በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ እየቀረበ ነው- የሰላም ሚኒስቴር
By: Date: January 19, 2021 Categories: ዜና Tags:

በሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል የህግ ማስከበር ሂደት ከተጠናቀቀ ወዲህ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እና የሕክም አቅርቦቶችን የያዘ የሰብዓዊ ድጋፍ በትግራይ ክልል ለሚገኙ 1ነጥብ 8 ሚሊየን ተጠቃሚዎች ደርሷል፡፡ በክልሉ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል (ኢ.ሲ.ሲ) የሚኒስትሮች ኮሚቴ መሪነት አፋጣኝ ፍላጎቶችን ለማሟላት ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ከክልል ቢሮዎች፣ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅቶችና ከአለም ዓቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተውጣጡ የቴክኒክ ቡድኖችን ያካተተ የአስቸኳይ ጊዜ ኦፕሬሽን ማስተባበሪያ ማዕከል (ኢ.ኦ.ሲ.) በመቀሌ ከተማ ተቋቁሟል፡፡

ተጨማሪ ፍላጎቶችን ለመለየት ባለ አራት ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበር ሥርዓት (የክልል፣ የዞን፣ የወረዳ እና የምግብ ማከፋፈያ ቦታዎችን ያካተተ) ተደራጅቶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
ተለይተው ለታወቁ ተጠቃሚዎች የድጋፍ ሽፋንን ለማሳደግ እንዲሁም በፍጥነት አቅርቦትን ለማዳረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ከልማትና ከሰብዓዊ አጋሮች ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

ብሄራዊ የመከላከያ ሰራዊት ደህንነቱ የተጠበቀ የሰዎችና የአቅርቦቶች እንቅስቃሴን በማመቻቸት የሰብአዊ ዕርዳታውን ቅንጅት በከፍተኛ ደረጃ በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡ ስርጭቱ በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ በአለም ዓቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ አስተባባሪ (ዩ.ኤን.ኦቻ) አስተባባሪነት በዓለም ዓቀፍና በሀገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በሴፍቲኔት መርሃ-ግብር (ፒ.ኤስ.ኤን.ፒ) እየተከናወነ ይገኛል።

ስርጭቱ የሚከናወነው ከአክሱም፣ አዲግራት፣ አላማጣ፣ መቀሌ ዙሪያ፣ ሽሬ እና መቀሌ ከተማ ከሚገኙ የማሰራጫ ጣቢያዎች ነው፡፡ በሂደቱ ለሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያንና የአካል ጉዳተኞች ለምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁስና የሕክምና አቅርቦቶች ስርጭት ቅድሚያ እየተሰጠ ይገኛል፡፡

መንግስት እና ሰብአዊ አጋሮች እ.ኤ.አ. ኖሼምበር 29 ቀን 2020 በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት በቅንጅት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የተጠቃሚዎችን ብዛት በትክክል ለመለየት የጋራ የፍላጎት ዳሰሳና ግምገማ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡ ለወገኖቻችን የሰብዓዊ ድጋፍ ለማዳረስ ትኩረት ተሰጥቶ በቁርጠኝነት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡ ፋና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *