ቤተ ክርስቲያን የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎቿን ለማልማት ዕቅድ መንደፏን አስታወቀች

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ጃንሜዳን ጨምሮ በአዲስ አበባ የሚገኙ የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎችን ለማልማት ዕቅድ የነደፈች ሲኾን፣ የጃንሜዳ ባለቤትነቷን የሚያረጋግጥ ካርታ እንዲሰጣት ጠይቃለች፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የካርታ እና የይዞታ ጉዳይን የሚከታተለው እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጸዴቅ የሚመራው ኮሚቴ፣ ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋራ ባደረገው ውይይት፣ ቤተ ክርስቲያን በስሟ የሚገኙ 38 የባሕረ ጥምቀት ቦታዎችን በተለያየ መልኩ የማልማት ዕቅድ እንዳላት ማስታወቁን፣ የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የመረጃ ክፍል ሓላፊ ላዕከ ሰላም ግርማ ተክሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

አብዛኛዎቹ የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያዎች፣ በመንግሥትም በግል ባለሀብቶችም እየተቀነሱ በመወሰድ ላይ እንዳሉና ይኸውም ቦታዎቹ፣ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ለጥምቀት በዓል ማክበሪያነት አገልግለው ከዚያ በኋላ ሳይሠራባቸው መክረማቸውን በመመልከት እንደኾነ የሚጠቅሱት ላዕከ ሰላም ግርማ፣ ይህ ኹኔታ ያሳሰባት ቤተ ክርስቲያን፣ ቦታዎቹን የማልማት ዕቅድ መንደፏን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙት 78 ጠቅላላ የበዓለ ጥምቀት ማክበሪያዎች ውስጥ፣ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ በተረከበችባቸው 38ቱ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ላይ፣ ከእምነቱ ዕሴት ጋራ የማይቃረኑ የማኅበራዊ ልማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበር መታቀዱን ነው ላዕከ ሰላም ግርማ ያስረዱት፡፡ በተቀሩትም ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንደተገኘባቸው ወደ ልማት እንዲገቡ አቅጣጫ መቀመጡን አመልክተዋል፡፡

በቦታዎቹ ላይ ሊተገበሩ ከታቀዱት የማኅበራዊ ልማት ፕሮጀክቶች መካከል፥ ቤተ መጻሕፍት፣ የመናፈሻ ውስጥ ክፍት የማንበቢያ ቦታዎች፣ ከሥርዓተ እምነቱ ጋራ የማይቃረኑ የመዝናኛ እና የመናፈሻ አገልግሎት መስጫዎች እና አረንጓዴ ልማት የማከናወን ዕቅዶች እንደሚገኙበት ሓላፊው አብራርተዋል፡፡ ሙሉ መረጃውን ለማየት ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *