ስብሐት ነጋ ማን ናቸው?

ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ አገሪቱን በመራው ኢህአዴግ ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ የነበረው የህወሓት ቀደምት ታጋይና መሪ እንዲሁም ቁልፍ ሰው የነበሩት አቶ ስብሐት ነጋ በፌደራል መንግሥቱ ሲፈለጉ ከቆዩት ግለሰቦች መካከል አንዱ ነበሩ።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ መንግሥት ለግጭቱና ለቀውሱ ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮችን ለመያዝ የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው ሰዎች መካከል አቦይ ስብሐት ይገኙበት ነበር።

ከባላባት ቤተሰብ የወጡት የ86 ዓመቱ አዛውንት አቦይ ስብሐት ነጋ መምህር፣ የመንግሥት ሠራተኛ፣ ታጋይ፣ የህወሓት ሊቀመንበር፣ እንዲሁም በኢህአዴግና በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ ተደማጭና ተጽእኖ ፈጣሪ ሆነው ለአስርታት ቆይተው ነበር።

አቦይ ስብሐት ከዚህ ሁሉ ባሻገር በአገሪቱ ኢኮኖሚና የውጭ ጉዳይ ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ያላቸውን ተቋማትን ለመምራትም ችለዋል።

ከእነዚህም መካከል ብዙ ሲባልላቸው የነበሩትንና ህወሓት የትግራይ ሕዝብ ንብረት ናቸው ይላቸው የነበሩትን ግዙፎቹን የኤፈርት ድርጅቶችን ለዓመታት አስተዳድረዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራተጂያዊ ጥናት ተቋምን ጡረታ እስከ ወጡበት ጊዜ ድረስ በዋና ዳይሬክተርነት መርተውት ነበር።

አቦይ ስብሐት በአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች ሲፈለጉ ቆይተው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ በሆነ ገደላማ አካባቢ ከባለቤታቸውና ከእህታቸው ጋር ተይዘው ወደ አዲስ አበባ መወሰዳቸው ተዘግቧል።

ከአርባ ስድስት ዓመታት በፊት የካቲት 1967 ዓ.ም የህወሓትን የትጥቅ ትግል ከጠነሰሱት ታጋዮች መካከል አንዱ ናቸው፤ አንጋፋው ታጋይ አቶ ስብሐት ነጋ። አቦይ በሚል ቅጽልም ይበልጥ ይታወቃሉ።

አብዛኛዎቹ የህወሓት መስራቾች የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትግራይ ተወላጅ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ ቀደም ሲል በዩኒቨርሲቲው የትግራይ ብሔረ ተራመጆች ማኅበር (ማገብት) የሚል ስብስብ ነበር።

አቦይ ስብሐት የዚሁ ማኅበር ጠንሳሽ አባል ሆነው በቀጣይ ስለሚካሄደው የትጥቅ ትግልን በተመለከተ በሚደረግ ውይይት ላይ ከይርጋለም ወደ አዲስ አበባ እየመጡ ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ እንደነበር ከማኅበሩ አባላት አንዱ ለቢቢሲ ገልጿል።

የደጃዝማች ነጋ ልጅ ስብሐት

በጣልያን ወረራ ወቅት በ1928 ዓ.ም በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን ከታሪካዊቷ የዓድዋ ከተማ ወጣ ብላ በምትገኘው ዓዲ አቤቶ በምትባል ስፈራ ከባላባት ቤተሰብ ነው የተወለዱት።

አባታቸው ደጃዝማች ነጋ የወረዳ አስተዳደሪ/ገዢ የነበሩ ሲሆን ከእሳቸው ጋር ወደ ተለያዩ ቦታዎች እየተዘወሩ የጸሐፊነት ሥራ ይሰሩ እንደነበር በ1989 ዓ.ም ‘እፎይታ’ ከተባለው መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።

አቦይ ስብሐት ትምህርታቸው እዚያው በተወለዱባት በዓድዋ ከተማ ነበር የጀመሩት።

መጀመርያ የቄስ ተማሪ እንደነበሩም ይናገራሉ። በዚያው በቤተ ክህነት ስር በነበረው ዘመናዊ ትምህርት ቤት ቀጣዩን ትምህርታቸውን ጀመሩ።

በወቅቱ አባታቸው ‘ዛና ወዲ’ ወደ ሚባለው አከባቢ ሲዘዋወሩ እሳቸውም አብረው ተጉዘዋል። አባተቸው ‘አንተ ነህ የእኔ ወራሽ’ ይሏቸው እንደነበርና በልጅነታቸው በግብርና ሥራ ተሰማርተውም እንደነበር ያስታውሳሉ።

ሆኖም በወንድሞቻቸው ውትወታ ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰው እስከ 8ኛ ክፍል እዚያው ዓድዋ ውስጥ ተምረዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመቀለ ከተማ በአንጋፋው የአጼ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው የተከታተሉት።

ከሪፖርተር መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ትምህርት ዘግይተው መጀመራቸው “ያኔ [የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ] ታናሽ ወንድሜ በድግሪ ተመርቋል” ሲሉ ተናግረው ነበር።

አብሯቸው የተማረ ታጋይ አቦይ ስብሐት በ1955 ዓ.ም የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሆነው ፀረ ፊውዳሊዝም በነበረው የተማሪዎች ተቃውሞ ወቅት በትምህርት ቤቱ አንዱ ቀሳቃሽና የእንቅስቃሴው መሪ እንደነበሩ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በኋላ ላይ ወደ ትጥቅ ትግል ገብተው የህወሓት አመራር ሆነው ያገኛቸው ይሄው ታጋይ በነበራቸው ንቁ እንቅስቃሴያቸው ያስታውሳቸዋል።

አቦይ ስብሐት ወደ ዩኒቨርሲቲ ከመግባታቸው በፊት በስለሌና ጎሃ ጽዮን፣ በፍቼና በደብረ ብርሐን ከተሞች ተዘዋውረው አስታማሪ ሆነው ሰርተዋል።

ወደ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል የመጀመርያ ድግሪ ተመርቀዋል። በኢኮኖሚ ሚኒስቴር ውስጥም የኢኮኖሚ ባለሙያ ሆነው ለአንድ ዓመት ሰርተዋል።

“በዚህ ወቅት የብሔር ጥያቄ ይነሳ ስለነበር ወደ ትግራይ ዝውውር ጠየቅሁ” ሲሉ ከዓመታት በፊት ለእፎይታ መጽሔት የተናገሩት አቦይ ስብሐት፤ የዝውውር ጥያቄያቸው ተቀባይነት ስላለገኘ ወደ ትግሉ ለመቅረብ ሥራቸውን ለቀው ወደ መምህርነት ተመለሱ።

ከዚያም ወደ ዓድዋ ተመልሰው የንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ሆነው የሰሩ ሲሆን፤ እዚያም ብዙ ሳይቆዩ ወደ ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ይርጋለም ከተማ ተዘዋውረው አስተምረዋል።

“እዚያ አስተማሪ ሆኜ ሳለ ደርግ ወደ ስልጣን ወጣ” ሲሉም ለእፎይታ መጽሔት ተናግረዋል።

‘አቦይ’ የሚለውን ቅጽል እንዴት አገኙ?

አቦይ የሚል አጠራር በትግራይ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው አገላለጽ ነው። ቃሉ ዕድሜን ብቻ አመላካች ሳይሆን ‘ዋናው’ የሚል ትርጓሜም ሊሰጠው ይችላል።

ብዙ ጊዜም የአገር አባት ሆኖ በሽምግልናና በዕርቅ ላይ ለሚሳተፍና ትልቅ አክብሮት ለሚሰጠው ሰው የሚሰጥ መጠርያ ነው።

የአጼ ኃይለሥላሴ ሥርዓት የሸንጎ እንደራሴ አባል የነበሩትና ሥርዓቱን ተቃውመው ወጣቶችን መርተው ወደ ደደቢት በርሃ የወረዱት በትግል ስማቸው ስሑል ተብለው የሚታወቁት አቶ ገሰሰ አየለ አቦይ ስብሐትን በዕድሜ በ10 ዓመታት ይበልጡዋቸዋል።

ስሑል በ1968 ዓ.ም ነበር ሲሞቱ ከእሳቸው በኋላ በታጋዮቹ መካከል በዕድሜ የበለጡ ስብሐት ነበሩ። ታጋዮቹን የሚደግፉ አርሶ አደሮች ጺማሙን ታጋይ ስብሐት ነጋን ሲያዩ ‘አቦይ’ እያሉ ይተሯቸው ነበር።

ይህንንም ተከትለው የትግል ጓዶቻቸው ቀልደኛና ተጫዋች የነበሩትን ስብሐትን ‘አቦይ’ እያሉ መጥራት ጀመሩ።

ቀልደኛው ስብሐት በአንድ ወቅት መለስ ዜናዊ ታሞ ጓዶቹ በቃሬዛ ተሸክመው እየወሰዱት ሳለ መንገድ ላይ ያገኟቸው አርሶ አደሮች ‘ማን ነው የተሸከማችሁት?’ ተብለው ሲጠየቁ፤ አቦይ ስብሐትም ‘ምላስ ነው’ በማለት በቀልድ የታመመው ተናጋሪው መለስ እንደሆነ ምላሽ ሰጡ ተብሎ ይነገራል።

ስብሐት ብቻ ሳይሆኑ ብዙዎቹ የህወሓት ታጋዮች በትጥቅ ትግሉ ወቅት በተሰጣቸው ቅጽል ይጠራሉ። ‘አቦይ’ም በቁጥጥር ስር እስከዋሉበት እስካሁን ድረስ መጠርያቸው ሆኖ ቀጥሏል።

አቦይ ስብሐት በትግሉ ወቅት

በህወሓት የትጥቅ ትግል ወቅት በከተማ አደረጃጀት ተመድበው የነበረ ሲሆን፤ በትግሉ መጀመሪያ ዓመታት ከሰባቱ አመራሮች መካል አንዱ አቦይ ስብሐት ነበሩ።

በወቅቱ የድርጅቱ ጊዜያዊ ሊቀመንበር የነበሩት አረጋዊ በርሀ (ዶ/ር) ሲሆኑ፤ በ1971 ዓ.ም የድርጅቱ የመጀመሪያ ጉባኤ ከተካሄደ በኋላ አቦይ ስብሐት የመጀመሪያው ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።

የሊቀመንበርነቱን ቦታ መለስ ዜናዊ በ1981 ዓ.ም እስከተረከባቸው ጊዜ ድረስም ህሓትን ለአስር ዓመታት መርተዋል። በመጀመርያዎቹ የትጥቅ ትግል ዓመታት አቦይ ስብሐት ቆራጥ ታጋይ እንደነበሩ ጓዶቻቸው ይመሰክራሉ።

ሆኖም ግን በድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ውስጥ የእርስ በርስ ትስስር (ኔትወርኪንግ) እንዲሰፍንና ክፍፍል እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል በሚል በተደጋገሚ ይወቀሳሉ።

በ1968 ዓ.ም በድርጅቱ ውስጥ የተከሰተው ‘ሕንፍሽፍሽ’ በሚል የሚታወቀው መከፋፈልና በ1977 ዓ.ም እነ አረጋዊ በርሀ (ዶ/ር) እና አቶ ግደይ ዘርአጽዮን ከድርጅቱ እንዲገለሉ አንዱ ምክንያት እሳቸው እንደሆኑ ይነገራል።

ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ በ1993 ዓ.ም በተከሰተው ክፍፍል ወቅት ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ‘አንጃ’ ተብለው ለእስርና ለስቃይ የተዳረጉ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ነበሩ።

አቦይ ስብሐት የአገሪቱ የደኅንት ተቋም፣ መከላከያ ሠራዊቱና የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን እንዲቆሙ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸው ይነገራል።

ሆኖም ግን በአቶ መለስ የስልጣን ዘመን መጨረሻ አካባቢ በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ለረዥም ጊዜ የበላይ ሆነው ሲመሩት ከነበረው ታላላቅ የምርትና የአገልግሎት ተቋማትን ከሚያንቀሳቅሰው ኤፈርት ኃላፊነት በመነሳታቸው ደስተኛ እንዳልነበሩ ይነገራል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም በአቦይ ስብሐት ምትክ መጀመሪያ ለተወሰነ ጊዜ በአምባሳደር አባዲ ዘሞ፣ ቀጥሎ ደግሞ ባለቤታቸውን ወይዘሮ አዜብ መስፍንን ሾመው ግዙፉን ተቋም እንዲመሩ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ህወሓት የከፍተኛ ካፒታል ባለቤት የሆኑ ተቋማትን በውስጡ የያዘው ኤፈርት የትግራይ ሕዝብ ንብረት መሆኑን ሲገልጽ የቆየ ቢሆንም፤ ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በድርጅቱ በሚመደቡ የፖለቲካ ሹመኞች ነበር ሲተዳደር የቆየው።

አቦይ ስብሐት ምን ብለው ነበር ?

የህወሓት አመራሮች በመርህ ደረጃ ማዕከላዊነትን የተከተለ የጋራ አመራር የሚከተሉ በመሆናቸው ከድርጅቱ ውጪ በነጻነት የራሳቸው ሐሳብ የመግለጽ ዝንባሌ የላቸውም።

አቦይ ስብሐት ይህንን ቢያውቁም ከሌሎቹ በተለየ የመሰላቸው በነጻነት ከመናገር አይቆጠቡም።

ባለፈው ዓመት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ “በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ መሰረት ያደረገ ትግል አይሳካም” ማለታቸው ይታወሳል።

ከኤርትራ ጉዳይ ጋር በተያዘ “ህወሓት ከሻዕቢያ በላይ ለኤርትራ ነጻነት መስዋዕት ከፍሏል” ብለው በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆነው ነበር። ለዚህም እንደ ምክንያት “ሻዕቢያ በመጨረሻው ሰዓታት ከደርግ ሥርዓት ጋር ድርድር ጀምሮ ነበር” በሚል ይከሳሉ።

አቦይ ስብሐት ኢህአዴግ ውስጥ ከፍተኛ ሙስና እንደተንሰራፋ በግልጽ ሲናገሩ ይታወቃሉ።

“ሙስና እየተንፏቀቀ የሚመጣ በሽታ ነው” የሚሉት አቦይ ስብሐት፤ ከሙስና ጋር የእርሳቸውም ስም እንደሚነሳ ጠቅሶ ቢቢሲ ጥያቄ አቀርቦላቸው ነበር።

“መጣራት አለባት። ማን ነው ሙሰኛ? ንጹህስ ማን ነው? ብሎ የሚያጣራ ጀግና አልተገኘም። ቆራጥነት የለም” በማለት ባልተጣራ ሁኔታ “እኔ እንዲህ ነኝ ማለት አልችልም” ብለው ነበር።

ከሁለት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ሥልጣን የመጡበት መንገድ ውስጥ የአሜሪካን እጅ አለበት ብለው የሚያምኑት አቦይ ስብሐት “ካዘዙን በላይ ኢህአዴግ ፈርሷል። ሕገ መንግሥቱም ፈርሷል፤ የፌዴራል ሥርዓቱም ፈርሷል” ሲሉ በአደባባይ ይወቅሱ ነበር። ቢቢሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *