ለምርጫ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ያስጠነቀቀው የኦፌኮ መግለጫ ሲዳሰስ
By: Date: January 17, 2021 Categories: ትንታኔ Tags:

(በጌታሁን ሄራሞ) የኦፌኮ ፓርቲን መግለጫ አንብቤ የበኩሌን ለማለት ወደድኩ(ሙሉውን በኮመንት ሳጥን ማግኘት ይቻላል)። በአጭር ቃል መግለጫው እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነው። ለምሣሌ መግለጫው መግቢያው ላይ እንደዚህ ይላል፡፡ “የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ከምስረታው ጀምሮ በሠላማዊ ውይይትና ድርድር የሚያምንና የአገራችንን ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት መነጋገር፣ መወያየትና መደራደር አስፈላጊ እንደሆነ ሲያሳስብ የቆየ ድርጅት ነው፡፡”

ኦፌኮ ሠላማዊ ውይይትንና ድርድርን መርሁ አድርጎ የተመሠረተ ፓርቲ እንደሆነ በዚህ መልክ ካስነበበን በኋላ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ውይይትና ድርድር ፈፅሞ የማይስተናገድባቸው ርዕሰ ጉዳዮች እንዳሉ የገለፀው በዚህ መልክ ነው፡፡ “በሌላ በኩል ደግሞ የወቅቱን የኢትዮጵያ ችግሮችን በመጠቀም የቀኝ ኃይሎች በቅርፅ ያገኘነው ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝሙ በዛ ብለው ሕገ መንግስቱንና ማንነትነ መሠረት አድርገው የተመሰረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፖለቲካ አውዱ እንዲወጡ ግፊት ማድረግ ጀምረዋል፡፡ የብሔሮች ጥያቄ ሕወሓት ከመመስረቱ በፊት ሲጠየቅ እንደነበረ ተረስቶ ከሕወሓት ጋር መኮነኑን ሥራቸው ያደረጉ ድርጅቶች እየበዙ ነው፡፡ እነዚህ የቀኝ ኃይሎች በጊዜ ሃይ ሊባሉ ይገባል እንላለን፡”

በተጨማሪም ኦፌኮ “ሕገ መንግስቱንና በሕገ መንግስቱ መሠረት የተዋቀረውን ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝሙን የሚቃወሙ የቀኝ ኃይሎች በአንድ በኩል ግፋ በለው! ሲሉ፤ የመንግስት በትረ ሥልጣኑን የተቆጣጠሩት ደግሞ የፌዴራል አወቃቀሩ እንዲቀለበስ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ፡፡ ይህ አደገኛ አካሄድ እንደሆነ ኦፌኮ ይገነዘባል፡፡” የሚል ማስጠንቀቂያ ያዘለ መልዕክት ያስተላልፋል።

ስለዚህ በኦፌኮ መግለጫ (ማስጠንቀቂያ) መሠረት በፌዴራል አወቃቀርና በብሔር ፖለቲካ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ፓርቲው ከያዘው አቋም የተለየ ሐሳብ ማራመድ “የቀኝ ኃይል” የሚል ታፔላ ያስለጥፋል። ከዚህም በተጨማሪ ብሔርን መሠረት ካደረገው ከኦፌኮ ፓርቲ ፕሮግራም የተለየ ሐሳብ ይዞ መገኘት ሀገሪቱን ወደ አደጋ እንደ መክተት ይቆጠራል።

በሀገራችን ፖለቲካ አንዱም ግድፈት ሰፊ ፅንሰ ሐሳብ ያላቸውን ቃላት በዘፈቀደ እያነሱ መጠቀም ነው። ለምሣሌ አፌኮ ከፕሮግራሙ የተለየ ሐሳብ የሚያራምዱትን ፓርቲዎች “የቀኝ ኃይሎች” ሲል ምን ማለቱ ይሆን? የግራ ኃይሎች የተባሉትስ እነማን ይሆኑ? ዝርዝሩን ለጊዜው እንተዋውና በአንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ዕሳቤ መሠረት የግራ ክንፍ/ኃይሎች ሊብራል አመለካከት ያላቸውን ቡድኖች ለማመላከት ጥቅም ላይ የሚውል ሐረግ ሲሆን የቀኝ ክንፍ/ ኃይሎች የሚለው ደግሞ ወግ አጥባቂ (Conservative) ቡድኖችን የሚወክል ዕሳቤ ነው። የግራ ኃይሎቹ ፅንፍ ሲይዙ ልክ እንደ ኮሚኒዝምና ሶሻሊዝም ርዕዮት አራማጆች አብዮተኞች ወደ መሆን ይዘልቃሉ። ቀኞቹ ፅንፍ ሲይዙ ደግሞ ፋስሽታዊ አቋም የሚያንፀባርቁ ናሽናሊስት ይሆናሉ።

እንግዲህ በኦፌኮ መግለጫ መሠረት አሁን ባለው የብሔር ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይም ሆነ ብሔርንና ቋንቋን ብቻ መሠረት ባደረገው “ሕብረ-ብሔራዊ” ፌዴራሊዝም ላይ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲመጣ ጥያቄ የሚያነሳ ሁሉ “ናሽናሊስት” ነው፣ ባስ ሲልም ፋሽስት ነው። ይህ የኦፌኮ አቋም ከሆነ ደግሞ ኦፌኮ የ”ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም” ፅንሰ ሐሳብ ምን እንደሆነ ያለው ግንዛቤ ጥያቄ ላይ ሊወድቅ ነው። በነገራችን ላይ በሀገራችን ላይ እንዳለ የሚታመነው ፌዴራሊዝም በራሱ “ሕብረ-ብሔራዊ” ነው ወይስ ሌላ? የሚለው በራሱ አንድ አጨቃጫቂ ጥያቄ ነው።

(የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችን በጂዖግራፊ(ከቅርፅ አኳያ) አዋቅረው ከጨረሱ በኋላ “ኢትዮጵያ የምትከተለው ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም (Multinational federalism) ነው” የሚሉ ደፋሮች ይገርሙኛል።”) የደቡቡ አወቃቀር ከሕብረ ብሔራዊው ይልቅ በአንዳንድ የፌዴራሊዝም አጥኚዎች ከአስተዳደር ይዘት አኳያ “Coalescent federalism” እየተባለ ለሚጠራው የፌዴራል ቅርፅ የቀረበ ነው። ነገሩ እንደዚህ ቢሆን ምንም ችግር አልነበረውም፣ የደቡቦቹ በአንድ ቅርጫት ውስጥ መታጨቃቸው በብሔሮቹ ፈቃድ ሳይሆን በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ መሆኑ ነው አጠያያቂው።

ስለዚህ ከሀገሪቱ ብሔሮች ውስጥ ከ50 በላይ የሚሆኑት የተዋቀሩት በሕብረ-ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት መርህ መሠረት አይደለም ማለት ነው። ለምሣሌ በሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ዲዛይን መሠረት ክልልንና የራስ ገዝ አስተዳደርን መጠየቅ አያስቀስፍም፣ ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ለብሔሮች የሚሰጠው መብት እስከ ታች ድረስ ወርዶ(ጥያቄው ካለ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ አከላልን ጭምር የሚያካትት) ተግባራዊ እስከመሆን የሚደርስ ነው። የሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም አቀንቃኞች(ብልፅግና ፓርቲን ጨምሮ) እየተተገበረ ያለው አወቃቀር “ሕብረ ብሔራዊ” እንደሆነ ከነገሩን በኋላ በተለይም ለአናሳ ብሔሮች ፅንሰ ሐሳቡ የሚፈቅደውን መብት ከመተግበር ሸርተት የሚሉ ከሆነ የሚከተሉት የፌዴራል ዲዛይን ችግር እንዳለበት አመላካች ነው። አሁንም ቢሆን ብልፅግና ፓርቲም ሆነ ሌሎች የብሔር ፓርቲዎች የሚያራምዱት የፌዴራል አወቃቀር ሕብረ-ብሔራዊ ነው ካሉን ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች በሕገ መንግስቱም ጭምር የተፈቀደውን በክልል የመደራጀት መብትን ፈፅሞ መከልከል አይችሉም፡፡

ይህን መፈፀም ካልቻሉ ደግሞ ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም የሚለውን ስያሜ ከመጠቀም መቆጠብ አለባቸው። በእኔ ግምት አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የደቡብ ብሔሮች በክልል እንዲደረጁ መንግስትን እየጠየቁ ያሉት ከብሔር ተኮር ክልል ጋር ፍቅር ይዞአቸው ሳይሆን የብሔር ፌዴራሊዝም ፅንሐሳብ በተለይም ደቡብ ላይ ዕውን ማድረግ ከባድ መሆኑን ለመጠቆም ይመስለኛል። በአጭር ቃል ድጋፉ ስትራቴጂክ ነው። ስለዚህም ኦፌኮ ሽንጡን ገትሮ የሚከራከርለት “ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም” ከፅንሰ ሐሳቡ ተነስተን ከፈተሽን ካለም አድራሻው በተወሰኑ የሀገሪቱ ክልሎች ብቻ ነው። በነገራችን ላይ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን በማክበርና በዲሞክራሲ መብቶች በተምሳሌትነት የምትጠቀሰው የሕንድ ፌዴራሊዝምም ቢሆን ለአቅመ ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም እንዳልደረሰ በማስረጃ ጭምር የሚሞግቱ ምሁራን አሉ። ለዚህም በዋቢነት የሕንዳዊውን የፖለቲካ ንድፈ ሐሳብ ፕሮፈሰር “Rajeev Bhargava” ጥናት መጥቀስ ይቻላል። ምንጭ፦ Should Indian Federalism Be Called Multinational? Rajeev Bhargava, chapter 11, Multinational Federalism Problems and Prospects, 2012.

ሌላው ኦፌኮ ከራሱ ሕብረ ብሔራዊ ፕሮግራም የተለየ ፕሮግራም ይዘው የሚንቀሳቀሱትን “የቀኝ ኃይሎች” በማለት መፈረጁ በዓለም ላይ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ለማስከበር ብቸኛው ፍቱን መድኃኒት መለስ-ወለድ ኢቲኖፌዴራሊዝም ብቻ እንደሆነ የደመደመ ያስመስልበታል። ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ከሀገር ሀገር ልዩ ልዩ ቅርፅና ይዘቶች አሉት። ለምሣሌ ኦፌኮ የብሔር ፓርቲዎች መፍረስን በተመለከተ ያለውን ስጋት ቢገልፅም ነገር ግን የብሔር ፓርቲን ከፖለቲካው አስወጥተው ከእኛ ሀገር ኢቲኖፌዴራሊዝምም በተሻለ የብሔር ብሔረሰቦቻቸውን መብት ለማስከበር የሚጥሩ አያሌ ሀገራት እንዳሉ ካለወቀ ይገርመኛል። ለዚህም እነ ጋናን፣ ታንዛኒያ፣ ናይጄሪያንና ሩዋንዳን ወዘተ በምሣሌነት መጥቀስ ይቻላል።

በአውሮፓና በኢስያ ደግሞ በተለይም የአናሳ ብሔሮችን መብት ከእኛ ሀገር አወቃቀር በተለየ መንገድ በመሄድ በተሻለ መልኩ እያከበሩ ያሉ ሀገራት አሉ፣ ለዚህም እነ ቤልጂየም፣ ኢስቶኒያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስፔን ተጠቃሽ ናቸው። ኦፌኮ እንዲያወቅልን የምንፈልገው እነዚህ ሀገሮች ውስጥ የብሔር ፓርቲ ብሎ ነገር የለም፣ የሚከተሉትም የክልል አከላለል ከእኛ በተቃራኒ ከሞላ ጎደል “Non-Territorial” የሚባለው ነው። እንግዲህ በኦፌኮ ፍረጃ መሠረት እነዚህ ሀገራት የብሔር ፓርቲ ስለሌላቸውና የፌዴራል አወቃቀራቸውም እንደ አኛ ብሔርንና ቋንቋን ብቻ መሠረት ባለማድረጉ “የቀኝ ኃይሎች” ሊባሉ ነው? አስቂኝ ነው!!! ኦፌኮ የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ለማስከበር ያለው መፍትሔ አንድና አንድ ብቻ ለዚያውም የጨፍጫፊውና ሰው-በላው ጆሴፍ ስታሊንና የኮራጁ መለስ ዜናዊ ብቻ ነው የሚለውን አቋሙ ላይ ፍተሻ ማድረግ አለበት። ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ቅርፁ ብዙ ዓይነት ነው፣ እኛ ከምናውቀው ቅርፅ የተለየ ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራል ቅርፅ እንዳለ ካለማወቅ ይመስለኛል ኦፌኮ ሁሉንም በቀኝ-ክንፍነት ለመፈረጅ የቸኮለው

እናም በእኔ እምነት ኦፌኮ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ ብቻ ነው፣ ስለዚህም ለሀገሪቱ ይበጃል ብሎ የሚያስበውን የትኛውንም ፕሮግራም በአማራጭነት ይዞ የመቅረብ መብቱ የተጠበቀ ነው። ከዚህ ባለፈ ከፓርቲው የተለየ ፕሮግራም ነድፈው የሚንቀሳቀሱትን ሌሎች ፓርቲዎችንም ሆነ ሀገር-ወደድ ዜጎችን “የቀኝ ኃይሎች” ብሎ የመሰየም ሥልጣኑን ከየት እንዳገኘው እስከአሁን ሊገባኝ አልቻለም። ለብሔሮች መብት ብቸኛ ተቆርቋሪ እኔና እኔ ብቻ ነኝ የሚለው አቋሙም ራሱን ወደ ኢቲኒክ-ፖፑሊስት ጎራ እንዳያሽቀነጥረው ጥንቃቄ ማድረግ አለበት። ኦፌኮ ገና ወደ ሥልጣን መንበር ሳይመጣ ከፕሮግራሙ ጋር አብረውለት የማይሄዱትን ፓርቲዎችንም ሆነ ዜጎችን በዚህ መጠን የሚኮንን ከሆነ ነገ ከነገ ወዲያ ሥልጣኑን ቢይዝ ምን ዓይነት አምባገናነዊ ሥርዓት ለማስፈን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አያደግትም።

ስለዚህም ኦፌኮ ኮሽ ባለ ቁጥር “የብሔር ፖለቲካዬም ሆነ ፌዴራል አወቃቀሩ ሊፈርስብኝ ነው” የሚለውን ስጋቱንና ራሱን በግራ ሌላውን በቀኝ የመመደቡን አለአስፈላጊ ፍረጃውን ትቶ ፕሮግራሙን እንደ አንድ አማራጭ ለውይይት ያቅርብ። መግቢያው ላይ “በሰላማዊ ውይይት” እንደሚያምን በገለፀልን መሠረት በውይይቱ ላይ ከፕሮግራሙ የተለየ አማራጭ ሊቀርብ እንደሚችል በማመን ራሱን በዕውቀት ላይ ለተመሠረተ መድረክ ያዘጋጅ። ከዚህ ባለፈ ኦፌኮ ከፕሮግራሙ የተለየ ፕሮግራም የሚያራምዱትን ፓርቲዎችንም ሆነ ዜጎችን “ሃይ ሊባሉ ዘንድ ይገባል” በማለት ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ ዲሞክራሲያዊ መብትን ለመንፈግ የሚያደርገው ሙከራ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው። ይህ ደግሞ ገና የፖለቲካ ሥልጣንን በምርጫ ለመያዝ ከሚያልም ፓርቲ የሚጠበቅ አቋምም ሆነ መርህ አይደለም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *