ሳዑዲ በ500 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ጭው ባለ በረሃ ላይ ግዙፍ ከተማ ልትገነባ ነው
By: Date: January 18, 2021 Categories: ዜና

ሳዑዲ አረቢያ በምድር ላይ አምሳያ የሌለው ከተማ በምድረ በዳ ላይ ለመገንባት አቅዳለች፡፡ ዘውዳዊው ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን በፕሮጀክቱ እቅዶች መሰረት በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኘው 170 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ መተላለፊያ መስመር ምንም የካርቦን ልቀት እንዳይኖረው ተደርጎ የሚገነባው ከተማው ከመኪና ነፃ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ዘመናዊው ከተማ ሙሉ በሙሉ የኃይል አቅርቦቱ ከንጹህ ታዳሽ የኃይል ምንጮች የሚሸፈን ሲሆን ይህም ሳዑዲ አረቢያ በነዳጅ ላይ ከተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመላቀቅ በምታደርገው ጥረት አንድ ትልቅ እርምጃ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

ዘ ላይን የሚል ስያሚ የተሰጠው ከተማው ኒኦም በተባለ ምድረ በዳ ላይ እንደሚገነባ ነው የተገለጸው፡፡ በከተማው አንድ ሚሊዮን ህዝብ ይኖርበታል የተባለ ሲሆን ነዋሪዎቹእንዲተሳሰሩ እና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ በሰው ሰራሽ አስተውህሎት (አርተፊሺያል ኢንተሊጀንስ) እንደሚተዳደሩም ነው የዘናሺናል ዘገባ የሚያመለክተው፡፡

በተለመዱ ከተሞች ውስጥ የከተማ ኑሮን አስቸጋሪ የሚያደርጉ የትራፊክ ፣ የብክለት እና የመሠረተ ልማት ተግዳሮቶችን በመጋፈጥ ይህ የወደፊቱ ልማት አዲስ የኑሮ ዘይቤን ለመፍጠር ለእግር ጉዞ ለንጹህ ኃይል እና ለቴክኖሎጂ ቅድሚያ ይሰጣል ተብሏል፡፡

የ ዘ ላይን ከተማ ፕሮጄክት ይፋ በተደረገበት በዛሬው ዕለት ልዑል መሐመድ ባደረጉት ንግግር በከተሞች ያለውን መጨናነቅ መቅረፍ እና በፍጥነት እያደገ ላለው የህዝብ ቁጥር መፍትሔ መፈለግ በከፍተኛ ደረጃ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡ “በ2050 የመጓጓዣ ጊዜዎች በእጥፍ ይጨምራሉ። በተመሳሳይ ዓመት የካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት እና የባህር ከፍታ በመጨመር አንድ ቢሊዮን ሰዎች ከሚኖሩበት ወደ ሌላ ቦታ መዛወር ይኖርባቸዋል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ኒኦም የተሰኘው የሳዑዲ ምድረ በዳ ፣ ሀገሪቱ ከፍተኛ የቱሪዝም እና የቢዝነስ ማዕከል ልታደርገው ያሰበችው በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የሚገኝ ስፍራ ሲሆን ስፍራው የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በ2030 ከነዳጅ ጥገኝነት እንዲላቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ታቅዷል፡፡ አላይን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *