“ቤኒሻንጉል በአጼ ምኒሊክ ጥያቄ ወደ ኢትዮጵያ ተካለለ እንጂ የሱዳን ነበር” የሱዳን የድንበር ኮሚቴ ሊቀመንበር

“ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣መተማና ሁመራ በአጼ ምኒሊክ ጥያቄ ወደ ኢትዮጵያ ተካለሉ እንጅ የሱዳን ግዛቶች ነበሩ ሲሉ የሱዳን የድንበር ኮሚቴ ሊቀመንበር ሙአዝ ተንቆ ተናግሩ፡፡ ቀመንበሩ ዛሬ በሱዳን ለሚገኙ የዲፕሎመቲክ ማህበረሰብ አባላት በሰጡት መግለጫ “የሱዳን ወታደር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አልገባም ይልቁንም የሱዳን የነበረ ቦታን ነው የተቆጣጠረው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ትናንት በሰጡት ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ “የሱዳን ኃይል በተጠናከረ ሁኔታ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የመግፋት እና ወደ ውስጥ ዘልቆ የመግባት እንቅስቃሴ እያሳየ ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ድርጊት እንደማያዋጣ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ እየገለጸች እንደምትገኝም አምባሳደር ዲና የገለጹ ቢሆንም ሱዳን ግን ድንበር ጥሳ እንዳልገባች እየገለጸች ነው፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ያለው የኢትዮሱዳን የድንበር ኮሚሽንም ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ መግባቷን ባሳለፍነው ሳምንት ማረጋገጡ ይታወሳል፡፡

የሱዳን የድንበር ኮሚቴ ሊቀመንበር በዛሬው መግለጫቸው ፣ ሱዳን በ1902 እንግሊዝና ኢትጵዮጵያ ባደረጉት ስምምነት የሀገራቱ ድንበር እንዲካለል ተስማምታ እንደነበር አንስተዋል፡፡ “አጼ ዮሐንስ አራተኛ መተማ ላይ ስለተገደሉ መተማ ወደ ኢትዮጵያ መካለል አለባት” በሚል አጼ ምኒሊክ ለእንግሊዝ ጥያቄ አቅርበው እንደነበርና መተማም ወደኢትዮጵያ እንደተካለለ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

ቤኒሻንጉል ጉሙዝም የሱዳን ግዛት እንደነበር ያነሱት ሊቀመንበሩ፣ ይህም ወደ ኢትዮጵያ የተካለለው በአጼ ምኒሊክ ጥያቄ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “አጼ ምኒሊክ ይህንን ያደረጉት አካባቢው የወርቅ ማዕድን ስላለበት ነው“ ብለዋል፡፡

በመግለጫው ላይ ተገኝተው አስተያየት የሰጡት በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ ማስከበር ስራ ስለነበረበት ወታደሮችን ወደ ትግራይ ባሰማራበት ቅጽበት ሱዳን ክፍተቱን ተጠቅማ የኢትዮጵያን ድንበር ገፍታ መግባቷን ገልጸዋል፡፡

አምባሳደር ይበልጣል “ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ከፈለገች ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ማስወጣት አለባት” ብለዋል፡፡ የሁለቱ ሀገሮች የድንበር ኮሚሽን አባላት የጋራ ስራ እንዲያከናውኑም ለማድረግ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የገቡ ወታደሮቿን ማስወጣት አለባት ብለዋል፡፡ በ1902 የተደረሰን ስምምነት ኢትዮጵያ እንደማትቀበል አምባሳደር ይበልጣል ገልጸዋል፡፡ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ቻርተር በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረሱ የድንበር ስምምነቶች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው እና የሀገራት ድንበሮች በነበሩበት መቀጠል እንዳለባቸው የሚገልጽ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል የተወከሉት የኢትዮ ሱዳን የድንበር ኮሚሽን አባል አምባሳደር ኢብራሂም ኢድሪስ ቀደም ሲል በሰጡት መግለጫ ሁለቱ ሀገራት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1972 በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የተፈራረሙትን ስምምነት ሱዳን መጣሷን ገልጸው ነበር፡፡ ስምምነቱም ሁለቱ ሀገራት በድንበር ጉዳይ የጋራ መፍትሄ እስኪያስቀምጡ ድረስ መሬት ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንዲቀጥል የሚስገድድ ነው፡፡

በተያያዘ ዜና የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር አብዱልፋታህ አልቡርሃን ወደ ኢትዮ ሱዳን ድንበር ማምራታቸው ተሰምቷል፡፡ ሊቀመንበሩ ወደስፍራው ያቀኑት የሱዳን ወታደሮችን ዝግጅት ለማየት ነው ተብሏል፡፡ አል አይን እንደ ዘገበው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *