የክልል ልዩ ኃይሎች

በ2000 አመተ ምህረት አገር በሚሊኒየም በዓል አከባበር ደምቆና ትኩረት ስቦ በነበረበት ወቅት፣ በሱማሌ ክልል በነዳጅ ሀብት ፍለጋ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ኢትዮጵያውያንና ቻይናውያን ላይ በኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንቦር (ኦብነግ) በተፈጸመ ጥቃት የበርካቶች ሕይወት ይቀጠፋል፡፡ በተደጋጋሚ በኦጋዴን የነዳጅ አሳሾችና ጎብኚዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ያሳሰበው መንግሥትም፣ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥትን በማስተባበር ከመደበኛ የፖሊስ ኃይል የተለየ ሥልጠናና ትጥቅ ያላቸውን የሶማሌ ልዩ ኃይሎች በማቋቋም ሰርጎ ገቦችን ማጥቃት ተያያዘ፡፡

ይኼ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ግን ሰርጎ ገብ ሆነው ንፁኃንን የሚያጠቁ ቡድኖችን በመከላከል ብቻ ሳይታጠር፣ በክልሉ ያሉ ንፁኃን ዜጎችን ማጥቃትና የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈጸም እስከ መከሰስ የደረሰ ቡድን ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ በመጋቢት ወር 2010 ወደ ሥልጣን እስከሚመጡ ድረስ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት በመሆን የመሩት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ)፣ ይኼንን ኃይል በመጠቀም የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲፈጽሙ እንደነበር ሲነገር ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን በመጡ በወራት ውስጥ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፣ በሶማሌ ክልል ሰዎችን በእስር ቤት ከማሰቃየት ባለፈም እስረኞችን እንደ አንበሳ ካሉ አራዊት ጋር አብሮ እስከ ማሰር የደረሰ ክፋት እንደሚፈጸም ገልጸው ነበር፡፡

ይኼ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በአካባቢው ላለው የፀጥታ ችግር መፍትሔ እንዲሆንና ሰላም ለማስፈን ከመደበኛ ፖሊስ ከፍ ያለና ሥፍራውንና ቋንቋውን የሚያውቅ ኃይል በማስፈለጉ የተመሠረተ ሲሆን፣ አመሠራረቱም ጥቃት ፈጻሚ ቡድኖች አባላት በሚመለምሉበት አግባብ የተመለመሉ አባላት ያሉት ኃይል እንደሆነ የተለያዩ ጽሑፎችና ሰነዶች ያሳያሉ፡፡

ልዩ ኃይል የሚል ስያሜን የተሸከሙና ከመደበኛ ፖሊስ ከፍ ያለ የሥልጠናና ትጥቅ ያላቸው የክልል ኃይሎች በሶማሌ ክልል ሳይቆሙ፣ በአሥሩም የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚታዩና አዳዲስ ክልሎችም ሲመሠረቱ መጀመርያ ከሚፈጽሟቸው ተግባራት አንዱ እስከ መሆን ደርሰዋል፡፡ ለአብነትም የሲዳማ ክልል በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. በይፋ ከተመሠረተ በኋላ በነሐሴ ወር 2012 የመጀመርያ ዙር የልዩ ኃይል አሠልጥኖ አስመርቋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያትም በተለይም በትግራይ፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተደጋጋሚ ዙሮች የልዩ ኃይሎች እየሠለጠኑ ሲመረቁ ይታያል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ ክልሎች በልዩ ኃይላቸው ፉክክር የያዙ ይመስላል ሲሉ ሁኔታውን ይገልጹታል፡፡

እነዚህ የልዩ ኃይሎች ወታደራዊ ባህርይ ያላቸው በመሆናቸውና ሥልጠናቸውና ትጥቃቸው ከመደበኛ ፖሊስ በእጅጉ የተለየ በመሆኑ፣ እንዲሁም በቁጥራቸው በርከት ያሉና በክልል ያሉ የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት ብቻ እንዲያገለግሉ የሠለጠኑ ስለማይመስሉ፣ የተለያዩ ታዛቢዎችና አስተያየት ሰጪዎች በተደጋጋሚ ሥጋታቸውን ሲገልጹ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ ይኼ አጀንዳ በትግራይ ክልል የነበረውን ጦርነት ተከትሎ እንደ አዲስ እየተስተጋባ ነው፡፡

በትግራይ ክልል በተለያዩ ዙሮች የሠለጠኑና በተደጋጋሚ ትርዒቶች የትጥቅና ሥልጠና ብቃታቸውን ሲያሳዩ የነበሩ የልዩ ኃይል አባላት፣ በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ አገሪቱን ወደ ጦርነት ያስገባ ክስተት በመፈጠሩ፣ ይኼንንም ተከትሎ ከፍተኛ የሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ በመድረሱ፣ የክልል ልዩ ኃይሎች ይኼን ያክል የተደራጁና የሠለጠኑ መሆናቸው በርካታ ጥያቄዎችን ማስነሳት ጀምሯል፡፡

ከዚህ ባለፈም የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት ተሳትፎ አድርጎ ከተመለሰ በኋላ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የዜጎች ጥቃትና ግድያ ተከትሎ ‹‹በርካታ የአማራ ብሔር ተወላጆች ናቸው እየተገደሉ ያሉት›› በሚል ምክንያት የፌዴራል መንግሥት በአካባቢው ሰላም ለማስከበር ካልቻለና ሥራ ከበዛበት፣ የአማራ ክልል ኃይል ሊያሰማራና መፍትሔ ሊያበጅለት እንደሚሻ የአማራ ክልል ፖሊስ ኪሚሽነር አበረ አዳሙ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይኼም እንዲህ መሰል ኃይሎች በሌሎች ክልሎች ጣልቃ ሊገቡ እንደሚችሉም ማመላከቻ ነው ያሉ አልጠፉም፡፡

ይባስ ብሎም በሶማሌና በአፋር ክልሎች የሚፈጠሩ ግጭቶች የሁለቱን ክልሎች ልዩ ኃይሎች ያሳተፉ መሆናቸው፣ ‹‹እነዚህ ኃይሎች የሰላም ጠባቂዎች ናቸው? ወይስ ሥጋቶች?›› የሚሉ ድምፆች መሰማት ጀምረዋል፡፡

መንግሥትም ይኼ ሥጋት የገባው በሚመስል ሁኔታ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል የመሥሪያ ቤታቸውን የሦስት ወራት ሪፖርት ኅዳር 23 ቀን 2013 ለፓርላማው ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ እነዚህ ኃይሎች ኢሕገ መንግሥታዊ በመሆናቸው ሊታሰብበት እንደሚገባ በማስታወቅ፣ አስፈላጊ ከሆነም ፓርላማው ሕግ ሊያወጣበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም አሳስበዋል፡፡

ሚኒስትሯ በፓርላማ ማብራሪያቸው የፖሊስ ሕጉ ክልሎች የራሳቸው ፖሊሶች ይኖራቸዋል ሲል መደበኛ ሥልጠና ያገኘ ፖሊስ እንጂ፣ ከፊል የመከላከያ ኃይል ባህሪ ይኖራቸዋል ማለት አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ፣ የመደበኛ ፖሊስ ሥልጠናው፣ ትጥቁና ሥምሪቱ በግልጽ ምን እንደሆነ ይታወቃል ብለዋል፡፡

ከዚህ የሚኒስትሯ ንግግር መረዳት እንደሚቻለው በአገሪቱ የፖሊስ ኃይል ውስጥ ዓለም አቀፍ ክስተት የሆነው ፖሊስን ወታደራዊ የማድረግ ተግባር እዳለ የሚያሳይ ሲሆን፣ ይኼ ክስተት በተለያዩ አገሮች ሊመጣ የቻለው የታጠቁና የተደራጁ ወንጀለኛ ቡድኖች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ተከትሎ እንደሆነ መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ቻርለስ ኮች ኢንስቲትዩት በጥናቱ አስታውቋል፡፡ ይህ ፖሊስን ወታደራዊ የማድረግ ተግባር ግን ኅብረተሰቡ በፖሊስ ኃይሉ ላይ ያለው ዕምነት እንዲሸረሸር ማድረጉንና የሕግ ማስከበር ተግባርንም የሚጎዳ እንደሆነ በግኝቱ አስነብቧል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጄይላን እነዚህን ልዩ ኃይሎች የሚገዛ ምንም ዓይነት ሕግ እንደሌለና ሥልጠናቸውም ሆነ ትጥቃቸው የሚገዛበት ስታንዳርድ (ደረጃ) እንደሌለ በመጥቀስ፣ እነዚህን ኃይሎች ለመቆጣጠር አዳጋች እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

‹‹ልዩ ኃይሎችን የሚገዛ ምን ሕግ አለ? ምንም፡፡ እነሱን የሚገዛ ሕግ የለም እኮ፤›› የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ ስማቸውም ልዩ ኃይል እንደሚባልና ሥልጠናቸውም ሆነ ትጥቃቸው ከፖሊስ ኃይል እንደሚለይ ይጠቅሳሉ፡፡ ይኼም ለክልሎች የተሰጠውን ፖሊስ የማደራጀት ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት የሚጥስ እንደሆነ በማሳወቅም፣ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 52 ለክልሎች የሚሰጠውን የፖሊስ ኃይል የማደራጀት ሥልጣን ግን እንደ ክፍተት ክልሎች እየተጠቀሙ እኛ ያደራጀነው የፖሊስ ኃይል ነው የሚል መከራከሪያ እንዳላቸውም ያወሳሉ፡፡

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው አጭር የስልክ ቆይታ በአማራ ክልል እንዲህ መሰል ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ኃይል እንደሌለና ክልሉ ያለው ‹‹ልዩ ኃይል ፖሊስ›› እንደሆነ በመግለጽ፣ በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ እየሠሩ እንደሚገኝ በማንሳት ተከራክረዋል፡፡ በማከልም ሕገወጥ የሆነው ቡድን የት እንዳለ ያውቀዋል፣ ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና ኮሚሽነሩ የትኛው ክልል ወይም ቦታ እሳቸው የሚሉት ሕገወጥ ቡድን እንዳለው ያልገለጹ ሲሆን፣ በአማራ ክልል የሚገኘውና እሳቸው ‹‹ልዩ ኃይል ፖሊስ›› የሚሉት ኃይል ያለው የሥልጠና ደረጃና ትጥቅ፣ ከመደበኛ ፖሊስ ኃይል ጋር ልዩነው ስላለው ማብራሪያ እንዲሰጡ ሲጠየቁ ግን ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

በቅርቡ በርካታ ቁጥር ያለውን የልዩ ኃይል አሠልጥኖ ያስመረቀው የኦሮሚያ ክልል ለልዩ ኃይል ራሱን የቻለ ኮሚሽነር ያለው ሲሆን፣ የመደበኛ ፖሊስ ኮሚሽነሩም ሆኑ የልዩ ኃይል ኮሚሽነር ከአዲስ አበባ ውጪ ለሥራ በመሰማራታቸው ስለክልሉ ልዩ ኃይል ማብራሪያ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡

አቶ ጄይላን በበኩላቸው የሁሉንም ክልል ልዩ ኃይሎች የትግራይ ክልል ልዩ ኃይል ያደረሰውን ጥቃት እያነሱ ማመሳሰልና በአንድ ዓይን ማየት እንደማይገባ በማሳሰብ፣ እነዚህ ኃይሎች ግን ለአንድ ክልል ወይም ለአንድ የፖለቲካ ኃይል አገልግሎት እንዳይሰጡ በአገር አንድነት አስተሳሰብ ሊቃኙ ይገባል ይላሉ፡፡

በባልሲል የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዳይሬክተርና የሰላምና ፀጥታ፣ እንዲሁም የወታደራዊ ባለሙያዋ አን ፊትዝ ጄራልድ (ፕሮፌሰር) የክልል ልዩ ኃይል ተብለው የሚዋቀሩ ምልምሎች ለአገራዊ ደኅንነት ሥጋት ሊደቅኑ እንደሚችሉ ይጠቁማሉ፡፡

‹‹በአንዳንድ ክልሎች የአገር መከላከያ ኃይል ሰላምና ደኅንነትን ማስጠበቅ ካልተቻለ፣ ከፊል ወታደራዊ የሆኑት የክልል ልዩ ኃይሎች ለብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይኼንንም የምልበት ምክንያት ክልሎች በፌዴራል ካለው መንግሥት ጋር መጠነኛ ልዩነት ካላቸው፣ በሥራቸው ያሉትና ወታደራዊ ባህርይ ያላቸው ኃይሎች ለተለያዩ አካላት ታማኝነት ስለሚኖራቸውና በተለያዩ የዕዝ ሰንሰለቶች ስለሚገዙ፣ ለሚያዟቸው ባለሥልጣናት ብቻ ተገዥ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነው፡፡ ይኼም ሁለቱ አካላት ወደ ግጭት እንዲገቡ ሊያደርግ ይችላል፡፡ የፖለቲካዊ አስተሳሰብ ብዝኃነት በሚኖርበት የፌዴራል ሥርዓት ደግሞ ክልሎች ከፌዴራል መንግሥቱ የተለየ ፓርቲ ሊያስተዳድራቸው ስለሚችል፣ ይኼንን መሰል ልዩ ኃይሎች መኖራቸው ለግጭት በር ከፋች ይሆናል፤›› ይላሉ፡፡

ይሁንና የክልል ልዩ ኃይሎች ለአገራዊ ሰላም ጥቅም አልባ ናቸው ብለው እንደማያምኑ አልሸሸጉም፡፡ የእነዚህ ኃይሎች አንዱ ጥቅም ሊሆን የሚችለው የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ችግር በተከሰተባቸው አካባቢዎች በፍጥነት ደርሰው፣ ለኅብረተሰቡ አስፈላጊውንና ተቀባይነት ያለው ጥበቃ መስጠት በማይችሉበት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡

‹‹በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለክልል መንግሥታት ደኅንነት ተጨባጭና የሚታይ ሥጋት ሲኖር ልዩ ኃይሎች በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ የክልሎችን የፀጥታ መዋቅር አቅም ሊያጠናክሩ ይችላሉ፤›› በማለት የሚያብራሩት ፕሮፌሰሯ፣ ‹‹ይሁንና በሕግ በተቀመጠው መሠረት ክልሎች የፌዴራል መከላከያ ሠራዊትንም ሆነ ሌላ የፀጥታ መዋቅርን ለድጋፍ መጠየቅ የሚችሉ በመሆኑ፣ የክልል ልዩ ኃይሎች መኖራቸው ፉክክር ሊያመጣ የሚችልና የግብር ከፋዩ ገንዘብ በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳይውል እንዲባክን ሊያደርግ የሚችል ነው፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

የክልል የፀጥታ ኃይሎች ለአገራዊ ኃይሎች እንደ ማቆሪያ ሊያገለግሉ የሚገባቸውና በተፈጥሮ አደጋ አልያም አገርዊ ለሆኑና ወታደራዊ ብቃት ለሚጠይቁ ፍላጎቶች በየትኛውም ጊዜ ሊጠሩ የሚችሉ መሆን የሚገባቸው ቢሆንም፣ አደገኛና የውትድርና ብቃትን የተላበሱ መሆን አይኖርባቸውም ይላሉ፡፡

በአሜሪካ እንዳለው ናሽናል ጋርድ እንደ እሳት አደጋና ጎርፍ ያሉ ክልላዊ ጉዳዮችን ለመወጣት ለክልሎች ተጠሪ ሆነው የሚቋቋሙ የክልል ኃይሎች መኖር እንደሚችሉ በመጠቆም፣ እነዚህ ኃይሎች ግን ጎረቤታቸው የሆነው ክልል ለመውጋት መዋል እንደሌለባቸው ይጠቁማሉ፡፡

ይኼንን ዕሳቤ የፌዴራል ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጄይላንም የሚጋሩት ሲሆን፣ ፖሊሶች ከየትኛውም የፖለቲካም ሆነ የብሔር ተፅዕኖ ነፃ መሆን ይኖርባቸዋል በማለት፣ ለየትኛውም ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ተገዥ ሊሆኑ አይገባም ይላሉ፡፡ ከዚህ አልፎም እንደ ሶማሌና አፋር ክልል ልዩ ኃይሎች ግጭት ውስጥ መግባት እንደማይኖርባቸውም ያሳስባሉ፡፡

ከዚህ በተረፈም እየተጠናከሩና እየበዙ የመጡት የክልል ልዩ ኃይሎች ለመከላከያም ሆነ ለፌዴራል ፖሊስ ሊመለመሉ የሚችሉ የሰው ኃይሎችን በመውሰድ ረገድ ተፅዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል በመጥቀስ፣ የሰው ኃይል ብክነት ሊከሰት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በተጨባጭ ይኼ ክስተት መኖሩንና ተፅዕኖውም በተቋማቱ ላይ ምን ያህል እንደሆነ በዝርዝር አላስቀመጡም፡፡ በክልሎች እያደገና እየሰፋ መምጣቱ በአገር አቀፍ የፀጥታ ኃይሎች ላይ ይኼንን መሰል የሰው ኃይል መሟጠጥ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ፕሮፌሰር ፊትዝ ጄራልድ ይናገራሉ፡፡

ለሪፖርተር ጥያቄዎች በኢሜይል ምላሽ የሰጡት ፕሮፌሰሯ፣ ‹‹በክልሎች ያለውንና እየተስፋፋ የሚገኘው ልዩ ኃይል የፌዴራል ፖሊስንም ሆነ የፌዴራል መከላከያ ሠራዊትን ሊደግፉ የሚችል የሰው ኃይልን ሊጎዳ ይችላል፤›› ይላሉ፡፡

የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች አገር አቀፍና ፖለቲካዊ ወገንተኝነት አይኖራቸውም ተብሎ ስለሚታሰብ፣ በክልሎች እንዲህ ጡንቻቸው የፈረጠሙ የልዩ ኃይሎች መኖራቸው እውነተኛ ወካይነት ያላቸውና ለሕዝብ የቆሙ ተቋማትን በመገንባት ረገድ፣ በብሔራዊ ኃይሎች ላይ ጫና ሊያሳርፍ ይችላል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በፓርላማው አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለመከላከያ ሠራዊት ቅጥር ማስታወቂያ ወጥቶ ብዙ ቁጥር ካላቸው አማራና ኦሮሚያ ክልሎች፣ ከእያንዳንዳቸው 1000 ያህል ምልምል ማግኘት አዳጋች እንደነበር አውስተው ነበር፡፡ ይኼንንም በርካቶች ከክልል ልዩ ኃይሎች ግንባታና መጠናከር ጋር ያያያዙት ሲሆን፣ በክልሎች ወጣቶች በገፍ እየተመለመሉ በልዩ ኃይል ስም ወታደራዊ ሥልጠናና ትጥቅ እንዲያገኙ መደረጉ ለዚህ ምክንያት ነው ሲሉ የተከራከሩ በርካቶች ናቸው፡፡ አቶ ጄይላን፣ ይኼንን የተዘበራረቀ የፖሊስ ኃይሎች መዋቅርና ደረጃ ለመፍታት አገር አቀፍ የፖሊስ ኃይል ስታንዳርድ (ደረጃ) ማውጣትና መተግበር ዓይነተኛ መፍትሔ ነው ይላሉ፡፡

‹‹እነዚህ ኃይሎች እንደገና ሥልጠና ተሰጥቷቸው እንዳስፈላጊነቱ የፌዴራል ፖሊስን አልያም መከላከያውን እንዲቀላቀሉ ማድረግም ይቻላል፤›› ይላሉ አቶ ጄይላን፡፡ ይሁንና የፖሊስ ኃይል ሥልጠናም ሆነ የትጥቅ ስታንዳርድ ለማውጣት ክልሎች፣ የሚያሠለጥኗቸውና የሚያደራጇቸው ልዩ ኃይሎችን በሕገ መንግሥቱ በተሰጠን ሥልጣን መሠረት ነው የምናከናውነው ማለታቸው እንቅፋት ሊሆን እንደሚችልም ይጠቁማሉ፡፡

የአገር አቀፍ የፖሊስ ደረጃ ማውጣትና መተግበር አስፈላጊነት አሌ የማይባል መሆኑን ፕሮፌሰር ፊትዝ ጄራልድ እንደሚገነዘቡ በማስታወቅ፣ ለዚህ የሚረዱ ሕጎች ከላይ ወደ ታች መውረድ ያለባቸውና ፌዴራል ፖሊስ የሚገዛባቸው ሕጎች ለክልሎችም እንዲሠሩ ማድረግ አግባብ ነው ይላሉ፡፡

‹‹ሕጎች በአገር አቀፍ ደረጃ በፌዴራልና በክልሎች እንዲተገበሩ የሚፈለግ ከሆነ፣ ከላይ መጀመር ነው ያለበት፡፡ ለፌዴራል የሠራን ሕግ ለክልሎችም መተግበር አዳጋች ይሆናል፡፡ የክልል ልዩ ኃይሎች የሚፈርሱ ከሆነ እንደ ፖሊሲ፣ ዶክትሪን፣ ሕግና ሥልጠናዎችን የመሳሰሉ የሰው ኃይል ግንባታ ተግባራት ለክልሎች መሰጠት ይኖርበታል›› ሲሉም ይመክራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ኃይሎች በተለይ በትግራይ፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲስፋፉ በመረደጉ እነዚህን ኃይሎች ለመቀነስ በርካታ ዓመታት ሊፈጅ መቻሉን አልሸሸጉም፡፡

‹‹ለወደፊት የሚቀጠሩ የክልል ፀጥታ ኃይሎች ቁጥር ደፍ ሊበጅለት ይገባል፤ የመሣሪያና የትጥቅ አቅማቸውም በስምምነት ደረጃ ሊበጅለት ይገባል፡፡ ከወንጀል ሕጉ በመቅዳትም ሥልጣን በተሰጠው አካል ከስምምነት የተደረሰባቸውን የመሣሪያና ትጥቅ ደረጃዎች ቁጥጥር ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይኼንን መሰል ሕግ የተለያዩ ኃይሎች ጥቅም ላይ የሚውሉባቸውን ግልጽ ሁኔታዎች መደንገግ ይኖርበታል›› ሲሉ ያሰምራሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በተደረጉ የፀጥታና ደኅንነት ዘርፍ ማሻሻያ አንዱ ተግባር የአገሪቱን ፀጥታ ኃይሎች ደረጃ ማውጣትና መተግበር ቢሆንም፣ ይኼ ደረጃ የማውጣት ተግባር በሒደት ላይ መሆኑ ከተገለጸ ዓመታት ቢፈጅም ከምን እንደደረሰ ግን እስካሁን አልተነገረም፡፡ ከዚህ ጋር ሊገናኝ የሚችል የቅርብ ጊዜ ክስተት የፖሊስ ዶክትሪን መፅደቅና መተግበር ሲሆን፣ ይኼም በሰላም ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ ለፌዴራል ፖሊስ እንዲሆን የተሰጠ ነው፡፡ (ብሩክ አብዱ በሪፖርተር ጋዜጣ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *