በመቀሌ ከተማ በመሣሪያ የተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች እንዳሉ ተገለጸ

የመቀሌ ከተማ ሰላምና ፀጥታ በአንፃራዊነት እየተሻሻለ ቢሆንም፣ አሁንም በመሣሪያ የተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች መኖራቸውን የመቀሌ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ከንቲባ አስታወቁ፡፡የተወሰኑ የመንግሥት ተቋማት፣ ትራንስፖርትና መሰል አገልግሎቶች በመቀሌ ከተማ ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሳቸውን፣ ሆኖም የትግራይ ፖሊስ ሙሉ በሙሉ በመፍረሱ ሕዝቡን መከላከል የሚችል የፀጥታ መዋቅር አልነበረም ያሉት አቶ የከተማ፣ አስተዳደሩ ጊዜያዊ ከንቲባው አታክልቲ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡

እንደ አቶ አታክልቲ ገለጻ፣ አዲስ የፖሊስ ኃይል በማደራጀት በጦርነቱም ሆነ ከጦርነቱ በፊት ምንም ዓይነት ተሳትፎ ያልነበራቸውን አባላት ተመልምለው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ ነገር ግን ትጥቅ ከማስፈታት በኋላ በድምፅ አልባ መሣሪያዎች የተደራጁ ዘራፊ ቡድኖች በየመንደሩ ዝርፊያ እየፈጸሙ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የዝርፊያ ወንጀሉን ለመከላከል የአገር መከላከያ ሠራዊት ታች ድረስ ወርዶ ከተቋቋመው የፖሊስ ኃይል ጋር እያስከበረ እንደሚገኝ አቶ አታክልቲ አስረድተዋል፡፡

የመሠረተ ልማት ዕድሳትና ግንባታን በተመለከተ በመቀሌ ከተማ ብዙ የተሻሻለ ሁኔታ ተፈጥሯል ያሉት ጊዜያዊ ከንቲባው፣ በመንግሥት የአገልግሎት ተቋማት ሆን ተብሎ ሰነዶች እንዲጠፉ መደረጋቸው፣ ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ግብዓቶች መዘረፋቸው ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው ሲመለሱ ለአገልግሎት አሰጣጥ አዳጋች ሆኖባቸዋል ብለዋል፡፡

‹‹በመቀሌ በዚህ ጊዜ የሰብዓዊ ድጋፍ እጥረት አለ፡፡ የጉልበት ሠራተኛው፣ ነጋዴውና የወር ደመወዝተኛው ወደ ተረጂነት ተቀይሯል፡፡ የፌዴራል መንግሥትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እያቀረቡ ያሉትን ዕርዳታ በማዳረስ ላይ ብንገኝም፣ ከጠበቅነው በላይ ዕርዳታ የሚጠብቅ ኅብረተሰብ በከተማችን ይገኛል፤›› ሲሉ አቶ አታክልቲ አስረድተዋል፡፡

ከሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፍ ጎለ ለጎን የደረሰውን የመሠረተ ልማት ውድመት ለማስተካከል እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ከንቲባው፣ አብዛኛው የከተማው በጀት ከውስጥ ገቢ የሚሰበሰብ ስለነበር አቀናጅቶ ለመጠቀም አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) መቀሌ ከተማ ተገኝተው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይትና ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በክልሉ ለሚገኙ ሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት 16 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መድኃኒቶች በማቅረብ የሥርጭቱ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

በመቀሌ ከተማ ምንም እንኳ ቀደም ሲል ከነበረው በአንፃራዊ ሁኔታ መረጋጋት ቢታይም፣ አሁንም በርካታ የንግድ መደብሮችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራ አለመጀመራቸው ታውቋል፡፡

በመቀሌም ሆነ በሌሎች የትግራይ አካባቢዎች ከሚፈጸሙ ዝርፊያዎች በተጨማሪ፣ ነዋሪዎች ለምግብ ችግር መዳረጋቸው በስፋት ይነገራል፡፡ የአስተዳደር መዋቅሮች በመፍረሳቸው ምክንያትም ነዋሪዎች የዘራፊዎች መፈንጫ መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡ ሪፖርተር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *