባላት ተቀናጅተው ግጭቱን በቁጥጥር ስር ያዋሉት ሲሆን የዞኑ ዋና አስተዳደሪ ዶ/ር መሃመድ ጉዳዩ የእስልምና እምነት ተከታዮችን የማይወክል መሆኑን በመግለፅ ከጸጥታ አካላቱ ጋር ባደረጉት ጥረት ህዝቡ በጽናት በመጠበቅ ከቀኑ አሥር ሰዓት በቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የቆዩት ታቦታቱ ወደየደብራቸው ተመልሰው እንዲገቡ ተድርጓል።

ዛሬ ጥር 12 ቀን የሚከበረው የቃና ዘገሊላ በዓል አከባበር በምን ሁኔታ መካሄድ እንዳለበትና የጸጥታውን ደህንነት አስመልክቶ የአካባቢው ቤተ ክህነት ኃላፊዎችና የመንግስት አካላት በጋራ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገልጿል።

በጥምቀተ ባህሩ የሚገኘው ታቦተ መድኃኔ ዓለምና ቅዱስ ሚካኤል ነገ ወደመንበረ ክብራቸው እንደሚመለሱ ይታወቃል። በ2004 ዓ.ም ተመሳሳይ ችግር የደረስ መሆኑ የሚታወስ ነው። በሀላባ ከተማ የሚገኘውን የጥምቀተ ባህር ቦታ ለዚሁ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲሰጥ ካርታና ፕላን ቤተክርስቲያናችን ከአሥር አመታት በፊት የተረከበች መሆኑም አይዘነጋም። (የምዕራብ አርሲ ሀገረ ስብከት)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *