“ስብሀት ነጋ በዚህ መልኩ በቁጥጥር ስር መዋል የኢትዮጵያን ህዝብ በድሎ በሰላም መተኛት እንደማይችል የሚያስተምር ነው ” አቶ ሊላይ ኃይለማርያም የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራር

የጁንታው ቁንጮ ስብሀት ነጋ በዚህ መልክ በቁጥጥር ስር መዋሉ የኢትዮጵያን ህዝብ በድሎ በሰላም መተኛት እንደማይችል የሚያስተምር እንደሆነ አቶ ሊላይ ኃይለማርያም አስታወቁ፡፡

የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ሊላይ ኃይለማርያም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ የጁንታው ስብሐት ነጋ በዚህ መልኩ ተዋርዶ መያዝ ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሠርቶ ማምለጥ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ በድሎ በሰላም መተኛት እንደማይችል ያሳየ ነው።

የህወሓት ጁንታ ቡድን ሲፈጠር ጀምሮ ከአንድ ቤተሰብ (ከስብሐት ነጋ ቤተሰብና አካባቢ) የወጣ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሊላይ ፣የኢትዮጵያን ኢኮኖሚም ሆነ ፖለቲካ በዚህ የቤተሰብ ኔትዎርክ በመያዝ አገሪቷን ሲዘርፍ ኖሯል ብለዋል።

በቤተሰብና በአካባቢ ተደራጅቶ ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሀብት ሲዘርፍ የቆየው የህወሓት ጁንታ አዲስ አበባ ውስጥ ከ600 ሺ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚከራይ ሕንፃ ያላቸው ጄኔራሎችን መፍጠሩን አመልክተዋል።

የጁንታው አባላት እነሱ እንደሚሉት ሳይሆን በትግራይ ህዝብ ላይ በፈጸሙት ክፋት እና በደል ፤ አደህይተው ለመግዛት ባደረጉት ጥረት በጣም የተጠሉ ሆነዋል፤ ይህንን ደግሞ ልቦናቸው በሚገባ ያውቃል ያሉት አቶ ሊላይ ፣ የትግራይ ህዝብ እነሱን አጥቶ ለአንድ ሳምንት እንኳን መኖር እንደማይችል ሲያስወሩ ቢኖሩም ነገሩ ግን በፍጹም ከሚሉት ተቃራኒ ነው ብለዋል ።አሁንም በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑ ህዝቡን ከሚገባው በላይ እያስደሰተው መሆኑን አስታወቀዋል፡፡

አሁን ላይ የህግ ማስከበር ዘመቻው ተጠናቅቆ እነዚህ አካላት በመከላከያ ሠራዊት እየተያዙ መሆኑ ለመላው ኢትዮጵያውያን ደስታን የሚፈጥር ቢሆንም ለትግራይ ህዝብ ደግሞ የድል ድል ሆኖ ነው ያገኘነው ያሉት አቶ ሊላይ ፤ጁንታው ለትግራይ ህዝብ ታሪካዊ ጥላት ነው። ላለፉት 46 ዓመታት የትግራይን ህዝብ ሲያርዱ ፣ሲገድሉ በስሙ እየነገዱ እነሱ ሲበለጽጉ ኑሯቸውን በተቀናጣ ሁኔታ ሲመሩ የነበሩ ናቸው ብለዋል።

እነዚህ ሰዎች ከዚህም አልፈው ኢትዮጵያውያንን በብሔር በቋንቋ ሲከፋፍሉ፣ ሲያራርቁና ደም ሲያቃቡ የኖሩ ሴረኞች መሆናቸውን አመልክተው ፣ አሁን መንግሥት ህግ በማስከበር ዘመቻው የወሰደው ዕርምጃ ከምንም በላይ ትግራይን ብሎም መላው ኢትዮጵያን ነፃ ያወጣ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የትግራይ ህዝብ በእነዚህ ፋሽስቶች መማረሩንና ከላዩ ላይም እንዲነቀሉለት መፈለጉ የሚታወቀው መከላከያ ሠራዊትን እየደገፈ መውጫ መግቢያቸውን እያሳየ ከተደበቁበት ጎሬ ተፈንቅለው እንዲወጡ የራሱን ሚና እየተጫወተ መሆኑ ነው ያሉት አቶ ሊላይ ፣ በዘመቻው መቶ በመቶ በሚባል ሁኔታ ተሳትፎውን አሳይቷል በማሳየት ላይም ነው ብለዋል። የትግራይ ህዝብ ጁንታው በፍጥነት ከላዩ ላይ ተነቅለው ወደቀድሞ ሰላሙና ልማቱ የሚገባበትን ቀን እየናፈቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *