በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚሰሩ ሀይ ባይ ያጡት የሸራ ሱቆች

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የእግረኛ መንገድን ጠርዝን ተከትለው እየተሰሩ የሚገኙ የሸራ ሱቆች በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የእግረኛ መንገዶችን ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረጉ መሆኑ ተገለፀ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በምህንድስና ዘርፍ የመንገድ ሀብት አስተዳደር ተጠባባቂ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ህይወት ሳሙኤል እንደገለፁት በከተማዋ በርካታ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ በጀት፣ጉልበትና ጊዜ ወስደው የተገነቡ የእግረኛ መንገዶች ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ የንግድ ሱቆች እየተሰራባቸው በመሆኑ ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ኢንጂነር ህይወት አክለውም በእግረኛ መንገዶች ጠርዝ ላይ እየተሰሩ የሚገኙ የሸራ ሸዶች ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘቡ እና በጥናት ተደግፈው የተሰሩ ባለመሆናቸው የሚመለከታቸው የክ/ከተማና የወረዳ አመራሮች በጥቃቅን እና አነስተኛ ለተደራጁ ዜጎች የሚሰጡትን የንግድ ቦታ እግረኛ መንገዶች ላይ ጉዳት የማያስከትል መሆኑን በቅድሚያ ሊያረጋግጡ ይገባል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የእግረኛ መንገዶችን ከጉዳት ለመከላከል ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑን የገለፁት ኢንጂነር ህይወት በቀጣይም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ጎን ለጎን ከአዲስ አበባ ከተማ የፀጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ ከወረዳና ከክፍለ ከተማ አመራሮች እንዲሁም ከመሰረተ ልማት ቅንጅትና የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በትብብር በመስራት ችግሩን ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ሲሉ ኢንጂነር ህይወት ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ለጉዳት እየተዳረጉ ከሚገኙ የእግረኛ መንገዶች መካከል ከቆሬ አደባባይ አሚጎ ካፌ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ፣ ተክለ ሀይማኖት አካባቢ፣ ዘነበ ወርቅ፣ ወይራ፣ ቤቴል አደባይ፣ ከስድስት ኪሎ ወደ ፈረንሳይ በሚወስደው መንገድ ላይ እና ሌሎችም አካባቢዎች ይጠቀሳሉ፡፡

የመስሪያ ሱቆቹ እየተሰሩ ያሉት በመንገዶቹ ጠርዝ ላይ ቢሆንም ግብይት እየተፈፀመ ያለው የእግረኛ መንገዱ ላይ በመሆኑ ከመንገዱ ጉዳት ባሻገር እግረኞችን ለከፍተኛ የትራፊክ አደጋ ሊያጋልጥ ስለሚችል ፈቃድ ሰጪው አካል ጥንቃቄ ሊያደርግበት ይገባል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *