ስግብግብ ጁንታችንን አልገደልንም (አቶ አብርሃም አለኸኝ )
By: Date: January 14, 2021 Categories: የግል እይታ

“ሙት ይዞ ይሞታል” እንደሚባለው በሞታቸው የሚገድሉን፣ ከመቃብራቸው በላይ የሚቀብሩን እነዚህ የሀገር ጠላቶች እውነትም አልተገደሉም። ጁንታዎች ተገድለዋል በሚለው የምስራች ነጋሪ ቃል ውስጥ በየቀኑ የሚገደሉ ንጹሀን እልፍ ናቸው። ገዳዮቻችን ሳይገደሉ ያውም ደጋግመው እየገደሉን ጁንታዎች ተገድለዋል የሚለው ዜና የጁንታዎችን ከመቃብር በላይ መኖር ያረጋግጣል። እመኑኝ ጁንታዎቻችን አልተገደሉም።

ኢትዮጵያ የወዳጆቿን መብዛት ያህል ጠላቶቿ እልፍ አእላፋት ናቸው። ደጋግመው የሚሳሳቱ ፣ በመሳሳት ልክፍት ውስጥ የተዘፈቁ አፍቃሪ ወያኔዎች ጥቂት አይደሉም። የወያኔ ሞት ህመማቸው የሆነ ከስህተታቸው ከመማር ይልቅ ለሌላ ስህተት የተዘጋጁ የስሁት ታሪክ ቁሞ ቀሮች ብዙ ናቸው። እነዚህ የስሁት ታሪክ ቁሞ ቀሮች የስግብግብ ጁንታዎች ትንሳኤ ሙታን የምስራች ቃል ነጋሪ ናቸው። እነዚህ የስሁት ታሪክ ቁሞ ቀሮች የትህነግ የሃምሳ አመታት የጥፋት እቅድ ፍሬዎች ናቸው። ትንሳኤ ትህነግ ጸረ ኢትዮጵያ ሀሳዊ ነብይ ናቸው።

መተከልን አኬል ዳማ ለማድረግ ትጥቅና ስንቅ የሚቋጥሩ የጥላቻ ደቀመዝሙሮች ምድርን በሞሉባት ኢትዮጵያ ስግብግብ ጁንታዎች ተገደሉ የሚለው ዜና እንዴት ትክክል ሊሆን ይችላል ? የአረመኔ ትህነጋውያን ጁንታዎች አሻራ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጤንነታችንን እያወከ ነፁህና ሰላማዊ አየር እንዳንስብ ሁለንተናችንን እየበከለ ፣ አብሮነታችንንና በመተባበርና በመደራደር ፍትሀዊ አማራጭ የመኖር ህልውናችንን እየተጋፋ ባለበት በዚህ ሰአት የጁንታዎች ተገደሉ ዜና ከስላቅ በላይ ነው።

በአንድ ወገን ስግብግብ ጁንታ እየገደሉ በሌላ ወገን ስግብግብ ጁንታ እየፈለፈሉ የደህንነት አዙሪት በሚፈታተናት አገር ውስጥ መኖራችን መቸ ያበቃል? እየተገደሉ የሚኖሩ ፣ እየሞቱ የሚቀብሩ፣ እልፍ ወራሽ ያላቸው ጁንታዎች ተገደሉ የሚለው ዜና ለኢትዮጵያ መልካም የምስራች የሚሆነው እንዴት ነው ? ትህነጋውያኑን የተፀየፍናቸው በቋንቋቸው ወይም በደማቸው እኮ አይደለም። ቋንቋቸውም የቋንቋችን ዘር ነው። ደማቸውም የደማችን ሸጥ ነው። አምባቸውም መኖርያችን ነው። የእነሱ መገደል ዜናም ያሳዝነናል እንጂ አያስደስተንም።

ይሰቀጥጠናል እንጂ ጮቤ አያስረግጠንም። ይሁን እንጂ በመረጡትና በተለሙት መንገድ መጓዝን የመረጡት ራሳቸው ናቸው። የያዙት መንገድ የተሳሳተ እንደሆነ ደጋግመን አሳስበናቸዋል። ከማሳሰብም አልፈን በወገናዊነት ስሜት ከአንጀታችን ተማጽነናቸዋል። የተማጽኗችን ክታብ ቤተመዛግብታችንን ሞልቶታል። በችርቻሮ ሳይሆን በጅምላ ደርዘን ምስክር ማቅረብ እንችላለን። አልተገደሉም የምንለው ስላልተገደሉ አይደለም። ቢገደሉም አለመገደላቸውን የሚተርክ የስሁት ትርክታቸው አልጋ ወራሽ በመቃብራቸው ጥግ ቁሞ መቃብራችንን እየቆፈረ ስለምናየው ነው። የስግብግብ ጁንታዎች የመቃብር ዘብ መተከል ላይ በህይወት አለ።

በየቀኑ ብዙ ንጹሀንን ይገድላል። በየክልሉ ሰርጎ እየገባ ለህጻናት ለአረጋውያን፣ ለአባዎራዎችና ለመበለቶች የሙት መንፈስ ያድላል። ብሄር መርጦ የሚበላው የኦነግ ሽኔ ክንፍ፣ የትህነግ ቅራሪ የሆነው የጉሙዝ አማፂ ቡድን ከሱዳንና ከግብጽ ጋር የፈጸሙት ህገወጥ ጋብቻ የትህነጋውያኑ የሙት መንፈስ ወራሾች መሆናቸው አያጠራጥርም። እነዚህ የኢትዮጵያ ጠላቶች መገደላቸው አይቀርም። የእነሱ መገደል ብቻውን ለኢትዮጵያ ሰላምና ለዜጎች ሰብአዊና ህሊናዊ ጤንነት አልፋና ኦሜጋ አይደለም። ስግብግብ ጁንታው ተገደለ አልተገደለ ፣ ኦነግ ሸኔ ተገደለ አልተገደለ ፣ የጉሙዝ አማጺ ተገደለ አልተገደለ ፣ የሱዳን ክፉ መንፈስ ተገደለ አልተገደለ ፣ የግብጽ ፈርኦናዊ መናፍስት ተገደለ አልተገደለ ኢትዮጵያን ነጻ አያወጣትም።

የመረጡት መንገድ ነውና ሁሉም ይገደሉ ሸጋ ነው። በዚህ ረገድ የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን እየፈጸመው ያለ ጀብዱና ኢትዮጵያዊ ተጋድሎ ታላቅ ክብር የሚሰጠውና በወርቅ ቀለም የሚጻፍ ነው። ኢትዮጵያን ነጻ የሚያወጣት ግን የስሁት ትርክት ቁሞ ቀርነት ሙሉ ለሙሉ ሲደመሰስ ነው። እዚህ ላይ ፖለቲከኞች ፣ ምሁራን ፣ የሚዲያ ሰዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ነፍስ ያወቅን ሁሉ መረባረብ ይኖርብናል። የስግብግብ ጁንታወች አካላዊ መገደል ሀሳባዊ ኑባሬያቸውን ካላከሰመው ነገም የሚቀጥል ችግር አለ ማለት ነው። ታሪክን በታሪክ መሞገት እየተቻለ ታሪክን ማጭበርበርም ሆነ በታሪክ ላይ የውንብድና ወንጀል ደጋግሞ መፈጸም ካለፈው ስህተት ባለመማር ለዳግም የመናቆር ቅርቃር መዘጋጀት ነው።

ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ችግር ያለባት አገር ብትሆንም ባለፉት አምስት አስርተ አመታት የተደረተባት ችግር ግን በቀላሉ የሚፈታ አይደለም። አሁን በምንገኝበት የታሪክ መድረክ ሳይቀር እየተፈጸሙ ያሉ ኢሰብአዊና ዘግናኝ ድርጊቶችን ሊያጭበረብር የሚፈልግ ስሁት ብዕርና ቀሳጢ አንደበት የነገሰባት ምድር ናት ኢትዮጵያ ።

በዘመናችን የተቆረጡ እጆች ፣ የተተለተሉ ሰውነቶች ፣ በግፍ የተቀሉ አንገቶች ፣ በጭካኔ የተበለቱ ልቦች፣ ጉበቶችና ኩላሊቶች ፣ ያለርህራሄ የተነቀሉ የሴት ልጅ ጡቶችና የወንድ ልጅ ሙርጦች፣ በታንክና በስካቫተር የተጨፈለቁ በድነ ስጋዎች፣ ለአእምሮ በሚዘገንን ሁኔታ በጭካኔ በትር ፣ በድንጋይ ፣ በቀስት ፣ በገጀራ ፣ በቢላዋ ፣ በተተኳሽና በተቀጣጣይ አውዳሚ መሳርያዎች የተለበለቡ የንጹሀን ዜጎች፣ እንደዝንጀሮ ናዳ ወደገደል ተወርውረው እልቂት የተፈጸመባቸው የሀገር ልጆች የምናስታውሳቸው በምንድን ነው ?

የበደኖ አዙሪት ለጉራ ፈርዳ ፣ የጉራ ፈርዳ አዙሪት ለጉሊሶ ፣ የጉሊሶ አዙሪት ለቡለን ፣ የቡለን አዙሪት ለማይካድራ፣ የማይካድራ አዙሪት ለድባጤ፣ የድባጤ አዙሪት ነገ ለማን እንደሆነ በማይታወቅበት ነባራዊ ሁኔታ ምን ብናደርግላቸው ነው የምናስታውሳቸው። በቁጥርስ በአይነትስ ስንት የሰማዕታት ሀውልት ያስፈልጋቸዋል። ኦ ጉራ ፈርዳ ብለን ሳናበቃ፣ ኦ ጉሊሶ ይተካል። ኦ ጉሊሶ ብለን ሳንጨርስ ኦ ማይካድራ ይተካል። ኦ ማይካድራ ብለን ሳንጽናና ኦ ቡለን ፣ ድባጤ እያለ ይቀጥላል። ይህንንም አይን ያወጣ የታሪክ ሀቅ ሊያድበሰብስ ፣ ሊያፈራርስ ፣ ሊያጭበረበር የሚፈልገው ስግብግብ ጁንታ ብዙ ነው። ህሊና ላለው ሰው፣ አእምሮ ላለው ፍጡር እንዲህ አይነት ቁማር መፍቀድ በእውነት ከስግብግብ ጁንታነት በላይ ነው። እርግጥ ነው የአምስት አስርተ አመታት እርስ በእርስ የመተላለቅ ውጥን አሁናዊ ድርጊት በቅጡ በቅጡ ካላደረግነው የነግ በኔ (ነገ በእኔ) ትንቢታዊ ሀቅ እንደወንዝ ሙላት ከተፍ ማለቱ አይቀርም። እስከአሁን የሆነው ሁሉ ሆነ ። ሀውልት አቁመን ቂምና ጥላቻን የማውረስ ቅንጣት ታህል ፍላጎት ባይኖረንም ቀለም በጥብጠን ፣ ብራና ፍቀን፣ ብዕር ቀርጸን በደብተራነት (የዘመኑ ዶክተር ፣ ፕሮፌሰር ፣ ተመራማሪ ፣ አማካሪ እንደማለት ነው) ጥበብ እንከትበዋለን። ቂምና ጥላቻ ፣ ፖለቲካዊ ደባና ርዕዮተዓለማዊ ሸፍጥ ለትውልድ አይተላለፍም ስንል በሰላም ፣ በይቅርታና በፍቅር ማህተም እንዘጋዋለን። እንዲህ ነበሩ አሉን ፣ እንዲህም አደረጉን እንዲህ ግን መሆንም ማድረግም አንፈልግም ስንል አገር በሚያሻግር የታላቅነት ምስጢር ክርችም አድርገን እንዘጋዋለን። መፍትሄው የጥላቻንና የስሁት ትርክት መናፍስታዊ ልክፍትን ጥርቅም አድርጎ መዝጋት ብቻ ነው።
ምክንያቱም ኢትዮጵያ ትቀጥላለች

ለንጹሀን ወገኖቻችን እልቂት መሠረቱ በታሪካችን ላይ የተፈጸመ ስሁት ትርክት ከፍ ያለ ተጠያቂነት ይይዛል። በዚህ ሁሉ እልቂት የሚደሰቱ ለኢትዮጵያ መበላሸትና መበሻቀጥ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱ ትህነግና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፍልስፍና ቅዠት አቀንቃኞች ናቸው። እነዚህ የስሁት ትርክት ቁሞ ቀሮች በየሚዲያዉ በሚንደላቀቁባት አገርና ባፈተተው እንዲጓዙ በተፈቀደበት የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ስግብግብ ጁንታዎች ተገደሉ የሚለው ዜና በእውነት ስላቅ ነው።

አገር ለማፍረስ ያሴሩ ጁንታዎች ተገደሉ ብለን የምስራች ቃል በምናውጅበት የቴሌቪዥን መስኮቶች፣ ጋዜጦች ፣ መጽሄቶች፣ በራሪ ወረቀቶች፣ የማህበራዊ ድረገጽ ትስስር የግንኙነት መረቦች፣ የባለስልጣናት መግለጫዎችና ቃለመጠይቆች ስግብግብ ጁንታዎች ያወረሱንን ትሩፋት የሚያቀነቅኑ ከሆነ በእርግጥም ጁንታዎች አልተገደሉም።

ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን መተከልን ጨምሮ በሁሉም የጦር አውድ ላይ እየከፈለው ያለውን ክቡር መስዋዕትነት የሚያግዝ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ስራ መጀመር ይኖርብናል። በዚህ አውድ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ጨምሮ ሁሉም መሪዎች የተጫወቱትን ሚና አለማድነቅ ንፉግነት ከመሆኑም በላይ ፍርደገምድልነት ነው። የመላው ህዝብ የደጀንነት ተሳትፎም ማለፍያ ነው። ጠቅለል ሲል ያሸነፈው ኢትዮጵያዊነት ነው። ነገር ግን ጁንታዎቻችን አልተገደሉም።

እንደሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ሁሉ በፖለቲካችን፣ በመዋቅራችን፣ በጽሁፋችን፣ በመንፈሳዊና በምድራዊ አስተምህሯችን፣ በየተሰማራንበት የስራ መስክ ሁሉ፣ በምናረጋግጠው አመራር ጭምር በውስጣችን የሚንከላወሱ ስግብግብ ጁንታዎቻችንን ማደን አለብን። በየቀኑ የሚገድለንንና የሚያስገድለንን ሁሉአቀፍ ያልተገራ መስተጋብራችንን ፈጥነን እናርም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *