ፖሊስ በጥምቀት በዓል ላይ ወንጀል ለመፈፀም ተዘጋጅተው የነበሩ 205 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የህብረተሰቡን ጥቆማ መነሻ አድርጎ ባደረገው ጥናት በጥምቀት በዓል ላይ ወንጀል ለመፈፀም ተዘጋጅተው የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በተለይም በበዓላት መዳረሻ ወቅቶች እንደሚያደርገው ሁሉ የ2013 ዓ/ም የጥምቀት በዓልን ህብረተሰቡ በሠላም እንዲያከብር ቅድመ ዝግጅቱን ጨርሶ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡ ይህ በዓል በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ኃይማኖታዊና ትውፊታዊነቱን ጠብቆ ሠላማዊ በሆነ መንገድ እንዲከበር ፖሊስ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ከህብረተሰቡ የመጣውን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ባደረገው ጥናት፣ የማስረጃ ማሰባሰብና የቁጥጥር ተግባራት በቀጥታ በወንጀል ተሳታፊ የሆኑ 205 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ቀደም ሲል በደረሱት ጥቆማዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ለወንጀል ድርጊት ያዘጋጁት ሰነድ አልባ ሦስት ተሽከርካሪዎችም ተይዘዋል፤ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይም የምርመራ መዝገብ በማደራጀት ወደ ስራ ገብቷል፡፡

በተመሳሳይ ኮሚሽኑ በአስሩም ክ/ከተማ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማና ይህንንም ጥቆማ መሰረት አድርጎ ባደረገው የቁጥጥር ተግባራት በዓሉ በሠላም እንዳይከበርና ሁከት እንዲነሳ ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ የነበሩ ከሦስት መቶ በላይ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን ገልጿል፡፡ ግለሰቦቹ ለወንጀል መፈፀሚያነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ድምጽ አልባ መሳሪያዎችን ጨምሮ ህገ ወጥና ፈቃድ የሌለው ሽጉጥም ይዘው ተገኝተዋል፡፡

መላው የከተማችን ነዋሪዎች የሠላም ጉዳይ የፖሊስ ስራ ብቻ ሳይሆን የእኛ ነው በማለት ላደረጋችሁት አጋርነት ኮሚሽኑ ልባዊ ምስጋናውን እያቀረበ አሁንም የሚኖራችሁን ማንኛውንም ጥቆማ በኮሚሽኑ የነፃ ስልክ መስመር 991 እንዲሁም በ0111 11 01 11 በመደወል ማድረስ እንደምትችሉ አሳውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *