ኢዜማ የክልል ልዩ ኃይል ወደ መከላከያ ወይም ፖሊስ ሊካተት ይገባል ሲል ጠየቀ

በአንዳንድ አካባቢዎች የአንድ ክልል ልዩ ኃይል ከሌላው ክልል ልዩ ኃይል ጋር ሲጋጩ እየታየ ዝምታው የት እስኪደረስ እየተጠበቀ እንደሆነ ኢዜማ ግራ መጋባቱን የፓርቲው የምርጫ ስትራቴጂና ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ከውሰር እንድሪስ ገልጸዋል፡፡ ወ/ሮ ከውስር ይኽንን የተናገሩት ሐሙስ ጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም. የፓርቲውን የምርጫ ዝግጅትና ወቅታዊ ጉዳዮች አስመልክቶ በነበረው መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡

‹‹መንግሥት በራሱ አካላት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በአስቸኳይ ማቆም አለበት›› ያሉት ወ/ሮ ከውሰር፣ በየክልሉ ያሉ የብልፅግና ፓርቲ አካላት እርስ በርሳቸው በሚፈጥሩት ግጭቶች የዜጎች ደኅንነት አደጋ ውስጥ መግባት የለበትም ብለዋል።

‹‹መንግሥት ሰላማችን እንዲጠብቅ እንጂ የባሰ ሥጋት ውስጥ እንዲከተን አንፈልግም፤›› ሲሉ አክለው ገልጽዋል፡፡ በተመሳሳይ የፓርቲው ብሔራዊ የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ተክሌ በቀለ፣ የክልል ልዩ ኃይል ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለውና ብሔርን ብቻ ለማገልገል የተፈጠረ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

በራሱ ክልል የሚኖርን የሌላ ብሔር ተወላጅ እንኳ እንደ ዜጋ የማይቆጥር እንደሆነ የገለጹት አቶ ተክሌ፣ የክልል ልዩ ኃይል ይፍረስ ባይባልም ችግሩ ተስተካክሎ ሕዝቡን ማገልገል እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ብቃቱ እየታየ ወደ ፖሊስና ወደ አገር መከላከያ ሊመደብ እንደሚገባ የጠቆሙት አቶ ተክሌ፣ ይህ ኃይል እያለ ምርጫ እንዴት ይካሄዳል የሚለው አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡

በቅርቡ የሰላም ሚኒስተሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ከሚል ከፓርላማ አባላት ጋር በነበራችው ውይይት፣ የክልል ልዩ ኃይል ምንም ዓይት ሕጋዊ መሠረት እንደሌለው መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም ክልሎች እያሠለጠኑ ማስመረቁን ቀጥለዋል።

በሌላ በኩል ወ/ሮ ከውሰር ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ እስረኞችን አስመልክተው ሲናገሩ፣ ‹‹በታሪካችን ያገኘነውን ዴሞክራሲን የማዋለድ ዕድላችን ፍርድ ቤቶችም ጭምር እንዲያደናቅፉት አንፈልግም፤›› ብለው፣ ሕጉን ጠብቆ ጉዳያቸው ማለቅ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ኢዜማ በመግለጫው መጪው አገራዊ ምርጫ ስለሚኖረው ፋይዳ፣ የአገሪቱ የፀጥታ ሁኔታና በምርጫው ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ፣ አመራሮቻቸው እስር ቤት ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ በምርጫው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖና ኢዜማ ለመጪው ምርጫ እያደረገው ባለው ዝግጅት ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ፓርቲው በ435 ወረዳዎች እንደሚወዳደርና በመጪው ጥር 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ሁሉም ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንደሚታወቁ አስታውቋል፡፡ ኢዜማ ለምርጫው ያደረገውን የፖሊሲ አማራጭ ዝግጅት አስመልክቶ በሰጠው ማብራሪያ፣ ፖሊሲዎቹ የኅብረተሰቡን ቁልፍ ችግሮች በሚፈቱ ዘርፎች በሙያው ብቃቱና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች መቀረፃቸውን አስታውቋል፡፡ አማራጭ ፖሊሲዎቹን ለሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ በየዘርፉ ባለሙያ ለሆኑ የፓርቲ አባላት ላልሆኑ ኢትዮጵያዊያን ጭምር በማቅረብ የተገኘውን ግብረ መልስ በመጠቀም በማዳበር ላይ መሆኑን በመግለጫው አስረድቷል፡፡

እስካሁንም በ18 የፖሊሲ ሰነዶች ላይ ምክክር መደረጉንና በመጪዎቹ ቀናት ቀሪዎቹን ለውይይት እንደሚያቀርብ፣ ጎን ለጎን ደግሞ የምርጫ ማኒፌስቶ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ኢዜማ ጠቁሟል፡፡

‹‹መንግሥት ከመብታችን ቆርጠን የሰጠነውን ኃላፊነት እንዲወጣና የምርጫ ሒደቱ ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ እንፈልጋለን፤›› ያሉት ወ/ሮ ከውሰር፣ ሕዝቡ ሳይፈራ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳበትም አክለዋል፡፡ ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *